የዩክሬን ቀዉስ፥ የሩሲያና የምዕራባዉያን ሽኩቻ | ዓለም | DW | 27.02.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የዩክሬን ቀዉስ፥ የሩሲያና የምዕራባዉያን ሽኩቻ

በሞስኮዎች ጥቅሻ ሳይጃገኑ አልቀረም የሚባሉ ታጣቂዎች የዩክሬንን ራስ-ገዝ ልሳነ ምድር የየክሬሚያን መንግሥት ፅሕፈት ቤት እና የምክር ቤት አዳራሽን ተቆጣጥረዉታል። ታጣቂዎቹ በሁለቱም ሕንፃዎች ላይ የሩሲያን ባንዲራ ሰቅለዋል።


የዩክሬን ፖለቲካዊ ቀዉስ የምዕራባዉያን እና የሩሲያን ሽኩቻ ይበልጥ አንሮታል።አፍቃሬ ሩሲያ ናቸዉ የተባሉ ታጣቂዎች የዩክሬንን ራስ ገዝ መስተዳድር የክሬሜያ ምክር ቤት እና የአስተዳደር መስሪያ ቤቶችን ተቆጣጥረዉታል።ባደባባይ ሠልፍ ሥልጣን የያዙትን የዩክሬን አዳዲስ መሪዎች የምትደግፈዉ ፖላንድ የታጣቂዎቹን እርምጃ አካባቢያዉ ግጭትን የሚቀሰቅስ ብላዋለች።የዩክሬኑ ተጠባባቂ ፕሬዝዳት ኦሌክሳንደር ቱርቺኖቭ በበኩላቸዉ ክሬሚያ የሠፈረዉ የሩሲያ የባሕር ጦር ከጦር ሠፈሩ እንዳይወጣ አስጠንቅቀዋል።ብራስልስ-ቤልጂግ የተሰበሰቡት የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሐገራት መከላከያ ሚንስትሮች ደግሞ ለዩክሬን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት መከበር ሙሉ ድጋፋቸዉን እንደሚሰጡ አስታዉቀዋል።ነጋሽ መሐመድ የዜና መልዕክቶችን አሰባስቧል።


ፕሬዝዳት ቪክቶር ያኑኮቪች እንደ መሪ ያመሰቃቀሉትን ፖለቲካ፥ በቅጡ ተደላድለዉ ያልተቀመጡበትን ቤተ-መንግሥት ጥለዉ ከጠፉ ወዲሕ ርዕሠ-ከተማ ኪየቭ በደስታ፥ ፌስታ፥ ሥትቀልጥ ሲምፌሮፖል- ክሬሚያ ላይ የብቀላ ሴራ ይዉጠነጠን ነበር።ከዉጪ የኪየቭ ሠልፈኞች ድል፥ ድላቸዉ የሆነዉ የዋሽግተን፥ ብራስልስ ተሻራኪዎች አዲስ ወዳጆቻቸዉን ለማጠናከር አንድ ሁለት ሲሉ፥ የኪየቩ ድሉ ሽንፈት የሆነባቸዉ ሞስኮዎች ባንፃሩ ጠንካራ ጡንቻዉን ለማሳየት እጅጌያቸዉን እየሸቀቁ ነዉ።


ኪየቮች ከምዕራባዉያን የሚጠብቁትን የፖለቲካ፥ ዲፕሎማሲ፥ የዶላር ዩሮ ድጋፍን የሚያስተዳድር ጊዚያዊ ጠቅላይ ሚንስትር ትናንት ሰየሙ።እንደ ሕዝባዊዉ ሠልፍ ሁሉ በኪየቭ የነፃነት አደባባይ ስብሰባ በጠቅላይ ሚንስትርነት የተሾሙት አርዘኒ ያሴንዩክ ያቺን ግዙፍ ጎረቤታቸዉን ቢጠሏትም ጥላቻቸዉን ባደባባይ የሚገልፁ የዲፕሎማሲ ጅል አይደሉም።«ለኛ ቁልፉ ሥራ ከሸሪካችን ከሩሲያ ጋር አዲስ አይነት ግንነት መመሥረት ነዉ።ምክንያቱም ሩሲያ ጎረቤት ሳትሆን ሸሪካችን ናት ብለን እናምናለን።»

ቭላድሚር ፑቲን ለኪየቮች አይደለም በዋሽግተን-ብራስልስ ሐይለኞች ለስላሳ ዲፕሎማሲያዊ ሽንገላ የሚለሳለሱ አልሆኑም።የያሴንዩክ ንግግር ከኪየቭ-ከመሰማቱ በፊት ጠንከራ ጦራቸዉን በተጠንቀቅ እንዲቆም አዘዋል።ግን ደግሞ የሩሲያዉ መከላከያ ሚንስትር ሠርጌይ ሾይጉ ነገሩን በዲፕሎማሲ ቃላት ለማለባበስ ጦሩ በተጠንቀቅ እንዲቆም የታዘዘዉ እንዲያዉ ለልምምድ እንጂ ለዩክሬን አይደለም ማለታቸዉ አልቀረም።

ከትናንት ጀምሮ ብራስልስ የተሰበሰቡት የምዕራቦቹ ሐገራት የጦር ተሻራኪ ድርጅት የኔቶ መከላከያ ሚንስትሮች ለሞስኮዎች እርምጃ የሰጡት አፅፋም እንደ ሞስኮዎች ሁሉ በዲፕሎማሲዉ ወግ የተቀመረ ነዉ።

«ለወደፊቷ ዩክሬን ዴሞክራሲያዊና ተጠያቂነት ያለባቸዉ ተቋማት (መኖር) አስፈላጊ ነዉ።ሉዓላዊት፥ ነፃ፣ የተረጋጋች፥ ለዲሞክራሲ እና ለሕግ የበላይነት ፅናት የቆመች ዩክሬን ለዩሮ-አትላንቲክ ፀጥታ በጣም አስፈላጊ ነች።»

ይላሉ የኔቶ ዋና ፀሐፊ አንድረስ ፎግሕ ራስሙስን።የወደፊቷ ዩክሬን እንዴትነት በርግጥ ወደፊት ነዉ የሚታየዉ።ያሁኑ ግን በሞስኮዎች ጥቅሻ ሳይጃገኑ አልቀረም የሚባሉ ታጣቂዎች የዩክሬንን ራስ-ገዝ ልሳነ ምድር የየክሬሚያን መንግሥት ፅሕፈት ቤት እና የምክር ቤት አዳራሽን ተቆጣጥረዉታል። ታጣቂዎቹ በሁለቱም ሕንፃዎች ላይ የሩሲያን ባንዲራ ሰቅለዋል።

ክሬሚያ ሳቫስቶፖል ወደብ የሚገኘዉ የሩሲያ ጦር የግዛቲቱን ሁኔታ በቅርብ ርቀት በጥብቅ እየተከታተለ ነዉ።የዩክሬኑ ጊዚያዊ ፕሬዝዳት ኦሌክሳንደር ቱርቺኖቭ የሩሲያ ባሕር ሐይል ከተከለለለት ጦር ሠፈሩ ከወጣ እንደ ወታደራዊ ወረራ እንደሚቆጠር አስጠንቅቀዋል።የፖላንድ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የራዶስላቭ ሲኮርስኪ ማስጠንቀቂያ ደግሞ ከራስዋ ከዩክሬን ጊዚያዊ መሪም ጠጠር-ጠንከር ያለ ነዉ።«የክሬሚያ ታጣቂዎችና ታጣቂዎቹን የደገፉ ሐይላት ጨወታ» አሉ ሚንስትሩ «አደገኛ ነዉ። አካባቢያዊ ግጭት የሚቀሰቅስ።»

ባለፈዉ ቅዳሜ ከኪየቭ የተሠወሩት ቪክቶር ያኑኮቮች ደግሞ ዛሬ ማርፈጃዉ ላይ ከተደበቁበት ሆነዉ የዩክሬን ሕዝብ የመረጠኝ «ሕጋዊ መሪ» አሁንም እኔ ነኝ ማለታቸዉ ተዘግቧል።ያኑኮቪች «ፅንፈኞች» ካሏቸዉ ጠላቶቻቸዉ ጥቃት ሩሲያ እድትከላከልላቸዉን ተማፅነዋልም።

ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic