1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩክሬን ስደተኞች አያያዝና የስራ ሁኔታ በጀርመንና በሌሎች የአውሮጳ ሀገራት

ማክሰኞ፣ የካቲት 19 2016

በተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት ለዩክሬን ስደተኞች የሚደረገው አቀባበል ይለያያል። ከአንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሰላሳ ሺህ በላይ ዩክሬናውያንን ሀገርዋ ያስገባችው ጀርመን ስደተኞቹን በመንከባከብ ተወዳዳሪ የላትም ። መንግሥት ለዩክሬን ስደተኞች የሚወጣው ገንዘብ በቢሊዮኖች ዩሮ የሚቆጠር ነው።

https://p.dw.com/p/4cxKI
የዩክሬን ስደተኞች በጎርጎሮሳዊው 2022 በባቡር በርሊን ሲገቡ
የዩክሬን ስደተኞች በጎርጎሮሳዊው 2022 በባቡር በርሊን ሲገቡ ምስል Hannibal Hanschke/Getty Images

የዩክሬን ስደተኞች አያያዝና የስራ ሁኔታ በጀርመንና በሌሎች የአውሮጳ ሀገራት

የዩክሬን ስደተኞች ይዞታ በጀርመን 

ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት በተጀመረው የሩስያ ዩክሬን ጦርነት ሰበብ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የዩክሬን ስደተኞች ጀርመን ይገኛሉ። የጀርመን መንግሥት ለነዚህ ስደተኞች አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ነው። ይሁንና በጀርመን ስራ የማግኘት እድልም ካላቸው የዩክሬን ስደተኞች ጥቂቶቹ ብቻ በስራው ዓለም መሰማራታቸው እያነጋገረ ነው። የሩስያ ዩክሬን ጦርነት ባለፈው ቅዳሜ ሁለተኛ ዓመቱን ደፍኗል።  በዚህ ጦርነት ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዩክሬን ስደተኞች በተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት ይገኛሉ።

የተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር UNHCR በዚህ ዓመት በየካቲት ወር አጋማሽ ላይ እንዳስታወቀው በአውሮጳ ብቻ ወደ 6 ሚሊዮን የሚጠጉ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከሀገራቸው የሸሹ ስደተኞች ተመዝግበዋል። ከመካከላቸው አብዛኛዎቹ የሚገኙት ጀርመን ነው። ጦርነቱ እንደተጀመረ የዩክሬን ስደተኞች በብዛት ይጎርፉባቸው ከነበሩ ስፍራዎች አንዱ ጀርመን ዋና ከተማ በርሊን የሚገኘው ወደ ስደተኞች መመዝገቢያና መጠለያነት የተቀየረው የቀድሞው የቴግል አውሮፕላን ማረፊያ ነበር ።የጦርነቱ ሁለተኛ ዓመት በተቃረበበት ሰሞን መጠለያውን የጎበኙት የጀርመን ሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፌዘር ያኔ ቦታው ምን ያህል በስደተኞች የተጨናነቀ እንደነበር አስታውሰዋል። 
«እንደምታውቁት በተለይ በርሊን የዩክሬን ስደተኞች ዋነኛ መዳረሻ ነበር። በጎርጎሮሳዊው 2022 በቀን 15 ሺህ ስደተኛ ነበር የሚመጣው። አሁን እዚህ ያሉት ግን ጥቂቶች ናቸው። ያም ሆኖ ጀርመን ውስጥ አሁን በጣም በርካታ የዩክሬን ስደተኞች ይገኛሉ። በደንብ ልንንከባከባቸው እንፈልጋለን። »

የዩክሬን ስደተኞች ከሁለት ዓመት በፊት በርሊን ሲደርሱ
የዩክሬን ስደተኞች ከሁለት ዓመት በፊት በርሊን ሲደርሱ ምስል Hannibal Hanschke/Getty Images

ጀርመን 1.13 ሚሊዮን ዩክሬናውያን ስደተኞችን ተቀብላለች


UNHCR እንደሚለው አሁን ጀርመን ያስጠጋቻቸው የዩክሬን ስደተኞች ቁጥር 1.13 ሚሊዮን አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሰላሳ ሺህ ደርሷል። ለዚህ የጀርመን በጎ ተግባርም የአውሮጳ ኅብረት ምስጋና አቅርቧል። የቴግሉን መጠለያ ከጀርመን ሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር የጎበኙት የአውሮጳ ኅብረት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ኮሚሽነር ኢልቫ ጆሀንሰን ጀርመን በርካታ የዩክሬን ስደተኞችን በመቀበሏ አድናቆታቸውንም ገልጸዋል። «በጊዜያዊው ጥበቃ የመስጠት መመሪያ ከ4.5 ሚሊዮን በላይ የዩክሬን ስደተኞች አሉን ።የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት መሪዎች ለዩክሬን ተጨማሪ የ50 ቢሊዮን ዩሮ እርዳታ ለመስጠት ተስማሙከአንድ ሚሊዮን የሚልቁት ጀርመን ይገኛሉ። በዚህ አጋጣሚ ጀርመንን፣ የጀርመን ህዝብን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የሲቪል ድርጅቶችን የአካባቢና የግዛቶችን ባለስልጣናት ለማመስገን እወዳለሁ በጣም ጥሩ ስራ ነው የምትሰሩት።»  
ከጀርመን ቀጥሎ በርካታ የዩክሬን ስደተኞችን የምታስተናግደው ፖላንድ ናት። 956 ሺህ ዩክሬናውያን ስደተኞች ፖላንድ ውስጥ ይኖራሉ። ከዚህ በተጨማሪም ቼክ ሪፐብሊክ 381 ሺህ ፣ ብሪታንያ 253 ሺህ ፣ስፔን 192 ሺህ ፣ጣሊያን 168 ሺህ ኔዘርላንድ ደግሞ 149 ሺህ የዩክሬን ስደተኞችን ተቀብለዋል።

የዩክሬን ስደተኞች አያያዝ በተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት

በተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት ለዩክሬን ስደተኞች የሚደረገው አቀባበል ይለያያል። ከአንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሰላሳ ሺህ በላይ ዩክሬናውያንን ሀገርዋ ያስገባችው ጀርመን ስደተኞቹን በመንከባከብ ተወዳዳሪ የላትም ። መንግሥት ለዩክሬን ስደተኞች የሚወጣው ገንዘብ በቢሊዮኖች ዩሮ የሚቆጠር ነው ።የበርሊኑ ዘጋቢያችን ይላማ ኅይለ ሚካኤል እንደሚለው ጀርመን በስደተኝነት የመጡ ዩክሬናውያን ስራ ለሌላቸው የጀርመን ዜጎችም ሆነ ቋሚ የጀርመን ነዋሪዎች የሚያገኙት ማኅበራዊ ድጎማ ይሰጣቸዋል።  ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችም ያገኛሉ። 
ዮክሬናውያን በተሰደዱባቸው ሌሎች የአውሮጳ ሀገራት ግን የድጎማው መጠንም ሆነ አያያዛቸው ከጀርመን ጋር የሚወዳደር አይደለም። ለምሳሌ ፖላንድ ለዩክሬኖች የገንዘብ ድጋፍ የምትሰጠው ለሦስት ወራት ብቻ ነው። ቼክ ሪፐብሊክ ደግሞ ከመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት በኋላ በወር 130 ዩሮ የሚሆን ድጋፍ ነው የምትሰጣቸው። ብሪታንያ የምትሰጣቸው ደግሞ ከዚህም ያነሰ ነው። ፖላንድና ቼክ ሪፐብሊክ ካስጠጓቸው የዩክሬን ስደተኞች ሁለት ሦስተኛው ብሪታንያ ከሚገኙት 50 በመቶው እየሰሩ ነው።ማሕደረ ዜና፣ ዩክሬን-የፍልሚያ ምድር

በጎርጎሮሳዊው 2022 ዓም በቀድሞው የቴግል አውሮፕላን ማረፊያ የሚገኙ  ስደተኞች ምግብ ለመውሰድ ተሰልፈው
በጎርጎሮሳዊው 2022 ዓም በቀድሞው የቴግል አውሮፕላን ማረፊያ የሚገኙ ስደተኞች ምግብ ለመውሰድ ተሰልፈው ምስል Markus Schreiber/AP/picture alliance

ጀርመን ውስጥ የሚሰሩ ዩክሬናውያን ስደተኞች ቁጥር ያነሰበት ምክንያት

በበርሊኑ ቴግል መጠለያ የሚገኝ የዩክሬን ይህ ስደተኛ ጀርመን ውስጥ ሰርቶ መኖር ከሚፈልጉት አንዱ ነው። «እዚህ ሁለት ወር ቆይቻለሁ። ቴግል በስደተኝነት ተመዝግቤያለሁ ። ስራ መጀመር የሚያስችሉኝን ሰነዶች እየጠበቅኩ ነው። እዚህ ስራ ለማግኘትና እዚሁ ለመቀጠል እየሞከርኩ ነው። ሆኖም ጀርመን ከሚገኙት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የዩክሬን ስደተኞች ውስጥ እስካለፈው ታህሳስ መጨረሻ ድረስ በስራ ዓለም የተሰማሩት 214 ሺህ ወይም 20 በመቶው ገደማ ናቸው ።የተቃዋሚው የመሀል ቀኝ አቋም የሚያራምደው የክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት ፓርቲ የCDU ፖለቲከኛ ሚሻኤል ኬርችማር ለአንድ የጀርመን ጋዜጣ እንደተናገሩት ጀርመን ከሚገኙ የዩክሬን ስደተኞች አብዛኛዎቹ የማይሰሩት በሚሰጣቸው የገንዘብ ድጋፍ ምክንያት ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። ይልማ እንደሚለው አሁን ጀርመን ውስጥ በሚያነጋገረው የዩክሬን ስደተኞች ጉዳይ ላይ ሌሎች ፖለቲከኞችና የኅብረተሰብ ክፍሎችም መሰል አስተያየቶችን እየሰጡ ነው ።በርካታ የዩክሬን ስደተኞች በሚገኙባት በበርሊን የሚኖሩትና የሚሰሩት የምጣኔ ሀብት ምሁር ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ ጀርመን ተሰደው የመጡ ዩክሬናውያን በስራ ዓለም ቁጥራቸው አናሳ ስለሆነባቸው ምክንያቶች ያላቸውን መረጃ አካፍለውናል።  የአውሮጳ ኅብረት ለዩክሬን ዘላቂ ድጋፉ ይቀጥላል አለ

ምንም እንኳን ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ዩክሬኖች ስራ መስራት ያልፈለጉት በሚሰጣቸው ገንዘብ ብዛት ምክንያት ሲሉ ቢከራከሩም  የጀርመን ጥምር መንግሥት አካል ለሆነው ለሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ቅርበት ያለው የፍሬድሪሽ ኤበርት የጥናት ተቋም ድጋፍ የተካሄደ አንድ ጥናት ያመለከተው ግን ከዚህ የተለየ ነው። አጥኚው ዲትሪሽ ትራንሀርድት ከጀርመን በተለየ ከፍ ያለ የዩክሬን ሰራተኛ ቁጥር ያላቸው የሌሎች የአውሮጳ ሀገራት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ለምሳሌ ዴንማርክ ከተሰደዱት ዩክሬናውያን 78 በመቶው ስዊድንና ኖርዌይ ውስጥ ደግሞ ከ50 በመቶው በላይ ይሰራሉ። በነዚህ ሀገራት ስራ ላይ የሚገኙ የዩክሬን ስደተኞች ቁጥር  ከፍተና የሆነበት ምክንያት በአጥኚው አስተያየት በነዚህ ሀገራት የስራ ገበያውን መቀላቀል ቀላል በመሆኑ ነው። ይሁንና አጥኚው እንደሚሉት በጀርመንኛ ተናጋሪዎቹ በጀርመን ኦስትሪያ እና ስዊዘርላንድ ግን በአሰራር ስርዓቱ ውስጥ ያሉት ገደቦችና ሌሎች ብዙ ማጣራትን የሚጠይቁ አሰራሮች ጀርመን ውስጥ ዩክሬናውያኑ ስራ እንዳያገኙ እንቅፋት ሆኖባቸዋል። ለትምሕርት ማስረጃዎች ማለትም ለዶክትሬትም ሆነ ለሌሎች ዲግሪዎች እውቅና የመስጠቱ ሂደት የተወሳሰበና ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ ስራ በቀላሉ መያዝ አዳጋች ነው። አብዛኛዎቹም በዝቅተኛ ስራዎች በመሰማራታቸው ሀገራቱ ከነርሱ ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም።  

ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ