የደህንነት ስጋት በኬንያ | አፍሪቃ | DW | 01.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የደህንነት ስጋት በኬንያ

ኬንያ በአሁኑ ወቅት የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን፤ እያደረሰ ያለዉ የሽብር ጥቃት በአፍሪቃ ቀንድ ያለዉን ተፅዕኖ ለማሳየት ምስክር ነች። «ታዋዊዛ» የተባለዉ የምስራቅ አፍሪቃ የጥናት ድርጅት እንዳመለከተዉ በኬንያና በሶማሌ የድንበር አቅራቢያ ቦታዎች ባለፈዉ ዓመት ጥቅምት ወር ብቻ ከ50 በላይ የፖሊስ መኮንኖች በአልሸባብ መገደላቸዉን አመልክቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:19

የደህንነት ስጋት በኬንያ

በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ የሚገኘዉ የዌስት ጌት የገበያ አዳራሽ ወከባ የበዛበት ነዉ።ሸቀጦችን በቅናሽ ለመግዛት የሚፈልጉ ሸማቾች የቀንስ አትቀንስ ክርክር፣ በተጠራዉ ዋጋ ገዝተዉ የከስዓት በኋላዉን የትራፊክ መጨናነቅ ለማምለጥ በሚጣደፉ ሰዎች፤ህጻናት ልጆቻቸዉን ለማስተኛት በመንሸራተቻ በሚገፉ ወላጆች፣ በብረታብረት ድምጾች በአጠቃላይ ቦታዉ በድምጾችና በእንቅስቃሴዎች የተሞላ ነዉ። በአዳራሹ ግድግዳ ጠርዝ ላይ የሚያስተጋባዉ የደህንነት ፍተሻ መሳሪያ ድምጽ  ለአንዳንዶቹ  ከፍተኛ የደህንነት ጥበቃን የሚያመለክት ሲሆን ለአብዛኛወቹ  የዌስትጌት ሸማቾች ግን ፤የተለዬ ትርጉም አለዉ። ይህ ድምፅ በጎርጎሮሳዉያኑ መስከረም 21 ቀን 2013 የ63 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈዉን የሽብር ጥቃት የሚያስታዉስ ነዉ።

ቀደም ሲል የተጠናከረ ፍተሻና ጥበቃ ያልነበራቸዉ የኬንያ የመገበያያ ቦታወች  አሁን አሁን በገበያ አዳራሾችም ይሁን  በቤተ ክርስቲያናት እንዲሁም የማህበራዊ  ጉዳይ በሚፈፀምባቸዉ ቦታወች የታጠቁና በተጠንቀቅ የሚጠብቁ የፖሊሶች መኮንኖችን ማየት የተለመደ ሆኗል።

በዌስትጌት የገበያ አዳራሽ የዶቼቬለዉ አንድሪዉ ዋሲከ ያነጋገራት ሽላ ንጉኒ የተባለች ሸማች የጥበቃዉ መጠናከር ደህንነት እንዲሰማት አድርጓታል። «በጣም ደስተኛ ነኝ።ምክንያቱም ሰወች የሽብር ጥቃቱን ረስተዉታል።እንደገና ደስተኛ ሆነዋል። እነዚህን ሰዎች መመልከት ደስተኛ ያደርግሃል።ኢኮኖሚያችንም እያንሰራራ ነዉ።»

ጆኒ ኪመኒ የተባሉ የዚሁ የገበያ አዳራሽ ደንበኛ በበኩላቸዉ ኬንያዉያንን ከሽብር ጥቃት ለመጠበቅ የሀገሪቱ መንግስት በርትቶ መስራት አለበት ይላሉ። በዌስትጌት የገበያ አዳራሽ ሲዘዋወሩ ስለ ሽብር ጥቃት የሚያስቡት አልፎ አልፎ ቢሆንም ቀደም ሲል በዚህ አዳራሽ በሽብር ጥቃት የተገደሉ ሰዎችን ግን መርሳት እንዳልቻሉ ይገልጻሉ።

ያም ሆኖ ግን የገበያ አዳራሹ እንደገና መከፈቱና ስራ መጀመሩ ጥሩ ስሜት ፈጥሮላቸዋል። «እንደገና መከፈቱ ለኛ መነቃቃትን ፈጥሮልናል። አዲስ የትግል መንፈስም ሰጥቶናል። አሸባሪዎች የሽብር ጥቃት ሲፈፅሙና ህንፃወችን ሲያወድሙ  ዋናዉ ዓላማቸዉ ሰወች በቦታዉ  የመታሰቢያ መናፈሻወችን እንዲገነቡ ነዉ። እኛ ግን  በዌስትጌት ይህንን እንዲያደርጉ አልፈቀድንላቸዉም።»

ተዋዊዛ የተባለዉ ገለልተኛና ለትርፍ ያልተቋቋመ የምስራቅ አፍሪቃ የጥናት ድርጅት በቅርቡ የኬንያዉያንን በደህንነት ስጋት፣ በፖሊስና በፅንፈኝነት ላይ ያላቸዉን አስተያየት የሚያሳይ ጥናት አዉጥቶ ነበር። በዚህ ዘገባዉ ታዲያ የሀገሪቱ ዜጎች በፍትህ ስርዓቱ ላይ ጥርጣሬ እንዳለቸዉና  በፖሊስ ላይ ያላቸዉ አመኔታም ቢሆን የተለያዬ መሆኑን አመልክቷል።

አርባ ስምንት በመቶ የሚሆነዉ ኬንያዊ በፖሊስ የህዝብ አገልግሎት ስራ« ደስተኛ» ነን ሲሉ 33 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ አለመደሰታቸዉን ይፋ አድርጓል። ድርጅቱ በ47 የኬንያ አስተዳደሮች አካሄድኩት ባለዉ ጥናትም በማህበረሰቡ ዉስጥ ከሃምሳ ኬንያዉያን ለአንዱ ሽብርተኝነት ቀዳሚ  የደህንነት ስጋት ተደርጎ ይታያል። ነገር ግን ድርጅቱ በቀጥታ ጥያቄ ካቀረበላቸዉ አስር ኬንያዉያን ስምንቱ ወደ 78 በመቶ የሚጠጉት ማለት ነዉ፤ አልሸባብ ለሀገሪቱ ዋና የደህንነት ስጋት ነው ብለው ያስባሉ ብሏል። በዚህም የተነሳ በርካታ ኬንያዉያን የሀገሪቱ ሰራዊት በሶማሊያ እንዲቆይ ድጋፋቸዉ እየጨመረ መሆኑ ታይቷል  ሲል ጥናቱ አመልክቷል።

የድርጅቱ ከፍተኛ የፕሮግራም ሀላፊ ቪክቶር ራቲንግ ጥናቱ  የደረሰባቸዉ ተጨማሪ ጉዳዮች መኖራቸዉንም ያብራራሉ። «በሀገሪቱ ዉስጥ የሽብር ጥቃት ዋና ጉዳይ ከመሆኑ በፊት ሰዎች ያለምንም ስጋትና ተጨማሪ ጥንቃቄ ወደፈለጉበትና ቦታና ወደ መገበያያ ቦታዎች  ይሄዱ ነበር። አሁን ወደ ዌስትጌት ብትሄድ ግን የስጋት ደረጃዉ በጣም ከፍተኛ ነዉ። ስለዚህ የኛ ሪፖርት በእርግጠኝነት የሚለዉ በጣም ትልቅ ቁጥር መጠን ያለዉና ወደ 80 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች እስካሁን የአልሸባብ የሽብር ጥቃት ሰለባ እንሆናለን በሚል ስጋት ዉስጥ ይኖራሉ።ነገር ግን በተመሳሳይ ሁኔታ የምናየዉ  ዜጎች የአክራሪ ሀይሉን እንዲቀላቀሉ የሚያደርጋቸዉ ምክንያት ምንድነዉ ብለን በምንጠይቅበት ጊዜ  አብዛኛዉ የሚናገረዉ ስለስራ አጥነት  ነዉ።»

በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ከአልሸባብ የሽብር ጥቃት በተጨማሪ የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች የሀገሬዉን ሰዉም ይሁን የዉጭ ሀገር ጎብኝዎችን ስጋት ላይ ጥሏልም ይላሉ። ስለ ደህንነት ሲወራ ምርጫን ተከትሎ በመንግስትና በተቃዋሚ ፓርቲወች መካከል ተፈጥሮ የነበረዉ ዉዝግብና ግጭትም ሌላዉ ለሀገሪቱ ዜጎች አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ እንደነበር  ተገልጿል። በተለይ የተቃዋሚ ፓርቲወች «ራይላ ኦዲንጋ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ለመሆን በጎርጎሮሳዊው ጥር 31 ቃለ መሃላ ይፈፅማሉ» ብለዉ  በነበረበት ወቅት የህዝቡ ጭንቀት ከፍተኛ ነበር ተብሏል። እናም ሀላፊነት ያለዉ መንግስት ለህዝብ የሚበጀዉን ሊያደርግ ይገባል ሲሉ ቪክቶር ራቲንግ መክረዋል።

«ይህ የደህንነት ስጋት እንደ ሆነ ሁሉ ያለዉ መንግስት በህዝቡ ላይ የሽብር መንፈስ እኒዲነግስ የሚያደርግ ከሆነ ይህ ህገመንግስቱን የሚጥስ በመሆኑ  እርሱን በቁጥጥር ስር መዋል ተገቢ ነዉ።ሀላፊነት ያለዉ መንግስት የዜጎቹን ሞት ለማስቀረት ተገቢ የሆነ ስራ መስራት አለበት።ምክንያቱም ንፁሃን ዜጎችን መጠበቅ የእሱ ስራ ነዉና።»

ፀሐይ ጫኔ

ኂሩት መለሰ
 

Audios and videos on the topic