የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ዲስኩር | ዓለም | DW | 29.01.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ዲስኩር

የዩኤስ አሜሪካ ህዝብ በአሁኑ ጊዜ የሚታየውን አዳጋች የኤኮኖሚ ሁኔታ እንዲቋቋም ፕሬዚደንት ጆርጅ ዳብልዩ ቡሽ ትናንት ስለ ሀገራቸው ጊዚያዊ ሁኔታ ባሰሙት ዲስኩር ጥሪ አቀረቡ።

ፕሬዚደንት ቡሽ

ፕሬዚደንት ቡሽ

በዚሁ ስልጣናቸው ለመጨረሻ ጊዜ ለሀገራቸው ህዝብ ንግግር ያደረጉት አሜሪካዊው ፕሬዚደንት በዩኤስ አሜሪካ ኤኮኖሚ ላይ ሊደቀን የሚችለውን ስጋት በግልጽ አስታውቀዋል። የኢራቅን ጦርነት ትክክለኛነት በድጋሚ ያረጋገጡት ፕሬዚደንት ቡሽ በኢራን አኳያም ግልጹን ማስጠንቀቂያ አሰምተዋል።

ለቤት ግዢና ሽያጭ ከባንክ የተወሰደው ብድርና ወለድን ተያይዞ የተፈጠረው ቀውስ፡ በብድር የተገዙ መኖሪያ ቤቶች፡ ገዢዎቻቸው ወርሀዊ ዕዳቸውን መክፈል ባልቻሉበት ድርጊት የተነሳ በጨረታ መሸጥ የያዙበት ሁኔታ፡ እየናረ የሄደው የነዳጅ ዋጋ እና በአክስየን ገበያው ላይ የሚታየው የመዋዠቅ ድርጊት - የተሰኙት ጉዳዮች አሜሪካውያኑን በአሁኑ ጊዜ እጅግ ያሳሰቡዋቸው አርዕስት እንደመሆናቸው መጠን፡ በፕሬዚደንቱ ዲስኩር ላይ ቀዳሚውን ትኩረት ያገኘውም የዩኤስ አሜሪካ ኤኮኖሚ ይዞታ ነበር። ይህም ቢሆን ግን፡ ስልጣናቸውን ሊያበቁ አንድ ዓመት የቀረራቸው ፕሬዚደንት ቡሽ የሀገራቸው ኤኮኖሚ የቀውስ ስጋት እንዳልተደቀነበት፡ በዚህ ፈንታ አስተማማኝ ባልሆነ ጊዚያዊ ሁኔታ ላይ ብቻ እንደሚገኝ ነበር በንግግራቸው ያይ ያስታወቁት።
« በረጅም ጊዜ ሲታይ አሜሪካውያን በሀገራቸው የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ ሊተማመኑ ይችላሉ፤ በአጭር ጊዜ ሲታይ ግን፡ ያ የኤኮኖሚ ዕድገት ማዝገሙን ሁላችን ተገንዝበናል። »

ቡሽ በሀገራቸው ኤኮኖሚ ላይ ሊደቀን የሚችለውን ስጋት ለማከላከል ያወጡትንና የህግ መምሪያውን ምክር ቤት ስምምነት ያገኘው የ 150 ሚልያርድ ዶላር መርሀ ግብር የኤኮኖሚ ፓኬት ባፋጣኝ የህግ መወሰኛውን ምክር ቤት ጽድቂያ እንዲያገኝና ተግባራዊ እንደሚሆን አሳስበዋል።

« ይህ የሀገራችንን ኤኮኖሚ የሚያሳድግና ህዝባችን በስራ የሚቆይበትን ሁኔታ የሚፈጥር ጥሩ ስምምነት ነው፤ እና ምክር ቤቱ በተቻለ ፍጥነት ማጽደቅ ይኖርበታል። »

የህግ መወሰኛው ምክር ቤት ቡሽ ባቀረቡት በዚሁ የኤኮኖሚ ፓኬት አንጻር ያዘጋጀውን ሌላ ረቂቅ ዕቅድ የምክር ቤቱ እንደራሴዎቹ እንዲጥሉ ቡሽ ተማጽኖ አሰምተዋል።
« ገና ያልጨረስናቸው ብዙ ስራዎች አሉ፤ የአሜሪካ ህዝብም እነዚህን ጉዳዮች ፍጻሜ ላይ እንድናደርስ ይጠብቀናል። »
ፕሬዚደንት ቡሽ ባነሱት የኤኮኖሚ ፓኬት ውስጥ አሜሪካውያን ለመንግስታቸው የሚከፍሉት ቀረጥ ዝቅ የሚልበት ውሳኔ በሀገሪቱ ህገ መንግስት የሚሰፍርበትና ተቋማትም ገንዘባቸውን በሀገራቸው እንዲያሰሩ የሚያበረታቱና ነቀፌታ የበዛበት የህጻናት ትምህርትን የሚመለከተው መርሀ ግብራቸው የሚራዘምበት፡ እንዲሁም፡ በጤናው ዘርፍና የውጭ ሀገር ዜጎችን በሚመለከተው ህግ ላይ ይደረግ ያሉትና በሁለቱም ምክር ቤቶች ውስጥ ጽድቂያ ያላገኘው የተሀድሶ ሀሳቦች ተጠቃለውበታል።
በዴሞክራቶችና ሬፐብሊካኖቹ እንደራሴዎች ልዩነት የተነሳ ካሁን ቀደም ብዙ ረቂቅ ህጎች መክሸፋቸውን ፕሬዚደንቱ በማስታወስ፡ የሁለቱ ፓርቲዎች እንደራሴዎች ለሀገር ሲሉ ከፓርቲ ባሻገር ባንድነት ተባብረው እንዲሰሩ በዲስኩራቸው ወቅት በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበዋል። ረቂቅ ህጎችን ተጨማሪ ገንዘብ በመመደብ ጽድቂያ እንዲያገኙ በማድረጉ አሰራር አንጻር ማስጠንቀቂያ በማሰማት፡ ወደፊት በዚህ መንገድ የሚያልፉ ህጎች የርሳቸውን ጽድቂያ እንደማያገኙ ቡሽ አስታውቀዋል።
የውጭ ፖሊሲን በተመለከተ በርካታ ጉዳዮችን ያነሱት አሜሪካዊው ፕሬዚደንት የኢራን መንግስት አከራካሪውን የሀገሩ የአቶም መርሀ ግብር ለማቆም ዝግጁ እስካልሆነ ድረስ፡ በዚችው ሀገር አንጻር አስፈላጊውን ርምጃ ለመውሰድ ካሁን ቀደም ያሰሙትን ማስጠንቀቂያ በተግባር እንደሚተረጉሙ በድጋሚ አሰምተዋል። እስራኤልና ፍልስጤማውያንም አንድ የሰላም ውል ይደርሱ ዘንድ የሚቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉና ዩኤስ አሜሪካ ወደ አፍጋኒስታንም ተጨማሪ ሶስት ሺህ ሁለት መቶ ወታደሮችን እንደምትልክ ነው ቡሽ ያስታወቁት።
በዲስኩሯጨው ለኢራቅ ሰፊ ቦታ የሰጡት ፕሬዚደንት ቡሽ በዚያ የሚንቀሳቀሰው የተቃውሞ ወገን አሁንም ትልቅ አደጋ መደቀኑን ገልጸዋል፤ ይሁንና፡ እንደፕሬዚደንቱ ገለጻ፡ ብዙዎች ባይጠብቁትም፡ ያሜሪካውያኑና የኢራቅ ጦር ኃይላት ባለፈው ዓመት የመንግስቱ ተቃዋሚዎች የሰነዘሩትን ጥቃት በማክሸፉ ረገድ የተሳካ ውጤት አስመዝግበዋል።
« ክቡራትና ክቡራን፡ አንዳንዶች የጦሩ መጠናከር ተፈላጊውን ውጤት ማስገኘቱን ይክዱ ይሆናል፤ አል ቓይዳ በመሸሽ ላይ መሆኑን ግን አሸባሪዎቹ በፍጹም እንደማይጠራጠሩት ግልጽ ነው፤ እና ይህ ጠላት ይሸነፋል። »
በዚህ ዓመት ሀያ ሺህ አሜሪካውያን ወታደሮች እንደታቀደው ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱ ይጠበቃል። ይሁንና፡ በኢራቅ ያለው የሀገራቸው ጦር ከዚችው ሀገር የሚወጣበት ድርጊት በኢራቅ በሚታየው ጊዚያዊ ሁኔታና በዚያ ያሉት ያሜሪካ ጦር ዋና አዛዥ ጀነራል ዴቪድ ፔትሬውስ የፊታችን መጋቢት በሚያቀርቡት ዘገባ ላይ ጥገኛ እንደሚሆን አሜሪካዊው ፕሬዚደንት አስታውቀዋል።