የዩክሬን ቀውስና የሩሲያ የነዳጅ ጦርነት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 02.05.2022
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የዩክሬን ቀውስና የሩሲያ የነዳጅ ጦርነት

ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችው ጦርነት ዛሬ ሰኞ 68ኛ ቀኑን አስቆጥሯል። ብርቱ ሰብዓዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ያስከተለው ጦርነት ሰሞኑን ወደ ነዳጅ ግብይት የመሻገር አዝማሚያ እያሳየ ነው። ሩሲያ ለፖላንድ እና ቡልጋሪያ የምታቀርበውን ነዳጅ በሩብል ለመክፈል ፈቃደኛ አልሆኑም በሚል ምክንያት አቋርጣለች። የአውሮፓ ኅብረት ውሳኔውን ነቅፏል

ማኅደረ ዜና፦ የዩክሬን ቀውስና የሩሲያ የነዳጅ ጦርነት

ዩክሬን የኔቶና የአውሮፓ ህብረት ተቋማት አባል ለመሆን የምታደርገውን እንቅስቃሴ ክፉኛ ስትቃወም የቆየችው ሩሲያ የኔቶ መስፋፋት ለህልውናዋ ከባድ ስጋት መደቀኑን በመግለጽ ዩክሬይን ከድርጊቷ እንድትታቀብ ደጋግማ ስታስጠነቅቅ ቆይታለች:: ከዚህ ሌላ የራሳቸውን ግዛት ለመመስረት የሚታገሉት የሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪዎቹ የዶኔስክ እና የሉሃንስክ ሕዝቦች በዩክሬን የጸጥታ ኃይላት የሚደርስባቸው ጥቃትና የመብት ጥሰት እንዲገታና የነጻነት መብታቸው እንዲከበር ፍላጎት እንዳላትም በተለያዩ ጊዜያት ገልጻለች:: በዩክሬይን እያቆጠቆጠ የመጣው የናዚ ርዕዮት አራማጆች እንቅስቃሴም ቢሆን ለቀጣናው ስጋትን ደቅኗል የሚል ምክንያት አላት:: በእነዚህ ሁሉ ሰበቦች የምድር የየብስና የባህር ኃይል እጅግ የተራቀቁ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎቿንና የስፔስ ሳተላይት ቴክኖሎጂዋን ጭምር ተጠቅማ ባለፈው የካቲት 17, 2014 ዓ.ም በዩክሬን ላይ የከፈተችው አስፈሪ ጦርነት 68ተኛ ቀኑን ቢያስቆጥርም ቁልፍ ስትራቴጂካዊ አካባቢዎችንና ወታደራዊ ተቋማትን ለመቆጣጠር የጀመረችው ግስጋሴ እንደ አጀማመሯ የተፋጠነ ሳይሆን ብዙ የሕይወት ዋጋ የሚያስከፍልና መሰናክል የበዛበት እየሆነባት ነው:: እንደ ዩክሬን የመከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ ከሆነ እስካሁን ለዘጠነኛ ሳምንት በዘለቀው ውጊያ ሩሲያ ከስድስት የማያንሱ የጦር ጄነራሎቿን ከ 16 በላይ ከፍተኛ አዋጊ የጦር መኮንኖችንና 16 ሺህ በላይ ወታደሮቿን በምድርና በአየር ጥቃት አጥታለች:: ይህ የከፍተኛ ጦር አመራሮች ግድያ ደግሞ በ 2ተኛው የዓለም ጦርነት በናዚ ጀርመን ላይ ለተገኘው የተጣማሪው ኃይል ድል የአንበሳው ድርሻ አለው የሚባለው የሶቪየት ህብረቱ ቀዩ ጦር ከደረሰበት ኪሳራ በእጅጉ የላቀ ነው ሲሉ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጽሉ:: ሩሲያም በአጸፋው በእስካሁኑ ውጊያ ከ 14 ሺህ የሚልቁ የዩክሬን ተዋጊዎች ተሰውተዋል ባይ ነች:: በዩክሬኑ ፍልሚያ ከፍተኛ ወታደራዊ ኪሳራ እንደደረሰባት ያልሸሸገችው ሩሲያ በሰራዊቷ ላይ ለሽንፈት የሚያበቃ የአጸፋ ጥቃት ደርሶባታል ተብሎ በተለይም በምዕራባውያን ዘንድ እየተነገረ ያለው መረጃና አሃዝ እጅግ የተጋነነ መሆኑን ገልጻ "ሰላምና ደህንነትን ማስከበር" ባለችው የዩክሬኑ ዘመቻዋም "ድል እየቀናኝ" ነው :: አብዛኛዎቹን የዩክሬን አደገኛ የጦር መሳሪያዎችና ወታደራዊ ተቋማትም ዶግ አመድ አድርጌያለሁ" ስትል ትችቱን አስተባብላለች:: ከቀናት በፊት በተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና በስካይ ኒውስ ቴሌቪዥን ለቃለ መጠይቅ በእንግድነት የተጋበዙት የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ኬስኮቭ "ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ አጭር ጊዜ ቢሆነውም ከ 16 ሺህ በላይ ሰራዊት ማጣታችሁ ይነገራል:: በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ታንኮችና አያሌ የጦር ተሽከርካሪዎቻችሁ ወድመዋል:: ፕሬዝዳንት ዘለንስኪንም እንዳሰባችሁት በቁጥጠር ስር ማዋልም ሆነ ከስልጣን ማስወገድ ተስኗችኋል:: እንደውም በተቃራኒው ጦሩን አስተባብረው እየተፋለሟችሁ ነው:: በዚህ ሁኔታ በጦርነቱ እያሸነፍን ነው ለማለት እንዴት ትችላላችሁ? በደቡባዊ ምስራቅ ዩክሬን እንደ ማሪኤፖልና ከ 400 በላይ ነዋሪዎች በሩሲያ ጦር ተገለዋል በተባለው የቡቻ ከተሞች በሰላማዊ ዜጎችና በሲቭል ተቋማት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችም ከባድ ውግዘትና ነቀፌታን ቀስቅሰዋል:: የክሬምሊን አስተዳደር ለዚህስ ምን መልስ አለው? " ተብሎ በቀጥታ ለቀረብላቸው ጥያቄ "ሰላምና ህግ ማስከበር" ባሉት ዘመቻ ሩሲያ ድል እየቀናት መሆኑን የገለጹት ኬስኮቭ በተለይም ከሩሲያ ወታደሮች ሞት ጋር በተያያዘ የሚነሳው ጥያቄ እውነትም ግነትም እንዳለው አልሸሸጉም::

Ukraine Krieg I Kiew

የጦርነት ጠባሳ በኪየቭ

"በእርግጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር ተሰውቶብናል:: ይህ ለእኛ እጅግ አሳዛኝ ክስተት ነው:: አሁንም የሰላም ዕድል አለ ብለን እናምናለን:: በመሆኑም ችግሩን ዘላቂ መፍትሄ በሚያስገኝ መልኩ በድርድር ለመቋጨት የጀመርነውን ጥረት እንቀጥላለን:: ከማሪኢፖልና ሌሎችም ከተሞች ጥቃት ጋር በተያያዙ ለሚነሱ ትችቶች የዩክሬን ተዋጊ ኃይላት ነዋሪውን ሕዝብ የጦር ከለላ አድርገው ትርፍ ለማግኘት የሚፈጽሙት ተግባር ለመሆኑ በግልጽ ሊሰመርበት ይገባል:: በነገራችን ላይ የራስ ገዝ አስተዳደር ጥያቄ ያነሱ የዶኔትስክ ሕዝቦች ከስምንት ዓመታት በላይ በዚህችው በማሪኢፖል በዩክሬይን የጸጥታ ኃይላት አፈና አስከፊ የመብት ጥሰትና ግድያ ሲፈጸምባቸው አንድም አካል ውግዘትና ተቃውሞ አለማሰማቱ በእጅጉ አስገራሚ ነው"  ብለዋል ኬስኮቭ::

ዩክሬንን ለመውረር አቅደዋል በሚል በተደጋጋሚ ሲከሰሱ የቆዩት ፑቲን ውንጀላውን ሲያስተባብሉ ቢቆዩም በመጨረሻ ግን ከዘጠኝ ሳምንታት በፊት ቃላቸውን አፍርሰው ጦራቸውን በአማፂያን ቁጥጥር ስር ወደሚገኙት ሁለቱ የምስራቃዊ ዩክሬን ክልሎች ዶኔስክና ሉሃንስክ እንዲዘምት ዕዛዝ ሰጥተዋል። ሩሲያ ከገነባችው ስምና ካላት እጅግ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ አንጻር ወረራው በጥቂት ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል የሚል ከፍተኛ መላምት ቢኖርም ከዩክሬን ጋር የከፈተችው ፍልሚያ ከዛሬ 14 ዓመታት በፊት በአስራ ሁለት ቀናት እንዳጠናቀቀችው የጆርጂያው ጦርነት ቀላል አልሆነላትም:: እስካሁን በሩሲያ ወረራ ምክንያት አንድ አራተኛው ያህል የአገሪቱ ሕዝብ ማለትም ከ 11 ሚልዮን በላይ ዜጎች መኖሪያ ቀያቸውን ለቀው ሲሰደዱ ከ 299 የሚልቁ ንጹሃንም ሕይወታቸው እንደተቀጠፈ ከእነዚህም ውስጥ ከ 210 በላይ ሕጻናት መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መረጃ ጠቁሟል:: በዚህም ሩሲያ ዓለማቀፍ ውግዘቶችንና ተቃውሞዎችን እያስተናገደች ትገኛለች::

ሩሲያ አሸናፊ የሆነችበት የነዳጅ ጦርነት

ሩሲያ ጎረቤቶቿና ምዕራባውያን ጠላቶቿ ለሚያደርሱባት የተለያየ ተጽዕኖና ማዕቀብ፣ ውሳኔያቸውን አስገድዳ ለማስቀየርና ለማሸበር ሁሌም መቃወሚያና መከላከያ እስካሁን አልተገኘለትም የሚባለውን ከድምጽ የፈጠነ ዘመናዊ የኒውክለር የጦር መሳሪያዋንና የነዳጅ ሃብቷን ወይም ሃይልን እንደ መሳሪያ እየተጠቀመችበት ትገኛለች። የኃይል አቅርቦት በእርግጥም ራሱን የቻለ የጦርነት መሳሪያ ነው።ለዚህም ነው የየፑቲን ጦር ወረራውን እንደጀመረ የዩክሬን የነዳጅ ማጠራቀሚያዎችን፣ የአቅርቦት ሰንሰለቶችንና ማጣሪያዎችን ለይቶ እያነጣጠረ አሰቃቂ ጥቃትና ውድመት በማድረስ ላይ የሚገኘው። እንደ ፖለቲካ ተንታኞች እምነት የጠላት ኃይል የቤንዚን፣ የናፍታ እና የዘይት መዳረሻ መቁረጥ ወታደራዊ የበላይነትን ለማግኘት በተለያዩ ጦርነቶች የተሞከረና ውጤትም ያመጣ የተሻለ ዘዴ ነው።

Ukraine Krieg I Mariupol

በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት የማሪዩፖል ከተማ

የሩሲያው ነዳጅ ላይ ያነጣጠረ ጦርነት አሁን ላይ ከዩክሬን አልፎ ወደ ሌሎች የአውሮጳ ሃገራት ተሸጋግሯል:: ባለፈው ሚያዝያ 18, 2014 ዓ.ም የሩሲያ መንግስት ንብረት የሆነው ግዙፉ የጋዝ ፕሮም ድርጅት የፖላንድና የቡልጋሪያ የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦትን እንዲያቋርጥ ያሳለፈውን ውሳኔ አጥብቀው የተቃወሙት የአውሮጳ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ዴር ላየን "እርምጃው ሩሲያ አስተማማኝ የንግድ ምርት አቅራቢ ላለመሆኗ በቂ ማረጋገጫ ነው" ሲሉም ነቅፈዋል። የኃይል አቅርቦት ማቋረጥ ውጤታማነትን በመረዳት ሩሲያ የውጭ ፖሊሲዋ መሳሪያ አድርጋ ስትጠቀም ረጅም ዓመታት አስቆጥራለች:: ለአብነትም እ.ኤ.አ. በ2009 ዓ.ም ዩክሬንንና አጎራባች የአውሮጳ ሀገራትን የጋዝ ማስተላለፊያ በመዝጋት፣በአስከፊው ብርዳማ የክረምት ወቅት ዩክሬንን ለማንበርከክ ያደረገችው ጥረት የሚጠቀስ ነው። በዚህም ውጤታማ የጋዝ አቅርቦትን የማቀብ ዘዴዋ ኪየቭ ከሞስኮ ጋር የአስር ዓመት የጋዝ ማስተላለፊያ ስምምነትና ሌሎችም ቅናሽ አገልግሎቶችን ለመቀበል ተገድዳለች።ሩሲያ በ 2014 ዓ.ምትም እንዲሁ በክፍያ ውዝግብ ምክንያት ዳግም ተመሳሳይ የጋዝ አቅርቦት እገዳ በዩክሬን ላይ መጣሏ አይዘነጋም:: በጣም አስገራሚው ጉዳይ የአውሮጳ ህብረት ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ለ 23 የአውሮጳ ሃገራት ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዟን በማስተላለፊያ መስመሮች በምታቀርበው ሩሲያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ግፊቱን አጠናክሮ የመጨረሻው የውሳኔ ምዕራፍ ላይ በተቃረበበት በአሁኑ ወቅት በራሱ በሕብረቱ አባል ሃገራት እርምጃው እየተጣሰ መገኘቱ ፑቲንን በነዳጅ የኃይል ጦርነት ያለጥርጥር ለማሸነፋቸው ማረጋገጫ ነው የሚሉ መረጃዎች በስፋት መሰራጨት ጀምረዋል:: ብሉምበርግና ሌሎችም የመገናኛ ብዙሃን በሰሞኑ ዘገባቸው እንዳጋለጡት አራት ግዙፍ የአውሮጳ የጋዝ አቅራቢ ድርጅቶች ከሞስኮ ለሸመቱት ነዳጅ በሩሲያ ሩብል ክፍያ ፈጽመዋል:: የሩሲያው የነዳጅ ኩባንያ ጋዝፕሮም የመረጃ ምንጭ እንደጠቆመው አስር ተጨማሪ የአውሮጳ የነዳጅ ምርት ሸማች ድርጅቶችም ፑቲን ዶላርና ዩሮን አልቀበልም ባሉት መሰረት ክፍያውን በሩብል ለመፈጸም የገንዘብ ዝውውሩ በጋዝፕሮም የባንክ አካውንት የሚፈጸምባቸውን ተጨማሪ የሂሳብ አካውንቶች ከፍተዋል:: ምንም እንኳ ሌሎች ገዢዎች የክሬምሊንን አዲስ ውል ውድቅ ቢያደርጉትም፣ተመሳሳይ አቋም በወሰዱት ፖላንድና 90 በመቶ የተፈጥሮ ጋዝ ከሩሲያ በምትሸምተው ቡልጋርያ ወደ ሃገራቱ የሚደረገው የጋዝ ፍሰት ባለፈው ረቡዕ ከቆመ በኋላ ቀጣዩ ክፍያ እስከሚጠናቀቅበት እስከ ግንቦት አጋማሽ ድረስ ሌሎችም ተጨማሪ ማቋረጦች እንዳይካሄዱ ምስጢራዊ ንግግሮች ከወዲሁ እየተካሄዱ እንደሆነ ነው መረጃዎች ያመለከቱት::

በሩሲያ መንግስት ቁጥጥር ስር ለሚገኘው ጋዝፕሮምባንክ የዩሮ እና የሩብል አካውንቶችን ለመክፈት የቀረበው ዘዴ የማዕቀቡን ውሳኔ እንደሚጥስ የአውሮጳ ህብረት ለአባል ሀገራቱ አሳውቋል። አንዳንድ ዘገባዎችም የጀርመን ነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶችም ከአውሮጳ ህብረት ማዕቀብ ውጪ በዚሁ ለሩሲያ የጋዝ ሽያጭ በሩብል የመክፈል ተግባር ላይ እጃቸው እንዳለበት እየገለጹ ይገኛሉ:: መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የአውሮጳ ሕብረት በዩክሬን ላይ የተፈጸመውን ወረራ ተከትሎ በሩሲያ የነዳጅ የተፈጥሮ ጋዝና የድንጋይ ከሰል ምርቶች ላይ ጠንካራ የግዢ ማዕቀብ እንዲጣልና አባል ሃገራቱም ለውሳኔው ተገዢ እንዲሆኑ ግፊቱን ባጠናከረበት በአሁኑ ወቅት ሩሲያ ከበፊቱ በበለጠ የጋዝና የድንጋይ ከሰል ምርቶቿን በእጥፍ ለአውሮጳና ሌሎችም ሃገራት በነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሮችና በግዙፍ መርከቦች እየቸበቸበች እንደምትገኝ ፋይናንሻል ታይምስና የእንግሊዙ ዘጋርድያን አጋልጠዋል:: "የፑቲንን ጦርነት በገንዘብ መደገፍ" በሚል ምጸት በተሰራጩት በእነዚሁ መረጃዎች ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ባሉት 65 ቀናት ውስጥ ሩሲያ ከ 63 ቢልዮን ዩሮ በላይ የሚተመን ለኃይልና ለኢንዱስትሪ ምርቶች ግብዓት የሚያገለግል የድንጋይ ከሰል ምርቷን የሸጠች ሲሆን ዋና ሸማቾቹም ጀርመን ጣሊያንና ቻይና መሆናቸውን ጠቅሰዋል:: የፕሮግራማችን የዘውትር ተሳታፊ የምጣኔ ሃብትና የፖለቲካ ተንታኙ ዶክተር ጸጋዬ ደግነህ በበኩላቸው "ከሩሲያ ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ ምርት የምትሸምተው ጀርመን በአስገዳጅ ጫና ምክንያት በሩሲያ የነዳጅ አቅርቦት ላይ ማዕቀብ መጣል የለበትም የሚለውን የቀደመ አቋሟን ወደ መቀየር የመጣች ትመስላለች:: የነዳጅና ማዕድናት አቅርቦት ዕቀባ ከተሽከርካሪዎች ሌላ በኢንዱስትሪዎች በንግድና በምርት እንቅስቃሴው ላይ ከባድ እንቅፋትና ችግር የሚፈጥር በመሆኑ የአውሮጳ ጀርመንም ሆነች የአውሮጳ ህብረት አማራጩን ከወዲሁ ካላዘጋጁ ከፍተኛ ቀውስ ማስከተሉ አይቀሬ ነው:: በጀርመን ልሂቃን ወደ ውሳኔው የሚደረገውን ሂደት ከወዲሁ እየተቃወሙት ነው ሲሉ ለዶይቼ ቨል አብራርተዋል::

የአሜሪካና አጋሮቿ አዲስ ሩሲያን የማዳከም ስትራቴጂ

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቫሮቭ ከሁለት ቀናት በፊት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ቃለ መጠይቅ " ዩክሬን ከዋሽንግተን አስተዳደርና ሌሎች የአውሮጳ ሃገራት በምትቀበላቸው ምክረ ሃሳቦች ሳቢያ በሰላማዊ ድርድር ሂደቱ መግባባት ላይ የደረስንባቸውን ጉዳዮች ጭምር ደጋግማ በመጣስ ችግሩ በሰላም እንዳይቋጭ እንቅፋት እየፈጠረች ነው" ሲሉ ክፉኛ ነቅፈዋል::ሃገራቱ ጦርነቱን ለማባባስ በኔቶ በኩል ከባድ የጦር መሳሪያ ጭምር እየላኩ የውክልና ጦርነት ከፍተውብናል ሲሉም ቁጣቸውን ገልጸዋል:: ሩሲያ የኔቶ የመስፋፋት እንቅስቃሴ እንዲገታ ለማድረግና የራሳቸውን ሉዓላዊ መንግሥት ለመመስረት በሚታገሉት የዩክሬይን ዶንቴስክና ሉሃንስክ ክልሎች "ሰላም ለማስከበር" በሚል ወታደሮቿን ካዘመተች በኋላ አሜሪካና ሸሪኮቿ የአውሮጳ ሃገራት ዩክሬይን በተከፈተባት ጦርነት ራሷን ልትከላከል ይገባል በሚል ከፍተኛ የጦር መሳሪያና የሰብዓዊ ድጋፍ ሲያደርጉላት ቆይተዋል:: ይህ የምዕራባውያን ለዩክሬን የሚደረግ የተጠናከረ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ድጋፍ የክሬምሊንን አስተዳደር በእጅጉ ያበሳጨ ሲሆን የኒውክለር ጦርነት ዛቻውም መጧጧፉ ግጭቱ ወደ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት እንዳያመራ ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል::

Schweiz Genf | Sergej Lawrow während Pressekonferenz im Januar 2022

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቫሮቭ

ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ለዩክሬን ለመርዳት ስታቅማማ የቆየችው ጀርመን ከቀናት በፊት ይህን ሃሳቧን ማጠፏ እንዲሁም "አሜሪካ ለዩክሬን ወታደሮች የከባድ መሳሪያ የራዳር ሲስተምና ሌሎችንም የዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች አጠቃቀም ጀርመን ራየንላንድ በሚገኘው የራምሽታይን የአሜሪካ አየር ኃይል የአውሮጳ ተልዕኮ ዋናው የጦር ሰፈር ስልጠና መስጠት ጀምራለች" የሚለውን መረጃ ከአሜሪካው የመከላከያ መስሪያ ቤት ፔንታጎን ቃል አቀባይ ጆን ኪርቤ ከተገለጸ በኋላ ድርጊቱ ያበሳጨው የፑቲን አስተዳደር ለጀርመን አስቸኳይ ማስጠንቀቂያ መላኩ ተነግሯል:: ሞስኮ ጀርመንን የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሽንፈቷን በማስታወስ ከድርጊቷ እንድትታቀብም ነው ያስጠነቀቀችው:: ሰሞኑን የኔቶ ወታደራዊ ክፍሎች ማዕከላዊ የስልጠና ጣቢያ በሆነው በዚሁ የራምሽታይን የአሜሪካው የጦር ሰፈር በተካሄደ የሚኒስትሮችና የጦር መሪዎች ስብሰባ ከብዙ ማቅማማት በኋላ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ለመላክ የተስማማችው ጀርመን 50 ያህል "ጌፓርድ" ወይም "አቦሸማኔ" የተሰኙ ፈጣን ፀረ-አውሮፕላን ዘመናዊ ታንኮቿን ወደ ኬይቭ ለመላክ በዝግጅት ላይ መሆኗ ይፋ ሆኗል:: በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት ጀርመን የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ከሃገሯ ለማባረር ያሳለፈችውን ውሳኔ ተከትሎ ሩሲያም ከሳምንት በፊት በአጸፋው 40 የጀርመን ዲፕሎማቶችን አባርራለሁ ማለቷ የሚታወስ ነው::

ዩክሬን እስካሁን ከዩናይትድስቴትስ እስከ ፈረንሳይ ከጀርመን እስከ እንግሊዝ የተራቀቁ ሚሳኤሎች ሮኬቶችና አየር መቃወሚያ የጦር መሳሪያዎች ድጋፍ ቢደረግላትም ከቱርክ ባይራካታር እስከ አሜሪካ ዘመናዊ ሰው አልባ የድሮን ስሪቶች ዕለት በዕለት ቢጎርፍላትም ለዘመናት የተገነባውን የሩሲያ ጦር በቀላሉ አንበርክካ ወደመጣበት የምትመልሰው አይመስልም:: ወታደራዊ ድጋፉ ከቀላል ወደ ከባድ አውዳሚ የጦር መሳሪያዎች ማደጉ ያበሳጫት ከብርሃን ፍጥነት በእጥፍ የሚምዘገዘጉ መቃወሚያ ያልተገኘላቸው የኒውክለር መሳሪያዎችና የባለስቲክ ሚሳኤሎች ባለቤት የሆነችው ሩሲያ "አሜሪካም ሆነች ሸሪኮቿ ዩክሬንን ማስታጠቃቸውን ካላቆሙ ያልተጠበቀ ፈጣን አጸፋዊ ምላሽ ይጠብቃቸዋል:: ይህንን ለማድረግ ደግሞ አቅሙም ብቃቱም አለኝ" ስትል ዝታለች:: ዛቻውን ጆሮ ዳባ ያሉት ፕሬዝዳንት ባይደን ባለፈው ሳምንት አስተዳደራቸው ለዩክሬን ተጨማሪ የ 33 ቢልዮን ዶላር ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎችንና የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ ማድረጓን ይፋ አድርገዋል:: ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንና መከላከያ ሚኒስትሩ ጄነራል ሎይድ ኦስቲን በቅርቡ ኪየቭን በጎበኙበትም ወቅት "ሩሲያ የምትፈጽማቸው ወንጀሎች በምንም ዓይነት የሞራል ሚዛን ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልጸው ሁለንተናዊ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል:: በተለይም መከላከያ ሚኒስትሩ ኦስቲን "ፍላጎታችን እንደ ዩክሬን ዳግም ሌሎች ሃገራትን ማጥቃት የማትችል የተዳከመች ሩሲያን ማያት ነው" ሲሉ በግልጽ ተናግረዋል::

"በእኔ በኩል ሩሲያ ዩክሬንን በመውረር የፈጸመችው ዓይነት ተግባር ዳግም እንዳትሞክር አቅሟ ተዳክሞ ማየት ነው ፍላጎታችን:: ዩክሬን ዲሞክራሲያዊ አገር ሆና እንድትቀጥና የግዛት ሉዓላዊነቷና ሰላሟ ተጠብቆ ማየትም እንፈልጋለን" ነው ያሉት መከላከያ ሚኒስትሩ ኦስቲን::

USA Washington | Weißes Haus | Joe Biden, Präsident | Statement Ukrainekrieg

የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን

ባሳለፍነው ወር አጋማሽ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ጥበቃ ም/ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ካላቸው አምስት ቋሚ የምክር ቤቱ አባላት መካከል አንዷ የሆነችው ሩሲያ በተለይም በምክር ቤቱ የፈጸመችውን ወረራ ለማውገዝና ከሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለማገድ በተጠሩ ስብሰባዎች በተደጋጋሚ ይህን መብቷን ተጠቅማ ውሳኔዎቹን ውድቅ ማድረጓን ተከትሎ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ለመገደብ የሚያስችል ሌላ እንቅስቃሴ በምክር ቤቱ ተጀምሮ እንደነበርም ይታወቃል:: ሩሲያ ከሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እንድትታገድ በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ 93 አባል አገራት ድጋፍ የሰጡ ሲሆን፤ 24 አገራት ሲቃወሙ 58ቱ ደግሞ ድምጸ ተአቅቦ ማድረጋቸውም የሚታወስ ነው። የአውሮጳ ህብረት አሜሪካና ሸሪኮቿ ሩሲያን ለማዳከምና በጦርነቱ ተሸናፊ እንድትሆን ለማድረግ በእጃቸው ላይ የሚገኘውን ልዩ ልዩ ማዕቀብ ሁሉ ጥለውባታል:: በነዳጅ ኃይል አቅርቦት ዘርፏ በዲፕሎማቶቿና ባለሃብት ኢንቨስተሮቿ ላይ ሳይቀር የቪዛና የጉዞ ዝውውር እገዳ የተጣለባት ሩሲያ የንግድ የኢንቨስትመንትና የምጣኔ ሃብት ትብብሯም በዓለም ዙሪያ እንዲገታ ላለፉት ዘጠኝ ሳምንታት አያሌ ዕቀባዎች ሲጣሉባት ቆይተዋል:: የሩሲያውን ማዕከላዊ ባንክ ከ 11 ሺህ የሚልቁ ባንኮችንና የፋይናንስ ተቋማትን በዓለም ዙሪያ ካስተሳሰረው የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ስዊፍትና ከዓለማቀፍ ግብይት የማገዱ እንቅስቃሴም የፑቲንን አስተዳደር ፈጣን ተመሳሳይ የአጸፋ እርምጃ እንዲወስድ ነው ያስገደደው:: በመሆኑም የፑቲን አስተዳደር በንግድ ግብይቱ ዶላርና ዩሮን እንደማይቀበል ይልቁንም በሃገሩ ገንዘብ ሩብል መካሄድ እንዳለበት መመሪያ አስተላልፏል:: የፖለትካና ምጣኔ ሃብት ተንታኙ ዶክተር ጸጋዬ አሁን ላይ አሜሪካና አጋሮቿ ቀደም ሲል የፑቲን ጦር ዩክሬንን ለቆ እንዲወጣ የያዙትን አቋም በመቀየር አስፈላጊውን ሁሉ የጦር መሳሪያ ድጋፍ በማድረግ ሩሲያን በምጣኔ ኃብትና በወታደራዊ አቅም ጨርሶ የመዳከም አዲስ ስትራቴጂ መከተል የጀመሩ ይመስላል የሚለውን የአንዳንድ ባለሙያዎች ሃሳብ እንደሚጋሩ ገልጸዋል:: በተለይም አሜሪካ የአውሮጳ ሃገራት አጋር ነኝ በሚል ይህን አጀንዳ በከፍተኛ ሁኔታ እየገፋችው ቢሆንም ሩሲያም ለአጸፋ ምላሽ የማትሰንፍ በመሆኑ የተራዘመ ጦርነት በአውሮጳ መቀጠሉ ዞሮ ዞሮ ጉዳቱ ለሌሎችም ሃገራት ጭምር በመሆኑ የጦርነት ዳፋው አውሮጳ ላይ ሆኖ እንዲቀጥል የተፈለገውን የአሜሪካ ምክረ ሃሳብ አንዳን ሃገራት ይህን የሚቀበሉት እንዳልሆነ ነው ጎክተር ጸጋዬ ጨምረው ያስረዱት:: በጀርመንም ከ 1960ዎቹ ጀምሮ ጦርነትና ግጭትን ሲቃወም የኖረው አረንጓዴው ፓርቲ አሁን ላይ ጀርመን የጦር መሳሪያ ለዩክሬን እንድትረዳና በጦርነቱ ውስጥ ተሳትፎ እንዲኖራት በአስገራሚ ሁኔታ ቀስቃሽ ሆኖ መገኘቱ ከፍተኛ ትችትና ውግዘት እንዲደርስበት አድርጎታል አንዳንድ አባላቱም ፓርቲውን እስከመልቀቅ ደርሰዋል ብለዋል:: በተለያየ የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ በርካታ የጀርመን ምሁራንም "ጀርመን በሩሲያ ላይ የጀመረችውን የምጣኔ ሃብት ማዕቀብ እንድትገፋበት ከዚህ ውጪ ግን ፈጽሞ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዳታደርግና ውዝግቡ በሰላም በሚፈታበት ጉዳይ ላይም ጠንክራ በመስራት የገለልተኝነት ሚናዋን እንድትወጣ ለቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ በላኩት ደብዳቤ መጠየቃቸው ታውቋል እንደ ዶክተር ጸጋዬ ማብራሪያ:: ለአብነትም ስዊትዘርላንድ በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች አሁንም በዩክሬኑ ግጭት ገለልተኛና አማካይ የሆነ ሚና ይዛ መቀጠሏን የሚያስረዱት ምሁራኑ ከጀርመን ጋር በትብብር የሰራቻቸው የጦር መሳሪያዎች ለግጭቱ እንዳይውሉ ያሳለፈችው ውሳኔን ጀርመንም ልትከተል ይገባል የሚል አስተያየትም አላቸው::

የስንዴ የሱፍና ሌሎችንም ልዩ ልዩ የግብርና ምርቶችን በብዛት ለዓለም ገበያ በሚያቀርቡት ሩሲያና ዩክሬን መካከል ቅራኔው ወደ ጦርነት ማደጉ በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ የእህል ምርት አቅርቦትና የነዳጅ እጥረትን እንዲሁም የዋጋ መናርን አስከትሏል:: ዓለማቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና የመብት ተሟጋች ተቋማትም እንደ አፍሪቃ ባሉ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሳቢያ ሕይወታቸው በአሳሳቢ ሁኔታ ለሚገኝ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ የተራቡ ዜጎች እርዳታን በተቀላጠፈና በተገቢው ሁኔታ ማዳረስ እንዳልተቻለ እየገለጹ ይገኛሉ:: ሆኖም የአፍሪቃ ሃገራት እስካሁን በዩክሬን ጦርነት ዙሪያ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግለት ከማሳሰብ ውጪ በተለይም በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ጥበቃ ም/ቤት ሩሲያን በሚያወግዙ አጀንዳዎች ጠንካራ ድጋፍ አለመስጠታቸውን ተከትሎ ሩሲያና ቻይና በአፍሪቃ ጠንካራ ትብብርና መሰረት መጣላቸው አሜሪካንን ወዳጆቿንና ዩክሬንን ጭምር ክፉኛ ማስጨነቁ ይነገራል:: ለዚህም ይመስላል የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በድጋሚ በአፍሪቃ ህብረት ጉባኤ ላይ ለህብረቱ አባል ሃገራት መሪዎች በአውታረ መረብ አማካኝነት መልዕክታቸውን ለማስተላለፍ እንዲፈቀድላቸው ለሁለተኛ ጊዜ አበክረው ጥያቄ ያቀረቡት:: የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ዩክሬንና ሩሲያ ደም አፋሳሽ ውዝግባቸውን በሰላም እንዲፈቱ ሁለቱን ወገኖች እንዲያደራድሩ ለሰየመው ግብረ ኃይል አፈ ጉባኤዋን ማጲሳ ናቅኩላ አስተባባሪ አድርጎ መምረጡም ታውቋል:: ዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሜትሪ ኩሌባ በዘለንስኪ ጥያቄ ዙሪያ ከአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ጋር የስልክ ውይይት ማድረጋቸውንም የገለጹት የዩክሬኗ አምባሳደር ሉቡፍ አብራቪቶቫ "ዘለንስኪ የሚያስተላልፉት መልዕክት ዩክሬን ከአህጉሩ ጋር ያላትን የቆየ ትብብር ለማደስና ለማጠናከር በእጅጉ ይጠቅማል" ባይ ናቸው::

Ukraine Kiew | Pressekonferenz Antonio Guterres und Wolodymyr Selenskyj

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በኪየቭ ከዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ በተገናኙበት ወቅት

"ዩክሬን ከአፍሪቃ ህብረት ጋር ያላትን የቆየ ጠንካራ ግንኙነት ለማደስ ትፈልጋለች:: ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ስለ ሩሲያ ወረራና ጦርነቱን በሰላም ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በተመለከተ አስፈላጊውን ማብራሪያ ሁሉ ለአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች መስጠት ይሻሉ:: እስካሁን ያለው መልካም ትብብርም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለን እናምናለን"

ባሳለፍነው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ በኪየቭ በአካል ተገኝተው ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ያጽናኑ ሲሆን በጦርነቱ የወደሙ ሕንጻዎችን መሰረተ ልማቶችንና ተቋማትንም ጎብኝተዋል::ዋና ጸሃፊው በሚጎበኙበት ወቅት ዋና መዲና ኪየቭ በሩሲያ ጦር በሮኬት ትደበደብ እንደነበር ተነግሯል::

"ከእነዚህ ከፈራረሱና ከወደሙ ሕንጻዎች በአንዱ ቤት ውስጥ የቤተሰቦቼን አባላት በምናቤ አሰብኳቸው:: የልጅ ልጆቼንም ደግሞ አስታወስኳቸው :: እነዛ ሕጻናት በአስገምጋሚ የጦር መሳሪያዎቹ ጩኸት ተደናግጠው እየተሯሯጡ ቤተሰቦቻቸውን በፈራረሰው ሕንጻ ውስጥ እየፈለጉ ነው:: ሆኖም አሳዛኙ ነገር ወላጆቻቸው የጥቃቱ ሰለባ ሆነው ነበር" በማለት ወደ ፈራረሱት ሕንጻዎች በዓይናቸው እየቃኙ በትካዜ ድባብ ተውጠው የተሰማቸውን ጥልቅ ኃዘን የገለጹት ዋና ጸሃፊው ጉቴሬዝ ጦርነቱ እንዲያበቃ እንዲሁም አስቸኳይ የሰላም ውይይት እንዲካሄድም ጠይቀዋል::

እንዳልካቸው ፈቃደ

Audios and videos on the topic