የዮናታን የጥፋተኝነት ብይንና የአምነስቲ ትችት | አፍሪቃ | DW | 18.05.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የዮናታን የጥፋተኝነት ብይንና የአምነስቲ ትችት

በቀድሞዉ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ በአቶ ዮናታን ተስፋዬ ላይ የተላለፈዉ የጥፋተኝነት ብይን ፍታዊነት የጎደለዉ ነዉ ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለዉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ገለጸ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:08

«ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ይጋፋል»


መንግስትን በሚተቹ ጽሁፎቹ ብቻ ጥፋተኛ መባሉ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚጋፋ መሆኑንም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች  ድርጅቱ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፈዉ  ማክሰኞ ባስቻለዉ ችሎት የቀድሞዉ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬን በተከሰሰበት የሽብርተኝነትን የማበረታታት ወንጀል የጥፋተኛኝነት ዉሳኔ ማሳለፉን አስመልክቶ የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ባወጣዉ ዘገባ እንዳመለከተዉየፍርድ ሂደቱም ሆነ የተላለፈዉ ብይን አግባብነት የለዉም ። 
አሸባሪነትን ማበረታታት በሚለዉ የጸረ ሽብር ህጉ አንቀጽ 7 የተከሰሰዉ አቶ ዮናታን ተስፋዬ መንግስትን በሚተቹ  ጽሁፎች ብቻ ከ10 እስከ20 አመት በሚደርስ እስራት ሊያስቀጣ በሚችል ወንጀል ጥፋተኛ መባሉ ኢፍታዊ ነዉ ሲሉ የድርጅቱ የአፍሪቃ ቀንድ ተመራማሪ አቶ ፍስሃ ተክሌ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።
አቃቤ ህግ ያቀረበዉ ማስረጃ የተወሰነ ሆኖ እያለ  ጉዳዩ ከአንድ አመት በላይ ክርክር ሲደረግበት መቆየቱ በራሱ ሂደቱም የተራዘመ መሆኑን ያሳያል ያሉት ተመራማሪዉ፣ ያም ሆኖ የተሰጠዉ ብይን የጸረ ሽብር ህጉ ሰወች ሃሳባቸዉን በነጻነት እንዳይገልጹ ማድረግ ላይ እየዋለ መሆኑን ያሳየ ነዉ ሲሉ አስረድተዋል።
በጸረ ሽብር ህጉ ተከሶ ሲቀጣ ዮናታን የመጀመሪያዉ አይደለም የሚሉት አቶ ፍስሃ ሰወች በሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸዉን እንዲገልጹ እድል የማይሰጥ  በመሆኑ የሀገሪቱ መንግስት የህዝቦችን ሰብአዊ መብት ከማክበር አንጻር ህጉን መንግስትን የሚተቹና የተለዬ ሃሳብ የሚያራምዱ ሰወችን ለማሰር ከማዋል መቆጠብ አለበት ሲሉ ተመራማሪዉ አሳስበዋል። 
ለህዝብና ለሀገር ጥቅም ሲባልም የጸረ ሽብር ህጉን ከዓለም አቀፍ ህጎችና አተገባበሮች ጋር በሚጣጣም መልኩ ክለሳ ሊካሄድበት ይገባል ብለዋል።የዓለም አቀፉ ህብረተሰብም የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ትኩረት ሰጥቶ እንዲከታተል የድርጅቱ ዘገባ  ጨምሮ አመልክቷል።

ፀሐይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ

  
   

Audios and videos on the topic