የዩክሬን ቀዉስና አዲሱ ስምምነት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 12.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የዩክሬን ቀዉስና አዲሱ ስምምነት

በምሥራቅ ዩክሬን የሚካሄደዉን ጦርነት ለማስቆም ሚኒስክ ቤላሩስ ትናንት ማምሻዉን የተጀመረዉ ዉይይት ዛሬ ረፋዱ ላይ የተኩስ አቁም ስምምነትን አስገኝቷል።

አራት ወገኖች ማለትም ባለጉዳይዋ ዩክሬን፣ ችግሩን ታባብሳለች ተብላ የምትወቀሰዉ ሩሲያ፣ እንዲሁም ባደራዳሪነት ጀርመንና ፈረንሳይ የተገኙበት ለሰዓታት የተካሄደዉ ዉይይት በተጨማሪም ከባድ የጦር መሳሪያዎች ከጦርቀጣናዉ ማራቅን ጨምሮ 13 ነጥቦችን ያካተተ የመፍትሄ ሃሳቦችንም አምጥቷል። በዉይይቱ የተደረሰበት ስምምነት ተግባራዊነቱ ሲታሰብ ግን የሁሉንም ልብ የሞላ እፎይታን የፈጠረ አይመስልም።

የዩክሬን፣ የሩሲያ እንዲሁም የጀርመንና ፈረንሳይ መሪዎች የተሳተፉበት ለዩክሬን ቀዉስ መፍትሄ ለመፈለግ ትናንት ማምሻዉን ሚኒስክ ቤላሩስ ላይ የተጀመረዉ ዉይይትዉጥረት በሰፈነበት ሁኔታ ነበር። ለስምንት ሰዓታት የዘለቀዉ ዉይይትና ድርድር ሲነጋም ዉጤት አለማሳየቱ አሁንም ሊሰናከል ነዉ የሚል ስጋት አሳድሮ ቆየና ረፋድ ሲል ተደራዳሪዎቹ ወገኖች ከስምምነት ላይ መድረሳቸዉ ተሰማ።

Ukraine Konferenz in Minsk Putin

ፕሬዝደንት ቪላድሚር ፑቲን

16 ሰዓት ፈጅቷል። ገና ከመነሻዉ ታዲያ የዩክሬን ፕሬዝደንት ፔትሮ ፕሮሼንኮ የሚፈልጉትና እጅግ ትኩረት የሰጡት አንድነገር ነበር። የተኩስ አቁም። እናም ከፊታችን እሁድ ጀምሮ ተግባራዊ ሊሆን ከተፋጠጧቸዉ የምሥራቅ ዩክሬን አማፅያን ጋ በእማኞች ፊት ዉሉ ተፈረመ። ጉባኤዉን በቅርብ የተከታተሉ ምንጮች እንደገለፁት ለድርድር የተቀመጡት መሪዎች ዛሬ የደረሱበት ስምምነት ከዚህ ቀደም የኪየቭ መንግሥትና አማፅያኑ መስከረም ወር ላይ ተስማምተዉ ሥራ ላይ ያላዋሉትን የሰላም ዉል ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚያደርግ ጣምራ ዉል ላይ ለመድረስ ረዥም ሰዓት ፈጅተዋል። ከስምምነቱ ዋናዉ የተኩስ አቁሙ ሲሆን ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ከጦር እንቅስቃሴ ነፃ ከሆነዉ አካባቢ 50 ኪሎሜትና ከዚያም በላይ እንዲያርቁ፣ የአዉሮጳ የሰላምና ትብብር ድርጅትም የነዚህ ተግባራዊነት ከእሁድ ጀምሮ እንዲያረጋግጥና በሳተላይትም ሆነ በሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች እንዲከታተል የሚሉት ይገኙበታል። ከዚህ ሌላ የጦር መሳሪያዎችን ከአካባቢዉ ከተነሱ በኋላ በአማፅያን ይዞታ ስር በሚገኙት በሉጋንስክና ዶኒየስክ ለጊዜዉ ራሳቸዉን እንዲያስተዳድሩ በዩክሬን ሕግ መሠረት ምርጫ እንዲካሄድም ከስምምነት ተደርሷል። ለዚህም የዩክሬን ፓርላማ በ30 ቀናት ዉስጥ ራስ ገዙን አካባቢ መለየት ይጠበቅበታል። በተጠቀሱት አካባቢዎች በግጭቱ ለተሳተፉ ምህረት ማድረግ፣ በኪየቭ መንግስትና በአማፅያን የተያዙ እስረኞችን መለዋወጥና የሰብዓዊ ርዳታ ማስተላለፊያ መስመሮችን መክፈት የመሳሰሉት በጥቅሉ ዝርዝር 13 ነጥቦችን ስምምነቱ አካቷል። በምሥራቅ ዩክሬን ብጥብጥ እጇ አለበት በሚል የምትወቀሰዉና ማዕቀቦች የተጫኑበት ሩሲያ መሪ ቪላድሚር ፑቲን ስምምነቱ አወዛጋቢ የድንበር ጉዳዮችንም ይመለከታል ይላሉ።

Ukraine Konferenz in Minsk Merkel und Hollande

አደራዳሪዎቹ ሜርክልና ኦሎንድ

«በዚህ ላይ ዉሳኔዎቹ ለድንበር ጉዳዮችም ከዶንባስ ሚሊሺያዎች ጋ በመሆን መፍትሄ መስጠትን አካተዋል፤ የሰብዓዊ ጉዳዮች ጥያቄ፤ እንዲሁም የዶኔስክና ሚኒስክን ልዩ የግዛት ይዞታ የተመለከቱ ቀደም ሲል የተደረሱ ዉሳኔዎችን ሁሉ ተግባራዊ እንዲሆኑ ይጠይቃል።»

የዩክሬን ቀዉስ በተመለከተ በማደራደሩ ተግባር ተጠምደዉ ከከረሙት አንዷ የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ግን ስምምነቱን አሁንም በጥንቃቄ እንደሚመለከቱት ነዉ በሰጡት አስተያየት ያመለከቱት።

«የሚኒስኩን ስምምነት አጠቃላይ ተግባራዊነት ላይ ነዉ የተስማማነዉ በዚህም መጠነኛ ተስፋ አለን። ሆኖም ተጨባጭ የሚባል ርምጃ መኬድ መቻሉ ባይካድም እንቅፋት ግን መኖሩ እሙን ነዉ። ነገር ግን ሁኔታዉ ሲመዘን አሁን የደረስንበት ምንም ዉጤት ማግኘት ካልቻልንባቸዉ ጊዜያቶች ይልቅ የተሻለ ተስፋ ያሳያል። ስለዚህ ይህ እንቅስቃሴ ዋጋ ያለዉና ፕሬዝደንት ፑቲንም ለመገንጠል የሚንቀሳቀሱት ላይ ጫና አድርገዉ ከቅዳሜ እኩለ ለሊት አንስቶ ተኩስ ለማቆም እንዲስማሙ ማድረግ ተችሏል።»

ሜርክል ይህም ሆኖ ገና ብዙ ሥራ እንደሚቀር ገልፀዋል። የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት በበኩላቸዉ ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይሆናል ብለዉ ባይጠብቁም ሁሉን ያካተተ ፖለቲካዊ መፍትሄ መሆኑን ደፍሮ መናገር ይቻላል ነዉ ያሉት። ስምምነቱ በዶኔስክና ሉጋንስክ ለመገንጠል በሚንቀሳቀሱት ኃይሎች መሪ፣ በቀድሞዉ የዩክሬን ፕሬዝደንት ሊዮኒድ ክችማ፣ በሩሲያ አምባሳደር ኪየቭ ሚኻኤል ዙራቦቭ እንዲሁም በአዉሮጳ የፀጥታና ትብብር ድርጅት ልዑክ ሃይዲ ታግሊያቪኒ ነዉ የተፈረመዉ። እጅግ የተጠበቀዉ የተኩስ አቁሙም ከፊታችን እሁድ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል መባሉን የምዕራብ አዉሮጳ መሪዎች በጥንቃቄ ቢመለከቱትም መፍቀሬ ሩሲያ አማፅያኑ እንደትልቅ ድል አወድሰዉታል። ጦርነት ግጭቱ በተባባሰባቸዉ የዩክሬን ግዛቶች የሚኖሩ ሲቪሎች ግን በጥርጣሬ ነዉ ዜናዉን የተቀበሉት። ይህ በእንዲህ እንዳለም ባለፉት 24 ሰዓት ብቻ ቢያንስ 49 ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀሩ የዩክሬን መንግሥት የምሥራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል ወታደራዊ ዋና ጽሕፈት ቤትና መስተዳድር አመልክቷል። ከእነዚህም 16 የሚሆኑት ክራማቶስክ ላይ በደረሰዉ የሮኬት ጥቃት ነዉ ሕይወታቸዉን ያጡት። በምሥራቅ ዩክሬን የተካሄደዉ ግጭት እስካሁን ከአምስት ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን አልቀዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic