1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

የደራ ወረዳው አሰቃቂ ግድያና አላባራ ያለው ውስብስብ ቀውስ

ረቡዕ፣ ኅዳር 11 2017

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ላለፉት ጥቂት ዓመታት የተወሳሰበው የጸጥታ ችግር አሁን አሁን ወደ አስከፊ ደረጃ የተሸጋገረ መስሏል።

https://p.dw.com/p/4nDFv
ሰሜን ሸዋ
ሰሜን ሸዋ ኦሮሚያ ክልል ፎቶ ከማኅደር ምስል Seyoum Getu/DW

የደራ ወረዳው አሰቃቂ ግድያና አላባራ ያለው ውስብስብ ቀውስ

 

ከሰሞኑ በታጣቂዎች የተፈጸመ የተባለውና አንድ ግለሰብ በጭካኔ በቢላ እንዲታረድ ሲደረግ የታየው ተንቀሳቃሽ ምስል ከትናንት ጀምሮ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት ተጋርቶ በመታየቱ በማኅበረሰቡ ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል። በወረዳው የሚፈጸሙ የተባሉ ተደጋጋሚ ዘግናኝ ግድያዎቹ እና የንብረት ውድመት ማኅበረሰቡ ከቀየው ሸሽቶ ወደ ጫካ ተሰድዶ እንዲኖርም እንዳስገደዱት ተነግሯል።

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳሰላልኩላ ከተማ የተፈጸመ የተባለውና እጅጉን አሰቃቂ ተንቀሳቃሽ ምስል የታጠቁ ሰዎች አንድን ግለሰብ በአጸያፊ ስድም እየገሰጹት እንዲታረድ ስፈርዱበት ይታያል። ከትናንት ጀምሮ ዛሬ ውሎውን በስፋት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተጋራው ይህ ተንቀሳቃሽ ምስል ማኅበረሰቡን ክፉኛ አስቆጥቷል።

የአሰቃቂ ግድያ መፈጸም ላይ የማህበረሰብ ምላሽ

አስተያየታቸውን የሰጡን ነገር ግን ለደህንነታቸው ሲባል ስሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ መሰል ዘግናኝ ግድያዎች በተደጋጋሚ ስከሰቱ ቢቆዩም የአሁኑ ተንቀሳቃሽ ምስል ልወጣ የቻለው በአንድ መንገደኛ ምክንያት ነው ይላሉ። «አሁን ምስሉ በስፋት የተጋራው ድርጊት የወጣው በአንድ መንገደኛ ነው። ቤተሰቦቹንም አነጋግሯቸው ነበር። ለዘግናኙ ግድያ የተዳረገውን ወጣት የወሰዱት ከጅሩዳዳ ቀበሌ ሲሆን ድርጊቱን የፈጸሙት ደግሞ በሰላል ኩላ ነው። ይህቺ የሰላል ኩላ ከተማ በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ነው የምትገኘው። የኔ ቤተሰቦች ከዚህ አካባቢ ሸሽተው በጫካ እየኖሩ በዚያው ያገኙትን እያበሰሉ ሕይወታቸውን ለማቆየት ስጥሩ ነበር። አሁን ገና አንድ ሳምንታቸው ነው ወደ ቤት ከተመለሱ» ብለዋል።

ወደ ጫካ ተሰዶ ለመኖር የተገደደ ሕዝብ

ሌላም የአካባቢው ነዋሪ አስተያየታቸው ቀጠሉ፤«በፋኖ ታጣቂች ምክንያት በተለይም ከሁለት ቀበሌያት ጅሩዳዳ እና ወሬገብሮ የተፈናቀሉ አሁንም ድረስ መኖሪያቸውን ጫካ ያደረጉ አሉ። በተለይ ሴቶችና ሕጻናት ሮጠው ማምለጥ ስለማይችሉ እነሱን በጫካ እያስጠለሉ ወንዶቹ ሕይወታቸውን የሚያቆየውን ከመንደር እየፈለጉ ይመለሳሉ። የስታቲስቲክስ መረጃ እንደሚያሳየው በእነዚያ ቀበሌያት ከ5,600 በላይ ነዋሪዎች አሉ። የፋኖ ታጣቂዎች በሚያዋስኗቸው አካባቢ ያሉ ከዚህ ቁጥር 60 በመቶ ግድም የሚሆኑት የሚፈጸሙትን አሰቃቂ ግድያዎች በመሸሽ እንዲሁም ቤታቸው በተደጋጋሚ ስለተቃጠለባቸው በዚያው በረሃ በሜዳ መቆየትን ምርጫው ያደረጉ ናቸው» ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ስለሰቆቃው የመንግሥት ምላሽ

በወረዳው «ሁለት ጽንፈኛ ታጣቂ ቡድኖች ይንቀሳቀሳሉ» በማለት አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፤ «ሁለቱም ቡድኖች ንፁሐን ላይ ግድያ ይፈጽማሉ» ብለዋል።

ዘላቂ እልባት መናፈቅ

በዚህ አካባቢ መንግሥት የጸጥታ ኃይሎችን አሰማርቶ ሰላም ለማስከበር ጥረት በሚያደርግበት ወቅት አካባቢው በአስተዳደር ወሰን ላይ የሚገኝ በመሆኑ ሁለቱ ታጣቂ ቡድኖች በተመሳሳይ ሰዓት ጥቃት እየፈጸሙ አስቸጋሪ ሁኔታን ይፈጥራሉ ብለዋል። የጥቃቶች አለመቆም ሳይሸሽጉም ማኅበረሰቡ የናፈቀውን ሰላም ለማምጣት መንግሥት በሁለት አማራጭ እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ