የዩጋንዳና የተቃውሞው ወገን | አፍሪቃ | DW | 24.07.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የዩጋንዳና የተቃውሞው ወገን

በዩጋንዳ ታዋቂው የተቃውሞ ወገን መሪ ኪዛ በሲግዬ ፣ ህገ ወጥ የፖለቲካ ስብስባ በአደባባይ ሊያካሂዱ ሳያቅዱ አልቀሩም በሚል ጥርጣሬ ከተያዙ ወዲህ፣ ዛሬ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ። የዩጋንዳ የተቃውሞ ወገኖች፤ ባለፉት ሳምንታት የፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒን

አገዛዝ በመቃወም የራሳቸውን ፖለቲካዊ ትግል በማጠናከር ላይ የሚገኙ ሲሆን ፤ ፖሊስ በፊናው፤ በሲግዬንና ሌሎች የተቃውሞ ወገን መሪዎችን እንደገና በድንገተኛ እርምጃ እየያዘ ማሠሩን ተያይዞታል። ከትናንት በስቲያ በዋስ የተለቀቁት በሲግዬ ዛሬ ፍርድ ቤት ለመቅረብ ቀጠሮ ተሰጥቶአቸዋል። ስለ ዩጋንዳ የተቃውሞው ወገን ትግልና ፈተና ተክሌ የኋላ ተከታዩን ዘገባ አጠናቅሯል።

ሥልጣን ከጨበጡ 27 ዓመት ሆናቸው፤ ገና በቃኝ አላሉም። የተቃውሞው ወገን የሲቭልና የፖለቲካ መብቶች እንዲጠበቁ ፤ መልካም አስተዳደር እንዲገነባ በሚያሳስበት ጊዜ ፣ ያልሆነ ትርጓሜ እንደሚሰጠው የፖለቲካና የሰብአዊ መብት ታዛቢዎች ይገልጻሉ። የዶቸ ቨለው የአንግሊዝኛው ክፍል ባልደረባ አያዛክ ሙጋቢ፣ ሄንሪ ካሳካህ የተባሉትን ዩጋናዳዊ ነጻ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ፣ የተቃውሞው ወገን ፕሬዚዳንቱ ሥልጣናቸውን ይለቁ ዘንድ በህግ ለማስገደድ ያለው ጥንካሬና ኅብረት እስከምን ድረስ እንደሆነ ጠይቆአቸው ተከታዩን መልስ ነበረ ያገኘው።

«በአሁኑ ጊዜ የተቃውሞው ወገን፤ ፕሬዚዳንቱን ከሥልጣን እንዲወገዱ ለማድረግ ወይም ሊወገዱ በሚችሉበት ህጋዊ ሂደት ላይ ያተኮረ አይመስለኝም። የተቃውሞው ወገን ፣ እስከሚቀጥሉት 5 ዓመታት ባለበት ይዞታ የሚቆይ ይመስለኛል። ዋና ትኩረታቸው ለቀጣዩ ምርጫ ሰፊ ዝግጅት ማድረግ ነው። ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን በሚነሡበት ሁኔታ ያወጡት እቅድም ሆነ የሚወስዱት እርምጃ ያለ አይመስልም። በሃገሪቱም፤ ይህን ርእሰ-ጉዳይ በማድረግ ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን እንዲነሱ ውይይት አልተካሄደም። አሁን ወደ ፍርድ ቤት የሄዱት ወገኖች፤ የአንድን ሚንስትር ሹመት በመቃወም እንጂ ፤ ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን ይውረዱ! ለማለት አይደለም።»

ዮዌሪ ሙሴቬኒ ፤ እ ጎ አ በ 1986 ሥልጣን ከጨበጡበት ጊዜ አንስቶ በቀጣዮቹ ዓመታት ሃገሪቱን በማረጋጋትና የዕድገት ፈርም በማስያዝ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃም ማለፊያ ሥም አትርፈው ነበር። ይሁንና፣ የተቃውሞ ወገኖች እንደሚያማርሩት፤ ፕሬዚዳንቱ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የፈላጭ ቆራጭነት አባዜ ተጠናውቶአቸዋል። ቀድሞ የሙሴቬኒ ተጓዳኝ የነበሩት ታዋቂው የተቃውሞ ወገን ፖለቲከኛ ኪዛ በሲግዬ ዛሬ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ። የአንድ ሚንስትር ሹመትም ክስ አስከትሏል፤ ታዲያ የዩጋንዳ ፍርድ ቤቶች

የቱን ያህል ነጻ ናቸው ከአድልዎም ሆነ ተጽእኖ እስከምን ድረስ የጸዱ ናቸው? ነጻ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ ሄንሪ ካሳክ---

«የዩጋንዳ ፍርድ ቤቶች፤ በአመዛኙ ከአድልዎ ነጻ ሆነው ሲሠሩ የቆዩ ናቸው። ያሳለፏቸው ብይኖች ለዚህ ወይ ለዚያኛው ወገን ሳይሆን፣ በትክክል ፍርድ መፍረዳቸው ነው የሚነገርላቸው። ዩጋንዳውያንንም ሆነ ቀሪውን ዓለም ያስደመሙበት ሁኔታም ነበረ። ፍርድ ቤቶቹ፣ አድልዎ ይፈጽማሉ ብዬ እንደጠራጠር የሚያደርግ ምክንያት አይታየኝም። ከዚህ ቀደም ህገ-መንግቱን ተመርኩዘው ብይን ሰጥተዋል። ህዝቡም ማለፊያ ተግባር ማከናወናቸውን ነው የሚያውቀው።»

የዩጋንዳ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ድርጅት (HRW)ከዛ በሲግዬ በየጊዜው እየተያዙ የሚታሠሩበትን ሁኔታ በመንቀፍ ድርጊቱ፤ የሀገሪቱን የዴሞክራሲ ግንባታ የሚያደናቅፍ ነው በማለት ይተቻሉ። መንግሥት በፊናው የተቃውሞ ወገኖች በአገሪቱ ምሥቅልቅል እንዲያጋጥም ይሻሉ እያለ ሲከስ ይሰማል።

«ይህ በእርግጥ የዐረቡ ዓለም ህዝባዊ የለውጥ እንቅሥቃሴ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየጊዜው ሲናፈስ የቆዬ የፈጠራ ክስ ነው። የሲቭሎች መብት መጠበቅ የሌሎችን ለመጋፋት ይውላል የሚለው ዘይቤ ያለማቋረጥ ሲያነጋግር የቆዬ ጉዳይ ነው። መንግሥት ፤ የተቃውሞው ወገን፤ ህግን ለመጣስና ሥርዓትን ለማናጋት ነው የሚፈልገው ባይ ነው። ዩጋንዳውያን ይህን ጉዳይ በጥሞና በማንሥት፤ የሚነጋግሩበት ነጥብ ነው። የሲቭልና የፖለቲካ ነጻነት ሳይገፈፉ፣ ህግን አክብሮ መኖር ተገቢ ነውና!አንዳንዴ፤ የሲቭልና የፖለቲካ መብቶች እንዲከበሩ ሲጠዬቅ፤ ከመንግሥት በኩል፣ ፀጥታን የሚያደፈርስ ሁኔታ ሊፈጠር ነው የሚል ዘይቤ መሰማቱ፤ የቱን ያህል የተዛባ አተረጓጎም እንደሚሰጥ ነው የሚያስረዳን።»

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic