የዩክሬን አውሮፕላን በስህተት በሚሳይል መመታቱን ኢራን አመነች | ዓለም | DW | 11.01.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የዩክሬን አውሮፕላን በስህተት በሚሳይል መመታቱን ኢራን አመነች

አውሮፕላኑ በዋና ከተማዋ ተሒራን ከሚገኝ ማረፊያ እንደተነሳ አቅጣጫውን የአገሪቱ ጦር ንብረት ወደሆነ እና ከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ ወደሚደረግበት ወታደራዊ የጦር ሰፈር ማዞሩን እና ተምዘግዛጊ ሚሳይል ሳይሆን አይቀርም በሚል ጥርጣሬ መመታቱን የኢራን አብዮታዊ ዘብ አስታውቋል።

ከተሒራን እንደተነሳ 176 ሰዎች ጭኖ የተከሰከሰው የዩክሬን አውሮፕላን "በሰው ስህተት" በሚሳይል መመታቱን ኢራን አመነች።  ባለፈው ረቡዕ ማለዳ ከኢማም ኾሚኒ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በረራ የጀመረው የዩክሬን አውሮፕላን በሰው ስህተት በተተኮሰ ሚሳይል መመታቱ በምርመራ መረጋገጡን የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሓሳን ሩኻኒ ገልጸዋል። ፕሬዝዳንቱ የሰባት አገራት ዜጎች ሕይወት የቀጠፈውን አደጋ "ይቅርታ የማያሰጥ ስህተት" ብለውታል።

የአገሪቱ ጦር አውሮፕላኑ በዋና ከተማዋ ተሒራን ከሚገኝ ማረፊያ እንደተነሳ አቅጣጫውን የኢራን አብዮታዊ ዘብ ንብረት ወደሆነ እና ከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ ወደሚደረግበት ወታደራዊ የጦር ሰፈር ማዞሩን እና ተምዘግዛጊ ሚሳይል ሳይሆን አይቀርም በሚል ጥርጣሬ መመታቱን አስታውቋል።

የዩክሬን ዓለም አቀፍ አየር መንገድ በበኩሉ በዛሬው ዕለት አውሮፕላኑ ከተሒራን አውሮፕላን ማረፊያ ሲነሳ ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ እንዳልተሰጠው ገልጿል። ብርጋዴየር ጄኔራል አሚራሊ ሐጂዛዴህ የተባሉ የኢራን አብዮታዊ ዘብ የጦር አዛዥ አውሮፕላኑን መቶ የጣለው የሚሳይል ተቆጣጣሪ የመረጃ ልውውጥ በመቋረጡ ምክንያት እርምጃውን በግሉ መውሰዱን በዛሬው ዕለት ተናግረዋል።

ጉዳዩ በትናንትናው ዕለት የተነገራቸው የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አሊ ኻሚኒ ከጸጥታ ጥበቃ ባለሥልጣናት ጋር ካደረጉት ውይይት በኋላ መረጃው ይፋ እንዲሆን መወሰናቸውን ፋርስ የተባለው የኢራን መንግሥት የዜና ወኪል ዘግቧል።

ብርጋዴየር ጄኔራል አሚራሊ ሐጂዛዴህ "ሙሉ በሙሉ ኃላፊነት እወስዳለሁ። ውሳኔውንም በጸጋ እቀበላለሁ" ብለዋል። "አደጋው የተፈጠረው የመረጃ ልውውጥ እንከን ከገጠመ በኋላ ነው። ይህ ግን ምንም ምክንያት አይሆንም። ይቅር የማይባል ስህተት ነው" ያሉት የጦር አዛዡ "እንዲህ አይነት ክስተት ሲፈጠር ከማይ ብሞት እመርጣለሁ" ብለዋል።

Iran 2019 | General Amir Ali Hajizadeh, Revolutionsgarden (Getty Images/AFP/A. Kenare)

ብርጋዴየር ጄኔራል አሚራሊ ሐጂዛዴህ

የጦር አዛዡ እንዳሉት ከተሒራን አውሮፕላን ማረፊያ የተነሳው ቦይንግ 737 አውሮፕላን ተምዘግዛጊ ሚሳይል ይሆናል ብሎ የተሳሳተው የአብዮታዊ ዘብ አባል ከውሳኔ ለመድረስ ያሉት አስር ሰኮንዶች ነበሩ።

አውሮፕላኑ የመከስከሱ ዜና ከመሰማቱ ቀደም ብሎ ኢራን የሜጀር ጄኔራል ቃሲም ሶሌይማኒ ግድያን ለመበቀል በኢራቅ የአሜሪካ ወታደሮች የተለጠለሉባቸውን ሁለት የጦር ሰፈሮች ደብድባለች። ኢራን ባለፉት ቀናት አውሮፕላኑ በሚሳይል ሳይመታ አልቀረም የሚሉ መረጃዎችን ስታጣጥል ቆይታለች።

ከተሒራን ወደ ዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ ለመጓዝ መንገድ የጀመረው ቦይንግ 737-800 NG  አውሮፕላን በደረሰበት አደጋ 176 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በአደጋው 86 ኢራናውያን፤ 63 ካናዳውያን፤ 11 ዩክሬናውያን፤ 10 ስዊድናውያን፤ 4 አፍጋኒስታናውያን፤ 3 ጀርመናውያን እና 3 ብሪታኒያውያን መገደላቸውን የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ቫዲም ፕሪስታይኮ አረጋግጠዋል።

የአየር በረራ መረጃዎች የሚያቀርበው ፍላይት ራዳር 24 (FlightRadar24) እንዳለው ረቡዕ ማለዳ ከኢማም ኾሚኒ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በረራ የጀመረው አውሮፕላን መረጃ ወደ መላክ ያቆመው ወዲያውኑ ነበር።

የዩክሬን ዓለም አቀፍ አየር መንገድ እንዳለው የተከሰከሰው አውሮፕላን ቦይንግ 737-800 NG የተባለ ሞዴል ሲሆን በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም ተመርቶ በቀጥታ ከአምራቹ ለአየር መንገዱ የቀረበ ነበር።