የዩክሬን ጦርነትና ዲፕሎማሲ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 21.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የዩክሬን ጦርነትና ዲፕሎማሲ

የኪየቭ ሞስኮዎች መወነጃጀል፤ የሞስኮ ዋሽግተን-ብራስልሶች መወጋገዝ፤ መበቃቀልም እንደናረ ነዉ።፤ በዚሕ መሐል የፈረሰዉ የሠላም ዉል ገቢር ይሆናል ብሎ ማሰብ አንዳዶች እንደሚሉት የዋሕነት ነዉ።ዩንግ ግን ሌላ ምርጫ የለም ባይ ናቸዉ።

የዩክሬን የርስ በርስ ጦርነት የሚቆምበትን ብልሐት ለማፈላለግ የራስዋ የዩክሬን፤ የሩሲያ፤ የፈረንሳይና የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ዛሬ በርሊን ዉስጥ ይወያያሉ።በጀርመን ጋባዥነት የሚደረገዉ የአራቱ ሐገራት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ዉይይት ተፋላሚ ሐይላት ሌላዉ ቢቀር ከባድ የጦር መሳሪያዎቻቸዉን ከምሥራቃዊ ዩክሬን እንዲያነሱ ለማግባባት ያለመ ነዉ።የዩክሬን መንግሥት እና የምሥራቃዊ ዩክሬን የሸመቁ አማፂያንን የምትረዳዉ የሩሲያ ባለሥልጣናት ዉዝግብ ግን እንደቀጠለ ነዉ።የሩሲያና የምዕራባዉያን ጠብም የመርገብ ምልክት አላሳየም።ምሥራቃዊ ዩክሬንን በተለይም ዶኔትስክን የሚያወድመዉ ዉጊያም አላባራም።

ለዲፕሎማሲዉ ወግ-ይሁን፤ጊዜ ለመግዛት፤ ወይም ለእዉነኛ ሠላም ፍለጋ ዉይይት፤ ድርድሩ ደንበር፤ገተር፤ ቆም-ራመድ እንዳለ ቀጥሏል። ዉጤት ግን ዜሮ።ዛሬ ማታ በርሊን የሚሰበሰቡት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ዉይይትም ከእስከዛሬዉ የተለየ አይደለም።በሩሲያ የጀርመን ልዩ መልዕክተኛና የቀድሞዉ የጀርመን መከላከያ ሚንስትር ፍራንስ ዮሴፍ ዩንግ ግን ተስፋ አላቸዉ።

«ተስፋ አለኝ።ዛሬ ማታ አንድ ርምጃ ወደፊት እንራመዳለን የሚል ተስፋ።ሁኔታዉ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ከሚችሉት በላይ ነዉ።ይሕ (ሁኔታዉን መለወጥ) ከተገንጣዮቹ ጎን ለቆሙትም አስፈላጊ ነዉ ብዬ አምናለሁ።እዚያ ለሚኖሩት ሰዎች ጦርነት ያስከተለዉ ጠብ እንዲቆም አጥብቀዉ ይመኛሉ።በዚሕም ምክንያት ዛሬ ማታ ተኩስ ለማቆም የሚረዳ ሁነኛ እርምጃ ይወሰዳል የሚል ተስፋ አለኝ።ተስፋ ብቻ ነዉ የማደርገዉ።»

ዶኔትስክ ግን እየጋየች ነዉ።በተለይ አዉሮፕላን ማረፊያዋ።እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ1985 ስቲግ የተሰኘዉ የብሪታንያ የሮክ ሙዚቃ ጓድ «በጦርነት አሸናፊ የለም» እያለ ያቀነቀነዉ ዘፈን የያኔዉን የምዕራብም፤የምሥራቃም ሙዚቃ አፍቃሪ ልብ ሠርቆ ነበር።የሙዚቃዉ ደራሲ የሶቬት ሕብረቱ ሰርጌይ ፕሮኮፍየቭ ነበር።ከዩክሬን ዘመናዊ መታወቂያዎች አንዱ የነበረዉ የዶኔትስክ አዉሮፕላን ማረፊያ በዚያ የሙዚቃ አዋቂ ሥም ነበር-የተሰየመዉ።ፕሮኮፍየቭ።

ከሠላሳ ዓመት በኋላ ዘንድሮ-ዘንድሮ፤ የተቦዳደሱ ሕንፃዎች፤የተመነቃቀሩ የብረት ዘንጎች፤የከሠሉ ቁሳቁሶች ካገጠጡበት፤ከትቢያ-ክምሩ-አዉሮፕላን ማረፊያ ሥም ጋር የዜማ ደራሲዉ ሥም ዳግም በጦርነት ሰበብ ናኘ።

በምዕራባዉያን የሚደገፈዉ የዩክሬን መንግሥትና በሩሲያ የሚረዱት የምሥራቅ ዩክሬን አማፂያን ባለፈዉ መስከረም ተኩስ አቁም ሲዋዋሉ ብዙ የተነገረ-የተዘፈነለትን«በጦርነት አሸናፊ የለም» ብሒልን እዉነትነት የተቀበሉ መስለዉ ነበር።መምሰል በርግጥ መሆን አይደለም።

ጀርመናዊ ፖለቲከኛ ፍራንስ ዮሴፍ ዩንግ እንደሚሉት ግን ዛሬ ማታ በርሊን ላይ የሚሰበሰቡት የመሠለዉን ለማድረግ፤የፈረሰዉን ዉል ለማፅናት ልዩ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል።

«የተኩስ አቁም ዉሉ በትክክል ገቢር እንዲሆንና የጠመንጃዉ ላንቃ እንዲዘጋ፤ የሚንስኩ ሥምምነት ገቢር እንዲሆን የምንችለዉን ሁሉ ማድረግ፤ በዛም አስፈላጊ ነዉ ብዬ አምናለሁ።ምክንያቱም ይሕ ስምምነት የዩክሬን፤የሩሲያ፤የአዉሮጳ የፀጥታና ትብብር ድርጅት በሙሉ የተቀበሉት ነዉ።ሥለዚሕ ሥምምነቱ አሁን በስተመጨረሻዉ ገቢር እንዲሆን የሚቻለዉ ሁሉ መደረግ አለበት።»

ምሥራቃዊ ዩክሬንን የሚያወድመዉ ጦርነት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ ከ4500 በላይ ሰዉ ፈጅቷል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠር አቁስሏል፤ ብዙ ሺዎችን አሰድዷል።በቢሊዮን ዩሮ የሚቆጠር ንብረት አጥፍቷል።ጦርነቱ የሩሲያና የምዕራቦችን «ወዳጅነት» ወደ ጠብ ቀይሮ በማዕቀብ ቅጣት፤ አፀፋ ቅጣት እያበቃቀለ ነዉ።

አንዳቸዉም ከየተፃራሪ አቋማቸዉ ፈቅ አላሉም።የዩክሬን መንግሥት ተጠባባቂ ጦሩ እንዲከት አዟል።የኪየቭ ሞስኮዎች መወነጃጀል፤ የሞስኮ ዋሽግተን-ብራስልሶች መወጋገዝ፤ መበቃቀልም እንደናረ ነዉ።፤ በዚሕ መሐል የፈረሰዉ የሠላም ዉል ገቢር ይሆናል ብሎ ማሰብ አንዳዶች እንደሚሉት የዋሕነት ነዉ።ዩንግ ግን ሌላ ምርጫ የለም ባይ ናቸዉ።ሁሉም ሐላፊነቱን መወጣት አለበት።

«ሁለቱም ወገኞች ዉላቸዉን ማክበር አለባቸዉ።መጀመሪያ ተኩስ ማቆም አለባቸዉ።ሁለተኛ የሚኒስኩ ሥምምነት ከነ ሙሉ ትርጉሙ ገቢር መሆን አለበት።ይሕ ማለት በሥምምነቱ የተዘረዘሩት ባካባቢዉ የራስ ገዝ አስተዳደር መመሥረት፤ ምርጫ መደረግ፤የነዋሪዎቹ የሠብአዊ መብት ይዞታ መሻሻል አለበት።»

እንዴት ከዚያ ይደረሳል?

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ