የደም ልገሳ ሳምንት | ጤና እና አካባቢ | DW | 18.06.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የደም ልገሳ ሳምንት

«ሕይወት የሆነውን ደም በመስጠት ሕይወት ያድኑ!»  ሰዎች ደም መለገሥን እንዲለማመዱ የሚቀሰቅስ ዓለም አቀፍነት ይዘት ያለው መሪ ቃል ነው። በየዓመቱ ደም ለጋሾች የሚመሰገኑበት ሳምንት በጎርጎሪዮሳዊው የዘመን ቀመር ሰኔ 14 ላይ ሲታሰብ 152ኛ ዓመቱን ያዘ። በኢትዮጵያ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:54

«ለጋሾች፤ ደም መለገሥ የመንፈስ ርካታን ይሰጣል ይላሉ»

«ጤናማ ደም ለሁሉም» ይላል የዘንድሮው የዓለም የደም ልገሳ ቀን መሪ ቃል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕለቱ ሩዋንዳ ላይ ነው የታሰበው። ይህ ዕለት በዓለም የሚከበረውም በነፃ ደም በመለገሥ ሕይወት ለሚያተርፉ ወገኖች ምሥጋና በማቅረብ ነው። ኢትዮጵያ ከሰኔ ሰባት ቀን 2011ዓ,ም ጀምሮ ባሉት ቀናት የደም ልገሣ ቀንን እያከበረች መሆኗን የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር፤ ዶክተር ሔለና ኃይሉ ገልጸውልናል። በ2004 ዓ,ም የደም ባንክ አገልግሎት አዲስ አበባ ላይ ከተቋቋመ ወዲህም በመላ ሀገሪቱ አሁን 42 ባንኮች መደራጀታቸውንም አስረድተውናል። የደም ልገሣው ሂደት በምን መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝም እንዲህ ያስረዳሉ።

«አሁን እንግዲህ ደም እየሰበሰብን ያለነው ከበጎ ፈቃደኞች ነው። በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሽ በፈቃዱ ደም በሚሰጠን ጊዜ ያንን ነው ተጠቅመን ለታካሚዎቻችን የምንሰጠው። ይሄ እንግዲህ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ2004  ጀምሮ ነው እንደዚህ በበጎ ፈቃደኝነት ላይ ያተኮረ የደም ማሰባሰብ ሥራ እየሠራን ያለነው።»

Weltblutspendetag Aktivität Äthiopien Addis Abeba PM Abiy Ahmed

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢል አህመድ በደም ልገሣ ላይ

ደም ልገሣውም ሆነ ማሰባሰቡ ፈቃደኛ ሲገኝ መሆኑ እሙን ነው፤ ደም ለመለገሥ ኅብረተሰቡ ምን ያህል ዝግጁ ነው?  ዶክተር ሔለና እንደሚሉት ግንዛቤው ገና ቢሆንም በያዝነው ዓመት እስካለንበት ወር ድረስ ያለው ሲታይ  ከሚያስፈልገው የደም መጠን ከዘጠና በመቶ በላይ ከለጋሾች ማሰባሰብ ተችሏል።

«በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሽ ለማግኘት ብዙ የትምህርት እና ቅስቀሳ ሥራ ያስፈልጋል። ኅብረተሰባችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕውቀቱ ደም መለገሥ ላይ እየተሻሻl ቢመጣም ከሚፈለገው ወይም ደግሞ የዓለም ጤና ድርጅት ከሚያስቀምጠው ደረጃ አንጻር ስናየው አሁንም ብዙ ይቀረናል።»

የሀኪም ቤቶች መስፋፋት እና በተለይም ከወሊድ እንዲሁም ካንሰርን ከመሳሰሉ ሕክምናዎች እና ከአደጋዎች ጋር በተገናኘ ጤናማ ደም የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ቁጥር መበራከት የደም አቅርቦት ላይ ጫና ማሳደሩ እየታየ መሆኑን ዶክተር ሔለና ኃይሉ ዘርዝረዋል። ሰዎች በነፃ ደም መለገሥ እንዲለምዱ ቅስቀሳ እየተደረገ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ሔለና በተለይ ታዋቂ እና በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ዜጎች ለምሳሌነት እየተጠቀሙ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዶክተር ሔለና እንደገለፁልን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነባለቤታቸው ደም የለገሡት በራሳቸው ጥያቄ በፈቃደኝነት ነው። እሳቸውን በመከተልም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚሠሩ ባለሙያዎች፤ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ አርቲስቶች እንዲሁም ኳስ ተጫዋቾችም ደም መለገሣቸውንም ጠቁመዋል።

ክብደቱ ከ45 ኪሎ ያላነሰ ሰውነቱን በአካላዊ እንቅስቃሴ በወጉ የሚጠብቅ ሰው ደም መለገሥ ይችላል ባለሙያዋ እንደገለፁልን። እግረመንገዱን ደግሞ የደም አይነቱ ከየትኛው ጎራ እንደሆነ፣ ያላወቀው ህመም ይዞት እንደሆነም በዚህ አጋጣሚ በነፃ ሊመረመር እና ጤንነቱንም እንዴት መጠበቅ እንደሚኖርበት ሊማር እንደሚችልም ዶክተር ሔለና ነግረውናል።

ደም መለገሥ የመንፈስ እንደሚያረካ 73 ጊዜ ደም በመለገሥ ልምድ ያካበቱት ሲስተር አሰጋሽ ጎሳኔ ገልጸውልኛል። የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ባልደረባ የሆኑት ሲስተር አሰጋሽ ሰዎች ምንጊዜም ደም አጥሎ ሊሞት ያለ ሰውን ማሰብ እንደሚገባቸውም ያሳስባሉ።  እሳቸውን ደም ለመገሥ ያነሳሳቸው አንድ አጋጣሚ ነው። የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ሰሎሞን ሙጬም ከሁለት ዓመታት ወዲህ ደም በመለገሥ ላይ መሆኑን ገልፆልኛል።

የዛሬ 10 ዓመት የቤተሰብ ምትክ በሚለው የደም ልገሣ 24 ሺህ ሰዎች በዓመት ደም ይሰጡ እንደነበር ነው የብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የገለፁልን። ዘንድሮ የያዝነው ዓመት ባይጠናቀቀም 204 ሺህ ገደማ በጎ ፈቃደኞች ደም መለገሣቸው ተመዝግቧል። ቋሚ ደም ለጋሾች በዓመት 3 ጊዜ እና ከዚያ በላይ መስጠት የሚችሉ ናቸው። አንድ ሰውም በየሦስት ወሩ ደም መለገሥ ይችላል።

ከዚህም ሌላ እስከ ዛሬ ደም ይቀዳበት የነበረውን ስልት የሚቀይር ዘመናዊ እና አስፈላጊውን የደም ክፍል መርጦ ሊወስድ የሚችል አዲስ መሣሪያ ኢትዮጵያ ማስገባቷን በመግለፅ ወደፊት ይህ ሥራ ላይ ሊውል እንደሚችልም ገልጸውልናል። ይህን መሣሪያ መጠቀም ሲጀመር ደግሞ የግድ ሦስት ወር መጠበቅ ላያስፈልግ ይችላል፤ የተወሰደው የደም ክፍል የሚተካበት ጊዜ ስለሚታወቅ በዚያ የሚያሰላ ይሆናል። ከለጋሾች የሚወሰደው ደም ለአገልግሎት ከመዋሉ አስቀድሞ ምርመራ የሚደረግለት ሲሆን የቆይታ ጊዜውም ከአምስት ቀን እስከ አንድ ዓመት ሊዘልቅ እንደሚችልም አስረድተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

 

 

 

Audios and videos on the topic