የይቅርታ ቦርድ የእነ አቶ በቀለን ጉዳይ ለፕሬዝዳንቱ መርቷል | ኢትዮጵያ | DW | 12.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የይቅርታ ቦርድ የእነ አቶ በቀለን ጉዳይ ለፕሬዝዳንቱ መርቷል

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ በቀለ ገርባ እና አብረዋቸው የተከሰሱ ስድስት ሰዎች ክሳቸው እንዲቋረጥ መንግስት መወሰኑን አስታውቋል፡፡ ፍርድ ቤት በመድፈር ወንጀል የተላለፈባቸው የእስር ቅጣትም በይቅርታ ቦርድ እንዲታይ እንደሚያደርግም ገልጿል፡፡ ቤተሰቦቻቸው እና ጠበቆቻቸው ግን በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት መረጃ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:52

«ቤት ስደርስ ነው የማምነው»- አቶ በቀለ ገርባ

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በእስር ላይ የሚገኙ ሌሎች የፓርቲው አመራሮች እና አባላት ክስ እንዲቋረጥ መወሰኑን ዛሬ አስታውቋል፡፡ ክሳቸው እንዲቋረጥ ከተወሰነላቸው ውስጥ የፓርቲው ምክትል ጸሐፊ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ የወጣቶች ክንፍ ምክትል ኃላፊው አቶ ጉርሜሳ አያኖ እና የወጣቶች ክንፍ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ አዲሱ ቡላላ ይገኙበታል፡፡ 

በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ክሳቸው በአንድ መዝገብ በመታየት ላይ የሚገኘው አራቱ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች “ፍርድ ቤት ተዳፍረዋል” በሚል አንድ ዓመት የእስር ቅጣት እንደተፈረደባቸው ይታወሳል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በዛሬው መግለጫው እንዳስታወቀው የእስር ቅጣታቸው ጉዳይ በፌደራል ይቅርታ ቦርድ ይታያል፡፡ ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማዕረጉ አሰፋ ተከታዩን ማብራሪያ ዶይቼ ቬለ ሰጥተዋል፡፡  

“ቀደም ብሎ ተወስኗል ተብሎ ነው ለቦርድ እዚህ የቀረበው፡፡ በጠቅላይ አቃቤ ሕግ የይቅርታ ቦርድ አለ አይደል? በእርሱ በኩል ነው [የሚታየው]፡፡ ምክንያቱም ቀደም ሲል በችሎት መድፈር የተቀጡ ስለሆነ በተቀጡበት ጉዳይ ላይ የግድ ምህረት የሚያደርገው በቦርዱ በኩል ለፕሬዝዳንት ቀርቦ ነው፡፡ ቦርዱ ውሳኔውን አስተላልፏል፡፡ አራቱ ለአንድ ዓመት፤ ሁለት ጊዜ ስድስት ወር ነው፤ የተቀጡት፡፡ ሶስቱ ስድስት ወር ነው የተቀጡት። ስለዚህ ሰባቱም በምህረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቦርዱ መግለጫውን አቅርቧል፡፡ የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ነው የሚያስተላልፈው፡፡ የቦርዱ ውሳኔ ይሄ ነው” ብለዋል አቶ ማዕረጉ፡፡  

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ውሳኔን አስመልከቶ አቶ በቀለ ገርባም ሆነ ሌሎች ተከሳሾች ምንም መረጃ እንዳልደረሳቸው ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ፡፡ የአቶ በቀለ ገርባ ልጅ ወይዘሪት ቦንቱ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት እስረኞቹን ለመጠየቅ ዛሬ ጠዋት ወደ ማረሚያ ቤት የሄዱ የቤተሰብ አባላት የተለየ ነገር አለመስማታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከአባታቸው ጋር ትላንት በተገናኙበት ወቅት በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ስለሚወራው የፍቺ ጉዳይ ተነጋግረው እንደነበር የገለጹት ወይዘሪት ቦንቱ አቶ በቀለ ይህን አስመልክቶ የሰጧቸውን ምላሽ እንዲህ አጋርተዋል፡፡ 

“እስከ ትላንት ድረስ ምንም የተነገረው ነገር የለም፡፡ ማህበራዊ ድረገጾች ላይ ያየሁት ነገር ነበር እና እርሱን አንደዚህ እየተባለ ነው ብዬ ነገርኩት፡፡ እስቲ እውነት ካደረጉት ቤት ስደርስ ነው የማምነው አለ፡፡ ያው ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ እንዲህ እየተባለ በዋስትናው ጊዜም የምታስታውሱት ነው፡፡ የዋስትና መብቱ ከተፈቀደ በኋላ ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ከተባለ በኋላ ነው ለሌላ ጊዜ እየተቀጠረ እስከዛሬ የተደረሰው ማለት ነው፡፡ እንደገና ደግሞ ባለፈውም መንግስት መግለጫ ከሰጠ በኋላ አስር ጊዜ ይሆናል የተለያየ ነገር ሲናገሩ የነበረው እና ቤት ስደርስ ነው የማምነው አለ እርሱም” ብለዋል ቦንቱ፡፡   

የእነ አቶ በቀለ ጠበቃ የሆኑት አቶ ወንድሙ ኢብሳም በተመሳሳይ ስለ ክስ መቋረጡም ሆነ ይቅርታው ጉዳይ የደረሳቸው መረጃ እንደሌለ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡ ደንበኞቻቸው ፍርድ ቤት በመድፈር ወንጀል ፍርደኞች እንደሆኑ ያስታወሱት ጠበቃው ስለይቅርታ አሰጣጡ ጉዳይ ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ “መንግስት ይቅርታ ማድረግ የሚችለው ታሳሪው፣ ፍርደኛው መጠየቅ አለበት፡፡ ህጉ ይህን ይላል፡፡ ፍርደኛ ናቸውና፡፡ ይቅርታ አልጠይቅም የሚሉ ከሆነ ምንድነው አማራጩ? ምህረት ማድረግ ነው፡፡ ምህረት ማለት ሙሉ ለሙሉ ማንሳት ነው፡፡ ፍርደኛ ሆኖ ክሱንም ሌላውንም እንዳልነበረ፣ ነጻ ሰው ሆኖ የሚቆጠር ማለት ነው፡፡ አሁን ይህን ለማድረግ ሰዎቹ ይፈቅዳሉ፣ አይፈቅዱም ሌላ ነገር ነው” ይላሉ አቶ ወንድሙ።    

“እነ አቶ በቀለ ይቅርታ ጠይቁ ይባላሉ ወይ?” ተብለው ለተጠየቁት የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የጽህፈት ቤት ኃላፊ የተረጋገጠ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ “ምናልባት የእነርሱ ጥያቄ ቀድሞ መቅረብ ያለበት ይመስለኛል፡፡ እርሱ መቅረቡን አላስታውስም፡፡ ነገር ግን ለቦርዱ ስለቀረበ፤ እኔ የቦርዱ አባል ስላልሆንኩኝ፤ በዚያ በኩል ምን እንደተደረገ አላውቅም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።  

እነ አቶ በቀለ በጸረ-ሽብር ሕጉ ክስ ሲቀርብባቸው 22 ተከሳሾች በተካተቱበት መዝገብ ነበር፡፡ ጉዳያቸውን ሲመለከት የቆየው ፍርድ ቤት አምስቱን በነጻ አሰናብቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ጉዳያቸውን ሲከታተሉ ከቆዩ ቀሪዎቹ ተከሳሾች መካከል ዘጠኙ በአንደኛው ዙር የእስረኞች ፍቺ ተለቅቀዋል፡፡

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ

 

Audios and videos on the topic