የዩጋንዳዉ አማጺ ቡድን መሪ ችሎት | አፍሪቃ | DW | 06.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የዩጋንዳዉ አማጺ ቡድን መሪ ችሎት

ዩጋንዳዊዉ ዶሚኒክ ኦንግዌን ራሱን የጌታ ተከላካይ ጦር (Lord's Resistance Army) በሚል የሚጠራዉን ሽምቅ ተዋጊ ቡድን መሪ ነበር።  በመካከለኛዉ አፍሪቃና በታላላቅ ኃይቅ አዋሳኝ አገሮች አካባቢ የሚንቀሳቀሰዉ ይህ ሽምቅ ተዋጊ ጦር ዶሚኒክ ኦንግዌንን ገና በለጋ እድሜዉ ነበር አፍኖ ወስዶ የጦሩ አባል እንዲሆን የመለመለዉ።

ዶሚኒክ ኦንግዌን ዴንሃግ ችሎት ላይ

ዶሚኒክ ኦንግዌን ዴንሃግ ችሎት ላይ

 

ኦንግዊን በዘ ሄግ ኔዘርላንድስ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት  በተጀመረው ችሎት ቀርቦ በስብዕና አንፃር ፈፅሞታል በሚል የተመሰረተበትን ክስ በጠቅላላ ውድቅ አድርጓል። ዋና ከሚባሉት የ(Lord's Resistance Army አማፂ ቡድን መሪዎች  አንዱ የነበረዉ የዶሚኒክ ኦንግዌን ችሎት ምናልባትም ለብዙ ዓመታት እንደሚዘልቅ ተገምቷል።

ዛሬ ኔዘርላንድ ዴንሃግ በሚገኘዉ የጦር ወንጀለኛ ተመልካች ፍርድ ቤት ችሎት የቆመዉ ዩጋንዳዊዉ የቀድሞ የሕጻን ጦረኛና የአማጺ ቡድን መሪ ዶሚኒክ ኦንግዌን  እስከዛሬ ታይቶ በማይታወቅ በተባለ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ በተቃጣ ከፍተኛ ጥቃትና ጦር ወንጀለኝነት የክስ ሂደቱ  ጀምሮአል።  ዶሚኒክ ኦንግዌን  የክስ መዝገብ 70 የጦር ወንጀል ክስ እንደተካተተበትም ተነግሮአል። 

ጌታ ተከላካይ ብሎ ራሱን የሚጠራዉ ቡድን ዋና መሪ ጆሴፍ ኮኒን

ጌታ ተከላካይ ብሎ ራሱን የሚጠራዉ ቡድን ዋና መሪ ጆሴፍ ኮኒን

ዶሚኒክ ኦንግዌን  በሚል ስሙ የሚጠራዉ የቀድሞ አማፂ ቡድን መሪ በርግጥ ርግጠኛ ስሙ መሆን አለመሆኑ የሚታወቅ ነገር የለም። የ 10 ምናልባትም የ 12 ዓመት አዳጊ ሕጻን ሳለ ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ መንገድ ላይ ሳለ ነበር ፤ራሱን የጌታ ተከላካይ ጦር (Lord's Resistance Army)በሚል የሚጠራዉ አማጺ ቡድኑ አፍኖ የወሰደዉ። በዚያን ጊዜ ለአማጺ ቡድኑ ስሙ ዶሚኒክ ኦንግዌን እንደሚባል ተናገረም ። የትዉልድ ስፍራዉንም ቢሆን ደብቆ ከተያዘበት ቦታ በጣም በብዙ ኪሎሜትር ርቆ ከሚገኘዉ ገጠር እንደመጣ ነበር  የተናገረዉ።  1980 ዎቹ ዓመታት በሰሜናዊ ዩጋንዳ የሚኖሩ ወላጆች ልጆቻቸዉ ምናልባት በአማቺ ቡድን ከወደቁ  ለዉጠዉ እንዲናገሩ ነበር የሚያስተምሩዋቸዉ።  በዝያ ወቅት ራሱን የጌታ ተከላካይ ጦር በሚል የሚጠራዉ አማጺ ቡድን በሰሜናዊ ዩጋንዳ ከፍተኛ ግድያና ቃጠሎ ያካሂድ ነበር። የእዚህ አማጺ ቡድኑ መሪ ጆሴፍ ኮኒ በዓለማችን በከፍተኛ ፍለጋ እየታደኑ ካሉ ወንጀለኞች መካከል የመጀመርያዉ አንዱ ነዉ። ይህ አማጺ ቡድን በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናትን የጎልበትና የጾታ ጥቃትና ብዝበዛ ፈጽሞአል፤ ሕጻናትን ለዉግያ መልምሎአል። ቡድኑ ለዉትድርና የመለመላቸዉን ሕጻናት አብዛኛዉን ጊዜ በገዛ መኖርያ ቀያቸዉ ቤተጠመዶቻቸዉን እንዲገድሉና፤ አልያም እንዲያዋክቡ  ይሰማሩ ነበር። በዚህም ሕጻናቱ ዘሰሩት ወንጀል ሃፍረት ወደቤታቸዉ እንዳይመለሱ ያደርጋሉ። 

« የተወሰኑ ሰዎች የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አኗኗራቸዉ ተቃዉሶአል። እጃቸዉ የተቆረጡ አሉ። መተዳደርያቸዉን አጥተዋል ወላጅ አልባም የሆኑ አሉ። »

«ከፈጣሪ ትዕዛዝ ተሠጥቶኛል፤ የዚህ ህዝብ መተዳደሪያም አስርቱ ቃላት መሆን አለበት” በሚል ማወናበጃ መርህ የጌታ ተከላካይ ጦር በሚል የሚንቀሳቀሰዉና በጆሴፍ ኮኒ ይመራ የነበረዉ አማጺ ቡድን በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድሎአል፤ ከሁለትሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን አፈናቅሎአል።  በጎርጎረሳዉያኑ 2004 ዓ,ም በዶሚኒክ ኦንግቪን ይመራ የነበረ ጦር  በሰሜናዊ ዩጋንዳ ሉኮዲ መንደር በነበረ የስደተኞች መጠለያ ጣብያ የግፍ ጭፍጨፋን አድርሰዉ ከ 60 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ይህ ከተከሰተ ከሁለት ዓመት በኋላ የዩጋንዳ ጦር አማጺ ጦሩን ከሃገሪቱ ለማባረር በቃ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አማጺ ቡድኑ በተደጋጋሚ ከፍተኛ ሽንፈት ቢገጥመዉም አሁንም በዴሞክራቲክ ኮንጎ በደቡብ ሱዳን በማዕከላዊ አፍሪቃ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። 

ዶሚኒክ ኦንግዌን እንደተያዘ

ዶሚኒክ ኦንግዌን እንደተያዘ

በጎርጎረሳዉያኑ 2005 ዓ,ም ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ተመልካች ፍርድ ቤት የጌታ ተከላካይ ብሎ ራሱን የሚጠራዉ ቡድን ዋና መሪ ጆሴፍ ኮኒን ፤ እንዲሁም ዶሚኒክ ኦንጌዌን ጨምሮ አራት ተከታዮቹን የቡድኑን መሪዎች እንዲያዙ ሲል የእስር ማዘዣ አወጣ።  ዩኤስ አሜሪካ በበኩልዋ እነዚህን የአማፅያን ይዞ የሰጠ አምስት ሚሊዮን ዶላር ወረታ እንደምትሰጥ ገለፀች። ከሁለት ዓመት በፊት በጎርጎረሳዉያኑ 2015 ዓ,ም መጀመርያ በማዕከላዊ አፍሪቃ የሚገኙት የሴሊካ አማጽያን ዶሚኒክ ኦንግዌን ይዘዉ ለአሜሪካዉያኑ ወታደሮች አስረከቡ።  ኦንግዌን ከጥቂት ቀናት በኋላ ዴንሃግ ኔዘርላንድ ወደሚገኘዉ ወደ ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት ተላልፎ ተሰጠ። ዶሚኒክ ኦንግዌን በሴሊካ አማፅያን እንደተያዘ አንድ የማዕከላዊ አፍሪቃ አንድ የራድዮ ጣብያ ላቀረበለጥ ቃለ-መጠይቅ እንደተናገረዉ የጌታ ተከላካይ እያለ የሚጠራዉ የአማፂ ቡድን ዋና መሪ ጆሴፍ ኮኒ ሊገለዉ ይፈልጋል።  

« ስሜ ዶሚኒክ ኦንግዊን ይባላል። ከጫካ ወጥቼ ለአሜሪካን ልዩ መከላከያ ኃይል ለመስጠት የወሰንኩት ጆሴፍ ኮኒ እኔን ለመግደል በመፈለጉ ነዉ»

በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኛ ተመልካች ፍርድ ቤት ዛሬ ችሎቱ የጀመረዉና በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ከፍተኛ የግፍ ጭፍጨፋና በማድረስ በጦር ወንጀለኝነት ክስ የተመሰረተበት የቀድሞ የአማፂ ቡድን መሪ  ዩጋንዳዊዉ ዶሚኒክ ኦንግዌን የፍርድ ሂደት ምናልባትም ረጅም ዓመታት ሳይወስድ እንደማይቀር ተመልክቶአል። 

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ