1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችኢትዮጵያ

የደራ ወረዳ የጸጥታ ችግር

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 16 2017

በኦሮሚያ ክልል የምትገኘው ደራ ወረዳ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና የፋኖ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ ሰላም ርቋታል። ነዋሪዎች እንደሚሉት ሰዎች በታጣቂዎች ይታገታሉ፣ ይገደላሉ። ወረዳዋ ከአዲስ አበባ የሚያገናኟት መንገዶች መዘጋታቸውን የገለጹ የአካባቢው ነዋሪ “ለወላዶች ሕክምና ማግኘት ፈተና ሆኗል፤ መድሐኒት ማግኘት ከባድ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4mGQP
ኦሮሚያ ክል
የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች በሚዋሰኑበት አካባቢ የምትገኘው ደራ ወረዳ ከአዲስ አበባ የሚያገናኟት መንገዶች ከተዘጉ ሁለት ዓመታት ገደማ እንደሆነ ነዋሪዎች ይናገራሉ።ምስል Seyoum Getu/DW

የደራ ወረዳ የጸጥታ ችግር

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ስር በምትገኘው ደራ ወረዳ ባለፉት ጢቂት ኣመታት ከፋ የአለመረጋጋት ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ ተደጋግሞ ስነገገር ቆይቷል፡፡ እንደ አከባቢው ነዋሪዎች አሁን አሁን ደግሞ ወረዳው የአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎችን እንደማዋሰኑ በሁለቱም ክልሎች ላለው የጸጥታ ሁኔታ ሰለባ ነው ተብሏል፡፡ የአከባቢው ባለስልጣናት በፊናቸው በአከባቢው ያለው የሰላም እጦት ነዋሪዎች ላይ አለመረጋጋት መፍጠሩን በማረጋገጥ ችግሮቹን ለመፍታት እየተሰራ ነው ይላሉ፡፡

ለደህንነታቸው ስባል ስማቸውን ከመግለጽ ተቆጥበው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ ያጋሩት የወረዳው ነዋሪ ወረዳዋ የተለያየ ዓለማ ያላቸው የሁለት ታጣቂ ተፋላሚዎች ፊልሚያ ሜዳ ሆናለች ይላሉ፡፡

“በዚህ ወረዳችን ሁለት ጉልበተኞች በዚም በዚህም ሰላማዊ ዜጎችን የመፋለሚያ ምድር እያደረጉ ነው፡፡ እነዚህም የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና ፋኖ ብለው እራሳቸውን የሚጠሩ አካላት ናቸው፡፡፡ መንግስት ደግሞ በመሃል አለ፡፡ ወረዳዋ በምራቅ በኩል ከሚያዋስናት መራቤቴ እና ከደቡብ ምዕራብ በኩል ከሚያዋስናት ሂደቡ አቦቴ ወረዳዎች በኩል በሚመጡ የታጠቁ አካላት የጦር አውድማ ነው የሆነችው፡፡ አሁን በቅርቡ የተቃጠለው ከአምስት ሺህ በላይ የገበሬ ቤቶች ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ አሁን ዛሬ እንኳ የወረዳው አስተዳደርን ጨምሮ የጸጥታ አካላት በውይይት ላይ ናቸው” ብለዋል፡፡

የመውጫ መግቢያ መንገድ ችግር

አስተያየት ሰጪው በዚህ ዓመት በተለይ ለደራ ነዋሪዎች ከዚሁ ከጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ወጥቶ መግባት ፈተና መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በፊት ይጠቀሙበት የነበረው ሁለት መውጫ መንገዶች በግጭት ምክንያት መዘጋቱም በብርቱ እንደፈተናቸው ነው ያስረዱት፡፡

በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ የከፋዉ ግጭት

“ከዚህ በፊት በዚህ በሂደቡ አቦቴ እና በምስራቅ ደግሞ በመራቤቴ አቋርጠን ነበር ወደ አዲስ አበባ የምናመራው፡፡ በዚሁ የጸጥታ ችግር እነዚህ መንገዶች ከተዘጉ ሁለት ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ ከዚህ የተነሳም ወላድ ህክምና ማግኘት ፈተና ሆኗል፡፡ መድሃኒት ማግኘትም ከባድ ነው፡፡ መኪና በሳምንታት አሊያም በወር አንዴ ታጅቦ ብተላለፍ ነው፡፡ እውነት ለመናገር ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነን፡፡  ከአገሪቱ መዲና 200 ግድም ኪ.ሜ ብቻ ርቀን ልክ የአገሪቱ ጠረፍ ላይ እንዳለ ሰው ነው እየተቸገርን ያለነው፡፡ በአራት አቅጣጫ ተዘግቶብን በዚህ ዘመን ይፈጠራል የማንለውን ችግር እያየን ነው” ሲሉም ችግራቸውን አስረድተዋል፡፡

የነዋሪዎች መሻት

የወረዳው ነዋሪዎች በወረዳው ለተፈጠረው የጸጥታ አጣብቂኝ አስቸኳይ እልባትም ይሻሉ፡፡ ችግሩም እልባት ካላገኘ ሰው የሚበላውን እስከማጣት ሊያደርሰው የሚችለውን አደጋ ልጋፈጥም እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

መንዲዳ
በደራ ወረዳ ሰላማዊ ሰዎች በታጣቂዎች እንደሚታገቱ ሲከፋም እንደሚገደሉ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል Seyoum Getu/DW

"አለቅን በሁለት ዱላ"

በወረዳው በዚህም በዚያም አስከፊ ሆኗል የተባለው የእገታ እና አፈና ጉዳዮች ሌላው የወረዳውን ነዋሪ ያሰለቸው ጉዳይ ነው፡፡ “አንዱ የታጣቂ ቡድን በሌላው ህዝብ ላይ እያነጣጠረ ያፍናል በሺዎች ገንዘብ ጠይቃል ከዚያን ይገድላል፡፡ በቅርቡ እንኳ የተፈጠረውን ባነሳልህ ከፊቼ ተነስተው በመንገድ ብልሽ ምክንያት ስንት ቀን መንገድ ላይ የተጉላሉትን 9 ሰዎች ታጣቂዎች ገንዘብ ተይቀውባቸው በመጨረሻም ረሽኖአቸዋል፡፡ በታሪክ ያልሰማነው ነው እየሆነ ያለው” ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የደራ ወረዳ ጥቃት

አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከፍያለው አደሬ ነዋሪዎቹ ተማረንበታል ያሉትን የጸጥታው ፈተና መኖሩን አልሸሸጉም፡፡ አስተያየታቸው ስያጋሩም በተለይም በኤጄሬ እና በዓለም ከተማ በኩል ያሉ ሁለት አማራጭ መንገዶች አንድም የጸጥታ ችግር ሁለትም የመንገዶች መበላሸት ችግር መኖሩን አብራርተዋል፡፡

“ባለው የጸጥታ ችግር ባለመጠገናቸው መንገዶች አገለግሎት ላይ ችግር የፈጠረበት አግባብ አለ፡፡ መንገዱ ወደ አስፓልት እንዲያድግ ኮንትራት ተሰጥቷል፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን ጥገና ይደረጋል፡፡ ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ግን በጸጥታ አካላት ድጋፍ ሰው ወጥቶ እንዲገባ እየጣርን ነው” ብለዋል፡፡

በሰሜን ሸዋ ደራ የተከሰተው ግጭት

ነዋሪዎች እንደሚሉት በጸጥታው ችግር ምክንያት ያልታረሰ ሰፊ መሬት ብኖርም የታረሰውንም ምርት ለመሰብሰብ ስጋቱ ሰፊ ነው፡፡ የወረዳው አስተዳዳሪም በጸትታው ችግር ጾም ያደረ ማሳ መኖሩን አላስተባበሉም፡፡

ይሁንና አስተዳዳሪው “ሰላም በሌለበት የሚሳካ አንዳችም ነገር አይኖርም፡፡ ያንን ለመለወጥ ነው እየሰራን ያለነው፡፡ አሁን ያለውን የጸጥታውን ችግር መለወጥ የምቻለው በመጠየቅ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ሰው የመንግስትን መዋቅር እየደገፈ ሰላምን ለማረጋገጥ አስተዋጽ በማበርከት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ልዩነት እንኳ ብኖር ህዝቡ ለጋራ ሰላም መተባበር አለበት” ነው ያሉት፡፡

ሥዩም ጌቱ

እሸቴ በቀለ