የዩጋንዳ ጋዜጦች የገጠማቸው ችግር | አፍሪቃ | DW | 22.05.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የዩጋንዳ ጋዜጦች የገጠማቸው ችግር

ፖሊስ የዩጋንዳ ፖሊስ ካለፈው ሰኞ ወዲህ በመዲናይቱ ካምፓላ የሚገኙትን የትላልቆቹን የመገናኛ ብዙኃን ጽሕፈት ቤቶችን በመያዝ፣ ጋዜጠኞች ወደ ስራ ገበታቸው እንዳይሠማሩ አከላክሎዋል። ፖሊስ የዕለታዊዎቹ ጋዜጦች

« ዘ ዴይሊ ሞኒተር »፣« ኦብዘርቨር » እና « ዘ ሬድ ፔፐር ር » ጽሕፈት ቤቶችን በቁጥጥር ያዋለው፣ አንድ ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለሥልጣን ጻፉት የተባለ አንድ አወዘጋቢ ደብዳቤ ለመፈለግ ሲል መሆኑን የመገናኛ ብዙኃኑ ጽሕፈት ቤቶች አባላት አስታውቀዋል። ንብረትነታቸው የ « ዘ ኔሽን ሜዲያ » የሆኑ ሁለት የራድዮ ጣቢያዎችም ካለፉት ሁለት ቀናት ጀምረው ሥርጭታቸውን ማስተላለፍ መከልከሉንም ነው ጋዜጠኞቹ የገለጹት።
በዩጋንዳ መዲና ካምፓላ አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ጽሕፈት ቤቶችን የዘጉት ከባድ የጦር መሣሪያ የታጠቁ ፖሊሶች የሀገሪቱ የስለላ ድርጅት አስተባባሪ የሆኑት ባለ አራት ኮከብ ጀነራል ዴቪዲ ሴጁሳ ቲንየፉዛ አወጡት የተባለ አንድ አከራካሪ ጽሑፍ እንዲፈልጉ ፍርድ ቤት የፍተሻ ትዕዛዝ እንደሰጣቸው በማስታወቅ በዕለታዊው የደይሊ ሞኒተር »ጽሕፈት ቤት ፍተሻ ማካሄዳቸውን የፖሊስ ቃል አቀባይ ጁዲት ናባኮቫ አስረድተዋል።
« የዩጋንዳ ፖሊስ ጀነራል ዴቪዲ ሴጁሳ ቲንየፉዛ ጻፉት የተባለ አንድ ደብዳቤ እና ሌሎችም ሰነዶችን ከዴይሊ ሞኒተር ጋዜጠኞች እንዲቀበል፣ እንዲሁም፣ ጋዜጠኞቹ ምንጮቻቸውን እንዲያሳውቁ የሚያዝ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ባለፈው ግንቦት 15፣ 2013 ዓም ከፍርድ ቤቱ ዋና ዳኛ ናካዋ ደርሶታል። »

ጀነራል ዴቪዲ ሴጁሳ ቲንየፉዛ ጻፉት የተባለው ጽሑፍ የዩጋንዳ ፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ልጃቸውን ብርጋድየር ሙሆዚ ካይኔሩጋባን በፕሬዚደንትነት እንዲተኩዋቸው እያዘጋጁዋቸው እንደሆኑ እና ይህንኑ የፕሬዚደንት ሙሴቬኒን ሀሳብ የሚቃወም ማንኛውም ግለሰብ የሚገደልበት ሥጋት መኖሩን ነበር ያመለከተው።
የዴይሊ ሞኒተር ዋና አዘጋጅ ዦሴፍ ኦዲንዶ የተባለው ደብዳቤ በጽሕፈት ቤታቸው እንደሌለ ፍተሻው አላስፈላጊ መሆኑን ለፖሊስ ቢገልጹም ፍተሻው ተካሂዶዋል ብለዋል።
« ደብዳቤው ስለሌለ ፍተሻው ጥቅም አልባ መሆኑን እንደሆነ ነበር ልናስረዳቸው የሞከርነው። ጀነራል ዴቪዲ ሴጁሳ ቲንየፉዛ ለጓዳቸው ጻፉት የተባለው ደብዳቤ እኛ ዘንድ የለም። አሁን ተሰሚነት ባላቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት አማካኘነት ፖሊስ የመገናኛ ብዙኃኑ ድርጅታችንን አሰራር እንዲረዳው ለማድረግ እየሞከርን ነው። » ይህን በተመለከተ ፖሊሶች ባለፈው ሣምንት ሦስት የ « ዴይሊ ሞኒተር » ጋዜጠኞችን መርምረዋል።

Uganda Poliizei

የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ሰነድ እንዲሰጡ እና ምንጮቻቸውን አሳልፈው እንዲሳውቁ ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ትዕዛዝ የጋዜጠኝነቱን ሥነ ምግባር የሚፃረር እና የፕሬስ ነፃነትን የሚረግጥ ነው በሚል የዩጋንዳ ጋዜጠኞች፣ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል። በዩጋንዳ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ሊቪንግስተንን የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መንግሥት ከፕሬሱ ጋ የሚግባባበት ሻል ያለ መንገድ እንዲያፈላልግ አሳስቦዋል። « መረጃ ማግኘት የሚቻልበት የተሻለ መንገድ አለ ብለን እናስባለን። ያልተቋረጠ ክትትል እና ጽሕፈት ቤቶችን መዝጋት በራሱ ግን መፍትሔ አይደለም። » ፖሊስ ኬ ኤፍ ም እና ዴምቤ ኤፍ ኤም የተባሉትን የራድዮ ጣቢያዎች ሥርጭት አቋርጧል የተባለበትን ዜና የፖሊስ ቃል አቀባይ ጁዲት ናባኮቫ በማስተባበል የዘጋው ይሆን የዩጋንዳ ኮምዩኒኬሽን ሚንስቴር መሆንኑን አስታውቀዋል።
የዩጋንዳ ፖሊስ ወቀሳ ቢፈራረቅበትም የዕለታዊዎቹ ጋዜጦች « ዘ ዴይሊ ሞኒተር »፣ « ኦብዘርቨር » እና « ዘ ሬድ ፔፐር ር» ጽሕፈት ቤቶችን አሁንም እንደተቆጣጠረ ይገኛል።

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic