የደ.ሱዳን የተኩስ አቁምም ስምምነት ተስፋ | አፍሪቃ | DW | 18.01.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የደ.ሱዳን የተኩስ አቁምም ስምምነት ተስፋ

የደቡብ ሱዳን መንግሥት፤ ከአማጽያኑ ጋር በቅርቡ የተኩስ አቁም ሥምምነት ለመድረስ ተስፋ እንዳለዉ መግለጹን አሁን ማምሻዉን የደቡብ ሱዳን መንግሥትን ጠቅሶ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገበ። በሌላ በኩል በኢጋድ የቀረበዉ መደራደርያ ነጥብ በአማፅያኑ ተቀባይነት ማግኘቱን ተልጸዋል።

የፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ቃል አቀባይ እንደገለፁት፤ የሳልቫኪርን መንግሥት በመወከል አዲስ አበባ ላይ የተጀመረውና የተገታዉ ፤ የመንግሥትና የአማፅያን የተኩስ አቁም ድርድር ላይ የቀረቡት ግለሰብ ወደ ጁባ ተመልሰዉ ምክር ከወሰዱ በኋላ ዉሉን ለመፈራረም ወደ አዲስ አበባ ለማቅናት በዝግጅት ላይ ናቸዉ። በዚህም ለሰላም ስምምነቱ የሚያበቃዉን ዉል ነገ ወይም የፊታችን ሰኞ ለመፈረም ተዘጋጅተዋል። በሌላ በኩል የአማፅያኑ ተደራዳሪና ከፍተኛ ባለስልጣን፤ ማቢዮር ጋራንግ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ ለመድረስ በኢጋድ የቀረበዉ መደራደርያ ነጥብ በአማፅያኑ ተቀባይነት ማግኘቱን አዲስ አበባ ላይ ገልጸዋል። የደቡብ ሱዳን መንግሥት እና የአማጽያኑ ተወካዮች ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአዲስ አበባዉ ሸራተን ሆቴል ለድርድር መቅረባቸዉ ይታወቃል። በሌላ በኩል በደቡብ ሱዳን መንግስት ወታደሮችና በአማጽያን መካከል የሚደረገዉን ዉግያ በመሸሽ ነዋሪዎች የደቡብ ሱዳንዋን ቦር ከተማ ለቀዉ መዉጣታቸዉን የተመድ አስታወቀ። እንደ ድርጅቱ ቃል አቀባይ ገለጻ በአሁኑ ሰዓት በከተማዋ ምንም አይነት ሲቢል ነዋሪ አይገኝም። ከተማዋ ለአንድ ሳምንት ከቀጠለ ጦርነት በኋላ በአማጽያኑ እጅ ወድቃ እንደነበርና ዛሬ በመንግሥት ወታደሮች እጅ ዳግም መግባትዋን የፈረንሳይ ዜና ወኪል AFP አመልክቷል። የጆንግላይ ግዛት መዲና ቦር፤ ከጁባ በስተሰሜን 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። የፕሬዝዳት ሳልቫ ኪር መንግሥት ጦር እና የቀድሞዉ ምክትል ፕሬዝዳት ሪክ ማቸር ደጋፊዎች የጀመሩት ዉጊያ፤ ከሁለቱም ወገን በኩል ህጻናት በዉትድርና መሳተፋቸዉን የተመድ ዛሬ ይፋ አድርጓል። አዲስ አበባ ላይ የተጀመረው የመንግሥትና የአማፅያን የተኩስ አቁም ንግግር በነበረበት እንደተገታ ነው። ለአንድ ወር በዘለቀዉ በዚህ የዕርስ በርስ ጦርነት በሽዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መገደላቸዉ ይታወቃል።

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ