የዮናታን ተስፋዬ ፍርድ እና ዘመቻ ለቆሼ ተጎጂዎች | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 19.05.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የዮናታን ተስፋዬ ፍርድ እና ዘመቻ ለቆሼ ተጎጂዎች

እንዳለፉት ሳምንታት ሁሉ በዚህ ሳምንትም የሁለቱ ቴዎድሮሶች (የቴዎድሮስ ካሳሁንና የቴድሮስ አድሐኖም) ጉዳይ የበርካታ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎችን ቀልብ ስቧል፡፡ የሁለቱም ደጋፊዎቻቸው እና ተቺዎቻቸው በሁለት ጎራ ተከፍለው ሀሳቦቻቸውን ሲያቀርቡ፣ ሲከራከሩ፣ ባስ ሲልም ክፉ እና ደግ ሲመላለሱ ሰንብተዋል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:57

ለሁለቱ ቴዎድሮሶች ድጋፍ እና ትችት ሲሰጥ ሰንብቷል

የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ቴድሮስ አድሐኖም ለዓለም የጤና ድርጅት (በምህጻሩ WHO) ኃላፊነት ቦታ እንደሚወዳደሩ በይፋ ካሳወቁ አንስቶ በኢትዮጵያውያን የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎች ዘንድ የተጀመረው የድጋፍ እና የተቃውሞ ክርክር እንደቀጠለ ነው፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ “የኃላፊነት ቦታው ይገባቸዋል” ለሚሉቱ ጸሀፌ-ተውኔቱ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ በፌስቡክ ገጹ ረቡዕ ዕለት ያጋራው ጹሁፍ ማሳያ ነው፡፡ ቴዎድሮስ ስለሞክሼው የቀድሞ ሚኒስትር “ቢያሸንፉ እደሰታለሁ” ሲል ይህን ጽፏል፡፡  

“ሰውየው ያንን ወንበር ይመጥናሉ ብዬ የማስበው የማምነው አለ ምክንያት አይደለም ። የሀገራቸው የጤና ሚኒስትር በነበሩ ወቅት ተጨባጭ የጤና ዘርፍ ለውጥ ማምጣታቸውን በማየቴ ነው ። ‘አንዲትም እናት በወሊድ አትሞትም’ የሚለውን የተጋነነ አባባል ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባያደርጉም (ሊያደርጉ ባይችሉም) እጅግ ትልቅ ለውጥ አምጥተዋል። አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች ቁጥር 10 በመቶ የማይሞላ ከነበረበት ተነስቶ አሁን ይህ ቁጥር እጅግ ከፍ ብሏል። ከነችግሮቹም ቢሆን በጤናው ዘርፍ ለታየው ለውጥ የዶ/ር ቴድሮስ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። ከዚያም ሌላ እኚህ ሰው ኢትዮጵያዊ ናቸው። አንድ ኢትዮጵያዊ ምሁር ለዚያ ክብር ሲወዳደር እሱን ዘልዬ ባዕድ ልመርጥ አልችልም። ከኢሕአዴግ ባለስልጣናት አንዱ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሪነት ቢወዳደርና ድምፅ መስጠት ቢቻል የምመርጠው እሱን ነው ። ያ ሰው 'ኢትዮጵያዊው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ፕሬዝዳንት' ተብሎ ነው የሚጠራው። ዶ/ር ብርሀኑ ነጋም ለዚያ ክብር ቢወዳደሩ የምመርጠው እሳቸውን ነው። ለእኔ ከእነዚህ ሁሉ ሰዎች በላይ ኢትዮጵያ ትበልጣለች። ፖለቲካው ሁለተኛ ጉዳይ ነው፡፡” 

በተቃራኒው ወገን ባሉት ግን በዶ/ር ቴድሮስ የፖለቲካ ስልጣን ዘመን የደረሱ ጉዳቶች እና ጥፋቶች ቅድሚያ ያገኛሉ፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ የካቢኔ አባል በነበሩ ወቅት ለተፈጸሙ ግድያዎች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ሌሎች ጥፋቶች “አባሪ ተባባሪ” በመሆናቸው ሊጠየቁ እንጂ ለዓለም አቀፍ የኃላፊነት ቦታ ሊታጩ አይገባም ባይ ናቸው፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩ ወቅት በኢትዮጵያ ተከስተው የነበሩ “የኮሌራ ወረረሽኞችን ደብቀዋል” በሚል የተሰነዘረባቸው ክስ “ኒውዮርክ ታይምስ” እና “ዋሽንግተን ፖስት” ጋዜጦች ማተማቸውን ለተቺዎቻቸው የመከራከሪያ አቋማቸዉን አጠናክሮላቸዋል። ዜና ማርቆስ የተባሉ ግለሰብ ማክሰኞ ዕለት ይህንኑ የሚያንጸባርቅ ጽሁፍ በፌስ ቡክ ገጻቸው ለንባብ አብቅተዋል፡፡   

“አንዳንድ ሰዎች ዶ/ር ቴድሮስ ቢመረጥ ኢትዮጵያዊ ነው ይሉናል ። ዜግነቱ ብቻ ምን ይሰራልናል ኢትዮጵያዊነት ተሰምቶት ለኢትዮጵያ ካልሰራ? ወገኖቹ ህክምና ሲያጡ ታማሚ ሲደብቅ፣ የኮሌራ ወረርሺኝ ቢከሰት ሲደብቅ፣ አተት (ይቺ ቃል የእነርሱ ፍልስፍና ትመስለኛለች) ቢከሰት ሲደብቅ የኖረ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ምን ሲከሰት፣ ምን ሲያመን ሊረዳን ነው ቴድሮስ ከሌሎች ይሻለናል የሚሉን? ዜግነት ሲነሳ ጀርመናዊውን የ“ሰዎች ለሰዎች” መስራችና ዳይሬክተር ዶ/ር ካርል ሄንዝ በም እንይ፡፡ እስቲ ከየት ነበር? ከወለጋ፣ ከሸዋ ወይስ ከሐረር? ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ በጎ አድራጎት ሠርቶ በክብር ያለፈ ያ ብሩክ ሰው ከየት ነበር? ለእኛ መልካም ሰውነት ሳይኖረው፣ መሞቻችንን ሲያሰላ የሚያድር የተረገመ ቡድን አባል የሆነ፣ እኩይ ሰው እንዴት ሆኖ ይመረጥ? እባካችሁ እየተስተዋለ።”

የዶ/ር ቴድሮስ ደጋፊዎችና ተቺዎች በማህበራዊ መገናኛዎች ከፊርማ ማሰባሰብ እስከ ሰልፍ ማደራጀት የሄደ የተጧጧፈ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በትዊተር የራሳቸውን ሀሽታግ ፈጥረው ቅስቀሳቸውን ቀጥለዋል፡፡ በቀጣዩ ሳምንት መጀመሪያ በዤኔቭ ስዊዘርላንድ የሚካሄደው የዓለም የጤና ድርጅት አጠቃላይ ስብሰባ የዶ/ር ቴድሮስን ዕጣ ፈንታ ይወስናል፡፡ 

ሰማያዊ ፓርቲን ወክሎ በ2007ቱ ምርጫ (ለምክር ቤት አባልነት የተወዳደረዉ) የተሳተፈው ዮናታን ተስፋዬ ከታሰረ አንድ ዓመት ከአምስት ወር አልፎታል፡፡ “ቀስቃሽ ጽሁፎችን በፌስ ቡክ አስተላልፏል” በሚል የቀረበበትን ክስ ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ፍርድ ባለፈው ማክሰኞ ግንቦት 8 ሰጥቷል፡፡ ፍርዱን አስመልክቶ በርካቶች አስተያየታቸውን በማህበራዊ መገናኛዎች አጋርተዋል፡፡

ዘካርያስ ዘላለም በትዊተር ገጹ “ኢህአዴግ በዮናታን ተስፋዬ እስር ለወጣቶች ያስተላለፈው መልዕክት ግልጽ ነው፡፡  አርሰናል፣ ቦሊውድ እና ጫትን አጥብቃችሁ ያዙ፡፡ በእኛ ስራ እጃችሁን እንዳትከቱ” ነው ሲሉ የወጣቱ ፖለቲከኛ ክስ “እኔን ያየ ተቀጣህ” አንደምታ እንዳለው ጽፈዋል፡፡ 

ሰሚር አሊ በፌስ ቡክ ባጋራው ጽሁፉ “ዮኒ ያመንክበትን ብቻ በመናገርህ እንዲህ ሲያሰቃዩህ ማየት ያማል፡፡ ከሁሉም በላይ የአንተን እና አብረውህ ሀሳባቸውን በመግለጻቸው ብቻ ታስረው የሚሰቃዩ ሺዎች ልፋት ከንቱ የሚያደርጉ የእርስ በእርስ ሹኩቻዎች፤ ብሽሽቆች፤ የመጠላለፍ አዙሪቶችን ማየት ደግሞ እጅግ ያሳፍራል” ሲል የተሰማውን ሀዘን ገልጿል፡፡ 

የዩኒቨርስቲ መምህሩና ጦማሪው ስዩም ተሾመ “ዮናታን ተስፋዬ በፌስቡክ ላይ በፃፈው ፅሁፍ ምክንያት በጸረ-ሽብር አዋጁ ተከስሶ ‘ጥፋተኛ’ መባሉን ስትሰሙ እንዳንዶቻችሁ ‘ምን ብሎ ፅፎ ይሆን?’ የሚል ጥያቄ እንደምታነሱ እገምታለሁ” በማለት አቃቤ ህግ ካቀረበው ክስ የተወሰነውን ቀንጭቦ በፌስ ቡክ ገጹ አቅርቧል፡፡ “ይህ በሽብርተኝነት የሚያስከስስ ከሆነ ሁሉም የፌስቡክ ተጠቃሚ አሸባሪ ነው!” ሲል አስተያየቱን አስፍሯል፡፡

ስሞዖን አለባቸው በትዊተር ገጹ “ሀገሬ በየቀኑ ወደታች የምትንደረደርበትን ማየት ያማል፡፡ ዮናታን ፌስቡክ ላይ በጻፈው ብቻ አሸባሪ ብሎ መፍረድ? ብዙዎች ሀሳባቸው ለመግለጽ ከባድ የሚሆንባቸው ዮናታን ተስፋዬ እንደቀረበበት አይነት በማይረባ፣ አላስፈላጊ እና ፖለቲካዊ ክስ ምክንያት ነው” ሲል ጽፏል፡፡ 

የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት በቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ላይ የቅጣት ውሳኔ ለማሳለፍ ለመጪው ግንቦት 17 ቀጥሯል፡፡ ዮናታን ጥፋተኛ የተባለበት አንቀጽ ከአስር እስከ 20 ዓመት እስራት ያስቀጣል፡፡     

በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው የአዲስ አበባ አካባቢ በመጋቢት ወር መጀመሪያ በደረሰው የቆሻሻ መደርመስ 115 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ አሳዛኝ አደጋ የተነኩት የከተማይቱ ነዋሪዎች እና ለጋሾች አደጋው በደረሰበት ቦታ ይኖሩ ለነበሩ እና በህይወት ለተረፉ ሰዎች ያዋጡት ገንዘብ ወደ 76 ሚሊዩን ብር መድረሱን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበው ነበር፡፡ ቱጃሩ ሼህ መሐመድ አሊ አላሙዲ ብቻ 40 ሚሊዮን ብር መስጠታቸውም ተዘግቦ ነበር፡፡ ይከፋፈላል የተባለው ገንዘብ በመንግስት መገናኛ ብዙሃኖች እና አጋሮቻቸው እንደተዘገበው ለተጎጂዎች አለመድረሱ በማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ዘንድ ሲነሳ ከርሟል፡፡ ጉዳዩ ሲብላላ ከርሞ “ገንዘቡ የት ገባ?” ወደሚል ዘመቻ አድጓል፡፡

ካለፈው ረቡዕ እስከ ዛሬ ድረስ ይቆያል በተባለው ዘመቻ ዋነኛ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል ኪራም ከበደ አንዱ ነው፡፡ የዘመቻውን ዓላማ ሰኞ ዕለት በፌስ ቡክ ገጹ እንዲህ አሳውቆ ነበር፡፡ “የቆሼ ተጎጂዎች ዛሬም የሚደርስላቸው መንግሥት አላገኙም ። የሚወዷቸውን ቤተሰቦቻቸውን እና ንብረታቸውን ያጡ ወገኖች ዛሬም እንባቸውን የሚያብስ አላገኙም። በስማቸው የተሰበሰበው ብዙ ሚሊየን ብር የት እንደገባ የሚተነፍስ ጠፍቷል ዘመቻው መንግሥት ከህብረተሰቡ የሰበሰበውን ገንዘብና ቁሳቁስ ለተጎጂዎች እንዲያደርስ የሚጠይቅ ይሆናል፡፡” ዘመቻውን የተቀላቀለው ጸሀፊ በኃይሉ ገብረእግዚያብሔር ተከታዩን መልዕክት በፌስ ቡክ አጋርቷል፡፡

“ግለሰቦች ገንዘብ አሰባስበው ሲረዱ፣ "ሕገ ወጥ ነው!" አላችሁ፤ በራሳችሁ ሚዲያም ምስልና ስማቸውን እየለጠፋችሁ አስሳጣችሁ፡፡  በመቀጠል መለመኛ የባንክ ሒሳብ ቁጥር አውጥታችሁ "ለወገን ደራሽ ወገን ነው!" አላችሁ፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ በየተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን የእርዳታ ጥሪ ላካችሁ፡፡ ገንዘቡ ተሰበሰበ፤ ተሰበሰበ፤ ተሰበሰበ፤ ተሰበሰበ፡፡ በስማቸው የተለመነባቸው ምንዱባን ግን ገንዘቡ አልደረሰንም እያሉ ነው፤ ታዲያ የት ገባ!? በሕዝብ እንባ ሻወር መውሰድ ይብቃ! ከድሃው ሕዝብ የተሰበስበው ብር ለድሆቹ ይሰጣቸው! ስቃያቸውን አታራዝሙት!፡፡”

ሄዋን አለማየሁ በበኩሏ ስለጉዳዩ ያላትን አስተያየት በፌስቡክ እንዲህ አካፍላለች፡፡ 

“ሁሌም በጣም ከሚገርሙኝ እና ቁስል ከሚያረጉኝ ነገሮች መሃል በሃገራችን አንድ ችግር ወይ አደጋ ሲከሰት ተከትሎት የሚመጣው መፍትሄው ሳይሆን ነገሩን ጭራሽ የሚያባብስ ተጨማሪ መአት መሆኑ ነው። ሰሞኑን ስለ ቆሼ ተጎጂዎች የምሰማው ለዚህ ምሳሌ ነው። መንግስት ያን ሁሉ ገንዘብ ሰብስቦ የታሰበላቸው ተጎጂዎች ገንዘቡ አልደረሳቸውም ብቻም ሳይሆን ባዶ ፖስታ እየተሰጣቸው ዜና ተሰራባቸው ሲባል መስማት እንዴት ያማል!!? ልጆቿን እና ባሏን ያጣችን እናት ‘ገና ምን አይተሽ አይነት ነገር’ የተሰበሰበላትን ገንዘብ አለመስጠት ምን ይሉታል? ይሄ በጣም ቢያሳዝንም ቢያንገበገብም ከነሱ አይጠበቅም አይባልም። ወደ ፊትስ ሌላ አደጋ ሲመጣ (እንዳለመታደል ሆኖ ላለመከሰቱ ምንም ዋስትና የለም) ማን ነው አምኖ ገንዘብ የሚያዋጣው?”

በዶ/ር ቴድሮስ ጉዳይ የጀመርነውን መነጋገሪያነቱ ስለቀጠለው ቴድሮስ ካሳሁን ጠቀስ በማድረግ እንደመድማለን፡፡ የቴዲ አፍሮ “ኢትዮጵያ” አዲስ አልበም ከፍተኛ ተደማጭነት ማግኘቱና የብዙዎችን ቀልብ ተቆጣጥሮ መክረሙ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስቧል፡፡ ቴዲ አፍሮም ቃለ ምልልስ በመስጠት ተጠምዶ ሰነብቷል፡፡ በሳምንቱ መጨረሻ በሀገር ቤት ለንባብ የበቁ ጋዜጦች ቃለምልልሶቹን እና ዘገባዎችን ይዘው ወጥተዋል፡፡ 

አድናቂዎቹ የመገናኛ ብዙሃኑን ዘገባዎች እያጣቀሱ የድምጻዊውን አንደበተ ርዕቱትነት በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን አወድሰዋል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን የሚሰብኩ ንግግሮቹን ሲቀባበሏቸው እና “በአንድነት የመቆም” መልዕክቶቹን ሸጋነት ሲመሰክሩ ተስተውለዋል፡፡ ቴዲ የሚያቀነቅናቸውን ሀሳቦች የሚቃወሙቱ በበኩላቸው “ኢትዮጵያ አሁን የደረሰችበትን ደረጃ ያልተረዳ፣ የድሮ ስርዓት ናፋቂ እና ብዝሃነትን የማይቀበል” ሲሉ ቃለ ምልልሶቹን አጣጥለዋቸዋል፡፡


ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ 
 

Audios and videos on the topic