የዩጋንዳ ፕሬዚደንት የገጠማቸው ፉክክር | አፍሪቃ | DW | 20.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የዩጋንዳ ፕሬዚደንት የገጠማቸው ፉክክር

በዩጋንዳ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አማማ ምባባዚ እአአ በ2016 ዓም በሚደረገው ምርጫ በፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ አንፃር ለገዢው ብሔራዊ መድን ፓርቲ መሪነት እና ለፕሬዚደንትነቱ ሥልጣን እንደሚወዳደሩ አስታወቁ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:52
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
05:52 ደቂቃ

የዩጋንዳ ፕሬዚደንት የገጠማቸው ፉክክር

የ70 ዓመቱ ፕሬዚደንት የቅርብ የነበሩት ምባባዚ የብሔራዊው መድን ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ቀጣዩ የሀገሪቱ መሪ የመሆን ፍላጎት እንዳላቸው ሰሞኑን በዩቲውብ አመልክተዋል።

« ዛሬ እዚህ የመጣሁት የናንተን ድምፅ በመፈለጌ ነው። በመጀመሪያ የፓርቲዬ የብሔራዊው መድን ፓርቲዬ መሪ ለመሆን፣ ቀጥዬም፣ እአአ በ2016 ዓም ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ የመላይቱ ሀገር ፕሬዚደንት ለመሆን በማደርገው ጥረቴ የናንተን ድምፅ በመፈለጌ ነው። »

ምባባዚ የ2016 ዓም ምርጫ ሀገራቸውን ወደከፍተኛ የልማት ደረጃ የሚያሸጋግር እንደሚሆን ለዩጋንዳውያን አስታውቀዋል። ዜናው በሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ልዩ ትኩረት ያገኘ ሲሆን፣ ዩጋንዳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሙሴቬኒ የገዛ ራሳቸው ፓርቲ የሚፎካከራቸው ብቁ ዕጩ መገኘቱን ብዙዎች በደስታ ተቀብለዋል። እአአ ከ1986 ዓም በሥልጣን ላይ የሚገኙት ሙሴቬኒ ለብሔራዊው መድን ፓርቲያቸው አመራር እስካሁን አንዴም ፉክክር ቀርቦባቸው አያውቅም።

ምባባዚ በሙሴቬኒ ስር ለብዙ ዓመታት ማገልገላቸው በሙሴቬኒ አንፃር ለመወዳደር የያዙትን ዕቅዳቸውን ሊያዳክመው እንደሚችል የትልቆቹ ሀይቆች የፖለቲካ ጥናት ተቋም የመልካም አስተዳደር እና ልማት ጉዳዮች ተንታኝ ጎድበር ቱሙሻቤ ቢጠቁሙም፣ በሰፊው የፓርቲው አባላት ደረጃ ያላቸው ከፍተኛ ድጋፍ ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገምታሉ።

« በብሔራዊው የመድን ፓርቲ ውስጥ የራሳቸውን አውታር ሲዘረጉ ቆይተዋል፣ ይህን በፓርቲው ያላቸውን ድጋፍ ፣ ከፓርቲው በሚባረሩበት ጊዜም፣ መባረራቸው ስለማይቀር፣ ይዘው መቀጠል ከቻሉ ፣ በሚቀጥሉት ወራት የሚጀመረውን የምርጫ ዘመቻ አካሄድን በተመለከተ ወሳኝ ሚና ሊጫወት ይችላል። »

ምባባዚ ፕሬዚደንት ሙሴቬኒ የሚመሩት መንግሥት ማከናወን ሲገባው ያላከናወናቸው ብዙ ጉዳዮች ፣ አሉ በሚል አብቅተው ይወቅሳሉ። የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ አውታሮችን ማስፋፋት በሚችሉበት ድርጊት ላይ እንደሚያተኩሩ እና ጠንካራ የመልካም አስተዳደርን ሥርዓትን እንደሚገነቡ ነው ምባባዚ ያስታወቁት።

« ቀጣዩ ምርጫ የወደፊቱን ዕጣ የሚመለከት ይሆናል። ዩጋንዳ ለሁሉም ዜጎችዋ የምትመች ሀገር ማድረግ ይሆናል። ሀገራችንን ልማት ማነቃቃት እና ለ21ኛው ምዕተ ዓመት እና ከዚያም በኋላ ለሚቀጥለው ጊዜ ዝግጁ ማድረግ ይሆናል። ደካማ እና ብቃት አልባ ለሆነው የመንግሥቱ አውታር አዲስ የሕይወት እስትንፋስ የሚሰጥም ይሆናል። የትምህርቱን፣ የጤና ጥበቃው እና የማህበራዊ አገልግሎት ዘርፎችን ማሻሻል እና ለሁሉም በእኩል ደረጃ ማዳረስ ይኖርብናል፣ የብሔራዊ የመድን ፓርቲያችንንም ዴሞክራሲያዊ እና በሕዝብ ዘንድም ተጠያቂ በማድረግ ካሁን ቀደም ይዞት የነበረውን ግርማ እንዲያገኝ እንሰራለን። »

ምባባዚ በዩጋንዳ የፕሬዚደንት ሙሴቬኒን የ30 ዓመታ አመራር ለማብቃት በአንፃራቸው እንደሚፎካከሩ እስካሁን በሀገሪቱ ይፋ ያደረጉ ሶስተኛው የታወቁ ፖለቲከኛ ናቸው። የምባባዚን ዕቅድ የገዢው ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ጃስቲን ካሱል ስርዓት የጎደለው ሲሉ አጣጥለውታል። ሌሎቹ ሁለት የሙሴቬኒ የግል ሀኪም የነበሩት ዶክተር ኪሴ ቤሲጄ እና የዩጋንዳ ጦር የቀድሞ ዋና አዛዥ አኔ ማጊሻ ማንቱ ናቸው። እንደሚታወሰው፣ የዴሞክራቲክ ለውጥ መድረክ መሪ ኪሴ ቢሲጄይ እአአ በ2011 ዓም በዩጋንዳ በተደረገው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ በሙሴቬኒ ተሸንፈዋል። ይህ በዚህ እንዳለ፣ የዩጋንዳ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሙሴቬኒን በሕዝብ ድምፅ ከሥልጣን ለማስነሳት የጀመሩትን ትግላቸውን ለማጠናከር በማሰብ ባለፈው ሳምንት በምህፃሩ «ቲዲኤ» በሚል የሚታወቅ አንድ የዴሞክራቲክ ህብረት አቋቁመው ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ አንድ የጋራ ዕጩ እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል። በዚሁ ህብረ።ት የሚጠቃለሉት የዴሞክራቲክ ለውጥ መድረክ፣ የወግ አጥባቂ ፓርቲ፣ የዴሞክራቲክ ፓርቲ እና የዩጋንዳ ፌዴራል ህብረት የተሰኙት የተቃዋሚ ቡድኖች ናቸው።

አርያም ተክሌ

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic