1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደሞዝ ይከፈለን ጥያቄ በዎላይታ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 8 2016

በዎላይታ ዞን በየጊዜው የሚነሳው የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ይከፈለን ጥያቄ አሁንም መቋጫ ያገኘ አይመስልም ፡፡ በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ሠራተኞች ከሰላማዊ ሰልፍ እስከ ሥራ ማቆም አድማ በመምታት ጥያቄያቸውን ቢያቀርቡም ዛሬም መፍትሄ አለማግኘታቸውን ይናገራሉ ፡፡

https://p.dw.com/p/4jSUt
ወላይታ ሶዶ
ወላይታ ሶዶምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የደሞዝ ይከፈለን ጥያቄ በዎላይታ

አንዶንዶቹ የሦስት ወራት የተቀሩት ደግሞ እስከ ሁለት ወራት ደሞዝ አለማግኘታቸው የጠቀሱት ሠራተኞች “ ለሌሎች ደግሞ የደሞዛቸውን መጠን በመቶኛ በማስላት አነስተኛ ክፍያ ለመሰጠት ተሞክሯል ፡፡ አብዛኞቻችን ግን ወረዳው ደሞዝ ሊከፍለን አልቻለም ፡፡  በዚህም የተነሳ ከነቤተሰቦቻችን ለከፋ የኑሮ ችግር ተዳርገናል ” ብለዋል ፡፡

የዋና አስተዳዳሪው እገታ

በዎላይታ ዞን የደሞዝ ይከፈለን ጥያቄ ለሚያቀረቡ የመንግሥት ሠራተኞች በየአካባቢው የሚገኙ መስተዳድሮች ምላሽ አለመስጠታቸው ሠራተኛው ሆድ እንዲብሰው ምክንያት ሆኗል ይላሉ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የዞኑ ነዋሪዎች ፡፡ ከዚህ መነሻም ይመስላል በዞኑ የሆቢቻ ወረዳ ሠራተኞች ትናንት የወረዳውን አስተዳደር ጽህፈት ቤት መውረራቸው ፣ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪን ለሰዓታት ማገታቸው የተሰማው ፡፡

በወረዳው የመንግሥት ሠራተኛ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ጳውሎስ አጋ ቅሬታ ለማቅረብ ወደ ወረዳው አስተዳደር ፅህፈት ቤት ካቀኑት መካከል አንዱ መሆናቸውን ይናገራሉ ፡፡ አብዛኛው ሠራተኛ ምላሽ በማጣቱ በቁጣ ሥሜት ውስጥ እንደነበር የጠቀሱት አቶ ጳውሎስ “ ተሰባስበው ወደ ወረዳው አስተዳደር ጽህፈት ቤት ያመራው ሠራተኛ በሺዎች የሚቆጠር ነው ፡፡

የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ይከፈለን ጥያቄ ሰዎች ተሰልፈው
የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ይከፈለን ጥያቄ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ሠራተኛው ከጽህፈት ቤት ግቢ በመውጣት ላይ የነበሩትን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ በማግኘት ደሞዝ ይከፈለን የሚል ጥያቄ አቀረበ ፡፡ ዋና አስተዳዳሪው  “መንግሥት ሳይልክልኝ ከየት አምጥቼ ልክፈላችሁ “ የሚል ምላሽ ሲሰጡ ሠራተኛው ሥሜት ውስጥ ገባ ፡፡

በመቀጠል ዋና አስተዳዳሪውን ከተሽከርካሪያቸው በማውረድና ወደ ቢሯቸው በመመለስ ደሞዛችንን ሳትከፍሉ ከዚህ መውጣት አትችሉም በሚል እንዳይወጡ ዙሪያውን ከቦ መጠበቅ ጀመረ ፡፡ በመጨረሻ ከምሽቱ 2 ሰዓት አካባቢ በሁለት ተሽከርካሪዎች የመጡ ፖሊሶች ሠራተኛውን በመበተን ዋና አስተዳዳሪውን ወደ ዎላይታ ሶዶ ከተማ ይዘዋቸው ሄዱ “ ብለዋል ፡፡

ራሳችሁን ቻሉ

ዶቼ ቬለ በሠራተኞቹ የደሞዝ ጥያቄ ዙሪያ የዞንና የክልል የሥራ ሃላፊዎችን አስተያየት ለማካተት ጥረት ቢያደርግም ሊሳካ አልቻለም ፡፡ በዎላይታ ዞን የሆቢቻ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ምላሽ ለመስጠት በሰጡት የቀጠሮ ሰዓት መሠረት ቢደወልላቸውም የእጅ ሥልካቸው ዝግ በመሆኑ ማግኘት አልተቻለም ፡፡ ያም ሆኖ በችግር ላይ እንደሚገኙ የሚናገሩት የወረዳው ሠራተኞች “ አሁንም ለጥያቄያችን ምላሽ ይሰጠን” በማለት  እየወተወቱ ይገኛሉ ፡፡

የቀጠለው የደሞዝ ጥያቄ በዎላይታ ዞን

ከተመሠረተ ከአንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል  በተለይ በዎላይታ ዞን የሠራተኞች የደሞዝ ጥያቄ ከክልል እስከ ተወካዮች ምክር ቤት በአጀንዳነት ያልተነሰባት ጊዜ የለም ፡፡ በቅርቡ  ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ያደረጉት  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ደሞዝ መክፍል የማይችሉ ክልሎች አሉ በሚል በምክር ቤት አባላት እንደተነሳላቸው በመጥቀስ  “ ይህ የአኔ ሥራ አይደለም ፡፡ አንድ ክልል የራሱን ገቢ አሻሻሎ ፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀመር የሚያገኘውን ሀብት ወስዶ  ደሞዝ መክፈልና ልማት ማምጣት የእሱ ሥራ ነው “ ብለዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ልደት አበበ

ኂሩት መለሰ