የደሐ ሐገራት ሕዝብ ችግሮችና የልማት እርዳ | ፖለቲካ | DW | 01.10.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ፖለቲካ

የደሐ ሐገራት ሕዝብ ችግሮችና የልማት እርዳ

እንደሚገመተዉ በየደቂቃዉ አንዲት እናት አንድም በርግዝና አለያም በወሊድ መቃወስ ምክንያት ትሞታለች።ይሕ ማለት በእርግዝናና በወሊድ መቃወስ ምክንያት ብቻ በየአመቱ ከ500 ሺሕ በላይ፥ በአንድ ትዉልድ ደግሞ ከአስር ሚሊዮን በላይ ሴቶች ይሞታሉ

default

የተመድ ጽ.ቤት

የበለፀገዉ አለም ለደሐ-ሐገራት መርዳት የሚገባዉን ያሕል አይደም፥ የሚረዳዉም ለችግረኛዉ ሕዝብ በአግባቡ አይደርስም ሲሉ ሁለት ግብረ-ሠናይ ድርጅቶች ወቀሱ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የጀርመን የሥነ-ሕዝብ ተቋማት በጋራ እንደሚሉት በተለይ የአዉሮጳ ሕብረት የሚሰጠዉ የልማት እርዳታ በቂ አይደለም።ከሚሰጠዉም መሐል መረዳት ለሚገባዉ ችግረኛ ሕዝብ በአግባቡ አይደርስም።በሁለቱ ድርጅቶች መግለጫ መሠረት ርዳታዉ መጠንና አጠቃቀሙ እስካሁን ባለዉ መንገድ ከቀጠለ «የአማአቱ ግብ» የተሰኘዉ የልማት ዕቅድ ለዉጤት አይበቃም።ክርስቶፍ ሐሰልባሕ የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።


የተባበሩት መንግሥታት የሥነ-ሕዝብ ድርጅትና የጀርመኑ አለም አቀፍ የሥነ-ሕዝብ ተቋም ወቀሳ ቅሬታቸዉን ለአዉሮጳ ምክር ቤት አባላት በግልፅ ነዉ-የነገሩት።በቅሬታ ያሳረገ ጥናታቸዉ መሠረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድሕነት፥ ማይምነትን፥ በሽታን ለመቀነስ ለአስራ-አምስት አመት የነደፈዉ እቅድ ግማሽ ጉዞ ነዉ።

የአለም መሪዎች ከስምት አመት በፊት ያፀደቁት «የአማአቱ ግብ» የተሰኘዉ እቅድ ዛሬ ባጋማሽ ዘመኑ ሲገመገም በየመስኩ በተያዘለት ጊዜ ለዉጤት ከመብቃቱ ደስታ ይልቅ በዕቅድ የመቅረቱ ሥጋት ነዉ የደመቀዉ።ዕቅዱ ግቡን ይስታል የሚለዉ-ሥጋት ምንጭ ሁለት ነዉ።የበለፀገዉ አለም መንግሥታት ገንዘብ ለማዋጣት፥ ድሆቹ ደግሞ ተገቢ መርሕ ለመንደፍ የገቡትን ቃል አለማክበራቸዉ።


ሁለቱ ድርጅቶች የአማአቱን ግብ አፈፃፀም እንዴትነት፥ የልማት እርዳታዉን መጠን-ሥንትነት፥ የሚደርስበትን ሥፍራ-የትነት ሲያስተነትኑ እንደ ስም-ምግባራቸዉ የሥነ- ሕዝብ እና የጤናዉን መስክ፥ ከተቀረዉ አለም ይብስ አዉሮጳን ነዉ-ያተኩሩባቸዉ።የአለም አቀፉ ድርጅት ተጠሪ ሲትስከ ሽቴንከር ለአዉሮጳ ሕብረት ፓርላማ አባላት እንደነገሩት አይኗን ባይኗ ለማየት፥ ኖራ-ልጅ-ዉላጅዋን ለማኖር እንደጓጓች የምትሞዉ እናት ቁጥር አስደንጋጭ ነዉ።«እንደሚገመተዉ በየደቂቃዉ አንዲት እናት አንድም በርግዝና አለያም በወሊድ መቃወስ ምክንያት ትሞታለች።ይሕ ማለት በእርግዝናና በወሊድ መቃወስ ምክንያት ብቻ በየአመቱ ከ500 ሺሕ በላይ፥ በአንድ ትዉልድ ደግሞ ከአስር ሚሊዮን በላይ ሴቶች ይሞታሉ ማለት ነዉ።ከሟቾቹ አብዛኞቹ ሁሉም ማለት ይቻላል፥-99ኝ ከመቶዉ በማደግ ላይ ያሉ ሐገራት ዜጎች ናቸዉ።»

ኢትዮጵያ አንዷ አብነት ናት።ከወላድ ኢትዮጵያዉን ሴቶች ዘመናዊዉን የወሊድ መከላከያ የሚወስዱት ሴቶች ከመቶ ስድስት ብቻ ናቸዉ።በቅጡ የሰለጠነ-ሐኪምና አዋላጅ የምታዉቀዉ ደግሞ ከአስሩ-አንድ ወላድ ናት።

ወላድ ሴቶች ተገቢዉን ሕክምና አለማግኘታቸዉን፥ በዚሁ ሰበብም ማለቃቸዉን ማየት ሽቴንከር እንደሚሉት ኢሰብአዊነት ነዉ።ምጣኔ-ሐብታዊ ጥፋቱ ደግሞ ድሆቹን ሐገራት ይብስ የሚያደኸይ ነዉ።የአማአቱ ግብ፥ ሰብአዊ ጥፋቱን ምጣኔ ሐብታዊ ድቀቱን ማስቀረት ቢከብድ ለመቀነስ ያለመ ነዉ።አለማዉ-ግቡን መምታት አለመምታቱ የሚወነዉ የአዉሮጳ ሕብረት የመማክርት መድረክ ፀሐፊ ኔይል ዳታ እንደሚሉት በአብዛኛዉ በአዉሮጶች ነዉ።
ድምፅ

«አለም ለልማት ርዳታ ከሚያወጣዉ ስልሳ-አራት ከመቶዉን የሰጡት የአዉሮጳ ሕብረት፥ ይሕ ማለት የአዉሮጳ ኮሚሽንና ሃያ-ሰባቱ አባል መንግሥታት ናቸዉ።የሕብረቱ አባል ያልሆኑ እንደ ኖርዌና ሲዊዘላንድን የመሳሰሉ ሐገራትን ብንጨምር ደግሞ፥ የምንሰጠዉ የልማት ርዳታ መላዉ አለም ከሚሰጠዉ ሰባ ከመቶዉን ይይዛል።ሥለዚሕ የአማአቱ ግብ መሳካት አለመሳካቱ የሚበየነዉ በአዉሮጳ ርዕሠ-ከተሞች በሚወሰደዉ እርምጃ ነዉ።»

ሁለቱ ድርጅቶች እርዳታዉ አነሰ ብቻ አይደለም የሚሉት።ያነሰዉንም ርዳታ ቢሆን የአዉሮጳ መንግሥታት መረዳት ለሚገባዉ ደሐ ሕዝብ ከማድረስ ይልቅ ለየመንግሥታቱና በየመንስታቱ በኩል መስጠታቸዉ ተገቢ አይደለም።በድርጅቶቹ መግለጫ መሰረት ለጋሽ መንግሥታት በተለይ በልማት ፕሮጀክቶች ፈንታ የመንግሥታትን በጀት መደጎማቸዉ የርዳታዉ አለማ-የሳተ፥ ፋይዳዉን ያሳነሰ ነዉ።

የአዉሮጳ ሕብረት የምክር ቤት እንደራሴ ወይዘሮ አነ ፋን ላንከር የሁለቱን ድርጅቶች ወቀሳ ከመቀበልም በላይ በአብነት ያጠናክሩታል።
ድምፅ

«በነዚሕ ሐገራት አንዳዴ፥ እንዲያዉምእ በጣም ብዙ ጊዜ የምናየዉ ትልቅ ችግር የሐገር ባለቤት ማለት፥ የመንግሥት ባለቤት ማለት ነዉ።መንግሥት ሲባል ደግሞ ብዙ ጊዜ (የልማት ርዳታዉን) የሚቆጣጠረዉ የገንዘብ ሚንስቴር እንጂ የጤና፥ የትምሕርት ሚንስቴር ፓርላማ ወይም የሲቢል ማሕበረሰብ አይደሉም።»

የሁለቱ ድርጅቶች ተወካዮችና ሐሳባችዉን የሚጋሩት የአዉሮጳ ምክር ቤት አባላት እንደሚሉት የአማአቱ ግብ ያዘም-ሳተ ለአዳጊ ሐገራት መንግሥታት የሚደረገዉ የበጀት ድጎማ መደረግ ያለበት ተረጂዎቹ መንግሥታት ገንዘቡን ለሕዝብ ልማት ካዋሉት ብቻ ነዉ።