1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕገ መንግስት ማሻሻያው በተቃዋሚዎች እና ድርጅቶች ተተችቷል

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 18 2010

የዩጋንዳ የተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ባደረገው ስብሰባ የሐገሪቱን የፕሬዝዳነት ሥልጣን በሚይዙ ፖለቲከኞች ላይ የተጣለዉን የዕድሜ ገደብ አንስቷል። የፕሬዝዳንትነት ስልጣንን ለመያዝ የሚወዳደሩ ግለሰቦች ዕድሜያቸው ከ75 ዓመት እንዳይበልጥ የዩጋንዳ ሕገ መንግስት ይደነግግ ነበር። ማሻሻያውን የገዢው ፓርቲ አባላት አፅድቀዉታል፡፡

https://p.dw.com/p/2pxwF
Uganda Parlament Debatte über Alter für Präsidialamt
ምስል DW/L. Emmanuel

የህገመንግስት ማሻሻያው በተቃዋሚዎች ክፉኛ ተተችቷል

ለጠብ የሚጋበዙ የህዝብ ተወካዮች፤ ግብግብ ያጀበው የእንደራሴዎች ውሎ - ይህ በዩጋንዳ ፓርላማ ከሰሞኑ የተደጋጋመ ትዕይንት ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ፕሬዘዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ለተጨማሪ ዓመታት ሥልጣን ላይ እንዲቆዩ ይረዳል የተባለው የህገመንግስት ማሻሻያ ረቂቅ ነው፡፡ በካሜራ ፊት ለጠብ የሚጋበዙት የህዝብ እንደራሴዎች ለሶስት ጊዜያት ያህል የማሻሻያውን ረቂቅ በመደገፍ እና በመቃወም የከረረ ሙግት እና አንባጓሮ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በስተመጨረሻ ግን የማሻሻያ ረቂቁን  የደገፉት ቀንቷቸዋል፡፡

Uganda Kampala  Rebecca Kadaga Sprecherin Parlament
ምስል DW/Lubega Emmanuel

የዩጋንዳ ፓርላማ አፈጉባኤ ሬቤካ ካዳጋ ‹‹የተከበራችሁ አባላት፡፡ ሁለት ድምጽ ተዓቅቦች አሉን፡፡ 97 ተቃውመዋል፡፡317 ደግሞ [ማሻሻያውን] ደግፈውታል ›› ሲሉ የየህገ መንግስት ማሻሻያው ረቂቅ በምክር ቤት ያገኘውን ድምጽ ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርገው ነበር፡፡ በስልጣን ላይ ባለው ብሔራዊ ተከላካይ ንቅናቄ  (National Resistance Movement-NRM) ፖለቲካ ፓርቲ እንደራሴዎች ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ ያገኘው አዲሱ የህገመንግስት ማሻሻያ ረቂቅ በፕሬዝዳንትነት ለመወዳዳር ከፍተኛው የዕድሜ ገደብ የነበረውን 75 ዓመት ያስቀራል፡፡

በተጨማሪም የህዝብ እንደራሴዎች የፓርላማ ዘመን እና የሀገሪቱ መሪ የአንድ ዙር የስልጣን ቆይታ ከአምስት ዓመት ወደ ሰባት ዓመት እንዲራዘም ያደርጋል፡፡ የአሁኑ የህግ ማሻሻያ ሀገሪቱን ከ30 ዓመታት በላይ ያስተዳደሩት ዮዌሪ ሙሴቬኒ በጎርጎሮሳዊያው 2023 ለስድስተኛ ጊዜ ለፕሬዘዳንትነት እንዲወዳዳሩ ያስችላቸዋል፡፡ ‹‹ለተጨማሪ ዓመታት በስልጣን ለመሰንበት መንገድ ጠራጊ ሆኖላቸዋል›› በሚልም እየተነሳ ነው፡፡

ሸንጎ ለዲሞክራሲያዊ ለውጥ (Forum for Democratic Change-FDC) የተሰኘው ዋነኛ ተቃዋሚ ፖለቲካ ቡድን የቀድሞው መሪ ኪዛ ቤሲጄ የህግ ማሻሻያውን በጽኑ ከተቃወሙት መካከል ቀዳሚው ናቸው፡፡ ውሳኔውን በካምፓላ ካቶንጋ መንገድ በሚገኝ ቢሯቸው ቅጽር በተሰበሰቡ ጋዜጠኞች ፊት ‹‹ጥቃት እና መፈንቅለ ህግ-መንግስት!›› ሲሉ ጠርተውታል፡፡

‹‹ያወሳሰኑን ሁኔታ ምክንያት አድርገን እኛ ጥቃት ብለን እንጠራዋለን፡፡ መፈንቅለ ህገመንግስት ብለን እንጠራዋለን፡፡ ሁሉም የኡጋንዳ ዜጎች በማናቸውም ጊዜ ለህገ መንግስቱን ተገን መሆን መብት እና ግዴታው አላቸው፡፡ በተለይም ደግሞ ህገ መንግስቱን ለማስወገድ የሚጥር ማንኛውንም ግለሰብ ወይንም የግለሰቦች ስብስብ የመገዳዳር መብትና ግዴታ አለባቸው›› ነው ያሉት፡፡

Uganda Präsident Yoweri Museveni
ምስል picture-alliance/dpa/I. Langsdon

በሀገሪቱ ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ የሲቪል ማህበራት እና ረድኤት ድርጅቶችም የአሁኑን ርምጃ ተችተዋል፡፡ በህግ ማሻሻያው ረቂቅ ላይ የኡጋንዳ ፓርላማ ድምጹን ከመስጠቱ አስቀድሞ ባሉ ጊዜያት ርምጃው ለሀገሪቱ እንደማይበጅ በመገናኛ ብዙሃን ብቅ እያሉ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል፡፡ ዊኒ ባይናይማ የኦክስፋም ኢንተርናሽናል የጋንዳ ቅርንጫፍ ኃላፊ ናቸው፡፡ ‹‹ለሀገራችን  መልካም አይደለም፡፡ ለኢኮኖሚያችንም መልካም አይደለም፡፡ ምክንያቱም በሀገሪቱ መጻኢ ሁኔታ ላይ አይገመቴ ጫና ይፈጥራልና›› ብለዋል ኃላፊዋ፡፡

የሀገሪቱን ህገመንግስት አንቀጽ 103 ለማሻሻል ድጋፍ ያገኘውረቂቅ እንደ ህግ በስራ ላይ የሚውለው የ73 ዓመቱ የሀገሪቱ ፕሬዜዳንት ዮዌሪ ካጉታ ሙሰቬኒ ፊርማቸውን ሲያሰፈሩበት ነው፡፡

ሀብታሙ ስዩም

ነጋሽ መሐመድ