የዩክሬን ቀውስና የጄኔቩ ስብሰባ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 17.04.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የዩክሬን ቀውስና የጄኔቩ ስብሰባ

ይህ የአራትዮሹ ንግግር ለዩክሬን ቀውስ ምን ዓይነት መፍትሄ እንደሚያስገኝ ከወዲሁ መገመት ቢያዳግትም ቢያንስ ዩክሬንና ሩስያን የዩክሬን ቀውስ ከተባባሰ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ላይ እንዲወያዩ በማድረጉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ።

ደቡብ ምሥራቅ ዩክሬን ዉስጥ በሩሲያ ወገንተኞችና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተካሄደ ግጭት ሶስት ተገድለዉ 13 ቆሰሉ። የዩክሬን የሀገር ዉስጥ ሚኒስቴር እንዳመለከተዉ በግጭቱ 300 ያህል ሰዎች ተሳትፈዋል። ጊዜያዊ የሀገር ዉስጥ ሚኒስትር አርሰን አቫኮቭ ትናንት ሌሊት የዩክሬን የጸጥታ ኃይሎች በሰፈሩበት ላይ ጥይት መተኮሱን ጓዳ ሠራሽ ፈንጂም መወርወሩ ገልጸዋል። በስፍራዉ የነበሩ ዘቦች የማስጠንቀቂያ ተኩስ በማስቀደም የተኩስ ምላሽ ሰጥተዋል። ዘቦቹ በልዩ ኃይሎችና ሄሊኮፕተር መታገዛቸዉንም ጨምረዉ አመልክተዋል። ዛሬ ጄኔቫ ላይ የሩሲያን ጨምሮ የዩክሬን፣ ዩናይትድ ስቴትስና የአዉሮጳ ኅብረት ዲፕሎማቶች የተባባሰዉን ዉጥረት ለማርገብ ይነጋገራሉ። የዩክሬን ጊዜያዊ የሀገር ዉስጥ ሚኒስትር በጉባኤዉ ላይ ሀገራቸዉ የምታቀርበዉ ጥያቄ ግልፅ እንደሆነ አመልክተዋል።

«በጉባኤዉ ላይ አቋማችን ግልፅ ነዉ። ሩሲያ ባጠቃላይ በምስራቃዊ ዩክሬን ግዛቶች የአሸባሪነት ተግባራትን እንድታቆም እንጠይቃለን።»

ምዕራቡ ዓለም የዛሬዉ የዲፕሎማቶች ድርድር ከመካሄዱ አስቀድሞ ሩሲያ ላይ ግፊት እያደረገ ነዉ። የኋይትሃዉስ ቃል አቀባይ ሀገራቸዉ አዲስ ማዕቀብ ለመጣል መዘጋጀቷን ተናግረዋል። የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን NATO በበኩሉ ምሥራቅ አዉሮጳ ዉስጥ የመከላከያ ኃይሌን አጠናክራለሁ ብሏል። ሞስኮ የኪየቭ መንግስት ወታደሮችና የጦር መሳሪያ ወደስፍራዉ ከመላክ ይልቅ ከሩሲያኛ ተናጋሪዉ ኅብረተብ ጋ እዉነተኛ ዉይይት ማካሄድ ይኖርበታል እያለች ነዉ። ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በቴሌቭዥን ባካሄዱት ቃለ መጠይቅም የዩክሬን ቀዉስ ከተቀጣጠለበት ጊዜ አንስቶም ሩሲያ ጣልቃ የገባችበት ሁኔታ የለም ብለዋል።

«ይህ መሠረተ ቢስ ነዉ። ምሥራቅ ዩክሬን ዉስጥ የሩሲያ ወታደሮች፣ የስለላ ሠራተኞች፣ እንዲሁም ወታደራዊ አማካሪዎች የሉም። ንቅናቄዉ የሚካሄደዉ እዚያዉ በስፍራዉ በሚገኙ ኗሪዎች ነዉ። ለዚህ ማረጋገጫዉም ፊታቸዉን ሳይሸፍኑ የሚታዩት ሰዎች ናቸዉ። ለምዕራብ ተጓዳኞቼ፤ በሰዎች አናት ላይ መደራደር እንደማይቻል ተናግሬያለሁ። የሀገራቸዉ ባለቤቶች ራሳቸዉ ናቸዉ። ከእነሱ ጋ መነጋገር ያስፈልጋል።»

ፑቲን ሀገራቸዉ ከቀሪዉ ዓለም ተነጥላ እንድትቀር የሚያደርጋት የቀድሞዉ የብረት መጋረጃ ዓይነት እንደማትፈልግ ዛሬ አመልክተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለም ዩክሬን ከ16 እስከ 60 ዓመት የሆነዉ ሩሲያዊ ወንድ ወደሀገሯ እንዳይገባ ማገዷ ተሰምቷል።

የዩክሬን ቀውስ ላይ ዩክሬን ሩስያ አሜሪካንና የአውሮፓ ህብረት ጄኔቭ ስዊዘርላንድ ውስጥ የሚያካሂዱት የአራትዮሹ ንግግር ለዩክሬን ቀውስ ምን ዓይነት መፍትሄ እንደሚያስገኝ ከወዲሁ መገመት ቢያዳግትም ቢያንስ ዩክሬንና ሩስያን የዩክሬን ቀውስ ከተባባሰ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ላይ እንዲወያዩ በማድረጉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ። ስለ ጄኔቩ ስብሰባ የብራሰልሱን ወኪላችንን ገበያው ንጉሴን በስልክ አነጋግረነዋል
ሂሩት መለሰ
ገበያው ንጉሴ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic