የዩኤስ አሜሪካ ዉ/ጉ/ሚ የአፍሪቃ ጉብኝት | ዓለም | DW | 06.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

  የዩኤስ አሜሪካ ዉ/ጉ/ሚ የአፍሪቃ ጉብኝት

 የዩናይትድ ስቴትስ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዚህ ሳምንት አምስት የአፍሪቃ ሃገራትን  ይጎበኛሉ።  ሬክስ ቲለርሰን የሚጎበኟቸዉ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ቻድ እና ናይጀሪያ ዋሽንግተን በምታካሂደዉ የፀረ ሽብር ዉጊያ ተሳታፊዎች ናቸዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:10

የፀጥታ ጉዳይ ቀዳሚዉ አጀንዳ ይሆናል፤

አሜሪካዊው ከፍተኛ ባለስልጣን ወደ አፍሪቃ የሚጓዙት አህጉሪቱን በጸያፍ ያቃላት ያጣጣሉት ፕሬዝደንቱ የፈጠሩትን ቅሬታ ለማለዘብም እንደሆነ ነዉ የሚነገረዉ። የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ለአፍሪቃ መሪዎች በጻፉት ደብዳቤ ለአህጉሪቱ ጥልቅ አክብሮት እንዳላቸዉ ቢገልፁም ጸያፍ አነጋገራቸዉ የፈጠረዉ ንዴት ግን እንዳለ ነው። ቻዳዊዉ ተሟጋች አህመት ኦማር በትዊተር መልዕክቱ «የእርስዎን ጥልቅ አክብሮት አንፈልግም፤ ቲለርሰን በእነዚህ «ቆሻሻ» ሃገራት መልካም አቀባበል አይጠብቃቸዉም።» በማለት ያ ንግግራቸዉ ዛሬም እንዳልተረሳ ጠቁሟል። 
የትራምፕ አስተዳደር  እስካሁን ለአፍሪቃ ያሳየዉ ፍላጎት አነስተኛ ነው፤ ሌላዉ ቀርቶ አሁንም አፍሪቃን የሚመለከት ይህ ነዉ የሚባል ስልት ገና አልቀረፀም ይላል በዋሽንግተን የዶቼ ቬለ ዘጋቢ ካርስተን ፎን ናመን። 
«የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ይህን ጉብኝት ባለፈዉ ኅዳር ወር ሬክስ ቲለርሰን ዋሽንግተን ላይ ከአፍሪቃ ተጓዳኞች ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ያካሄዱት ጉባኤ ቀጣይ አድርጎ ነዉ የሚመለከተዉ።  የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ከያዙ አንስቶ አፍሪቃ ላይ አላተኮረም ተብሎ እየተተቸ ነው። አፍሪቃን በሚመለከት የአሜሪካ ፖሊሲ በግልፅ አልተቀመጠም፤ በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ዉስጥ አፍሪቃን የሚመለከቱ ወሳኝ ቦታዎች ሰዎች አልተሾሙባቸውም። እንዲያም ሆኖ ግን አሁን አሜሪካኖች ያንን ለመለወጥ እየሞከሩ ነው።»
የዩናይትድ ስቴትስ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን በአፍሪቃ በሚያደርጉት ጉብኝት ግንባር ቀደሙ አጀንዳ ፀረ ሽብር ዉጊያዉን ይመለከታል ተብሏል። በአፍሪቃ የቲለርሰን ወኪል የሆኑት ዶናልድ ያማሞቶ ጉብኝታቸዉን አስመልክተዉ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ቲለርሰን ከአፍሪቃ ኅብረት መሪዎች በሚያደርጉት ዉይይት አፍሪቃ የተጋፈጠቻቸዉን መሠረታዊ ጉዳዮች ያነሳሉ ነዉ ያሉት።


«በአንድ ወገን አፍሪቃን እየፈተኑ ስላሉት ጉዳዮች ለመነጋገር ሙሳ ፋኪን እና የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽነሮችን ያገኛሉ። ስለ ደቡብ ሱዳን፣ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፤ ሶማሊያ  ቀውስ፣ እንዲሁም   የቡድን አምስት ሃገራትን ስለመደገፍ  ጉዳይ ይመክራሉ። ዋናዉ ነገር ደግሞ ለኤኮኖሚ እድገት ያሉትን ዕድሎች ይፈትሻሉ። በተጨማሪም ለመላዉ የአፍሪቃ አህጉር ጥላ የሆነዉን የአፍሪቃ ኅብረትም ይመለከታሉ።»
የአፍሪቃ የፀጥታ ጉዳይ ዋሽንግተንን ማሳሰብ የጀመረዉ ባለፈዉ ጥቅምት ወር ሁለት የአሜሪካ ወታደሮች ኒዠር ዉስጥ በፅንፈኛ ታጣቂዎች ጥይት ከተገደሉ በኋላ ነው። በአፍሪቃ እራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ ራሱን ከሚጠራዉ ቡድን ጋር ትስስር አላቸዉ የተባሉ ጥቂት ታጣቂዎች በጥቁር መዝገብዋ ዉስጥ ስማቸዉ ሰፍሯል። ዋሽንግተን ለእነሱ ከዩናይትድ ስቴትስ የሚደረገዉን የገንዘብ ድጋፍ  ማገድ ትፈልጋለች። ፔንታገን ወደ አፍሪቃ 6,000 ወታደሮችን ልኳል፤ ወታደሮቹ ከሚገኙባቸዉ ቦታዎችም ኒዠር ፣ ሶማሊያ እና ጅቡቲ ይጠቀሳሉ። በእዚያ ሃገራት የዩናይትድ ስቴትስ ትልቅ ወታደራዊ ጣቢያ ይገኛል። ወታደሮቹ በፀረ ሽብር ዉጊያዉ ከመሳተፍ ሌላ ለአጋር ሃገራት ወታደራዊ ስልጠና ይሰጣሉ። በዚህ ረገድ ጅቡቲ ተፈላጊ ሀገር ናት። ጅቡቲ ዉስጥ ፈረንሳይ እና ጃፓንም የጦር ሠፈር አላቸው። በቅርቡ ደግሞ ቻይና የራሷን የጦር ሠፈር እዚያዉ ከፍታለች። ዩናይትድ ስቴት ጅቡቲ ላይ ወታደራዊ ጣቢያ የመሠረተችዉ ቻይና የአፍሪቃን አህጉር በተመለከተ ያላትን እቅድ ለማወቅ ትሻለች። ለዚህም በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የፀደይ ወራት ዋሽንግተን ላይ ከቤጂንግ ጋር እንደምትነጋገር ያማሞቶ ተናግረዋል። ዋናዉ ጉዳይም ፀጥታን በተመለከተ እንዴት መተባበር እንደሚቻል ለመወያየት ነው ብለዋል ዲፕሎማቱ። 


ምንም እንኳን ከጅቡቲ፣ ቻድ እና ከአፍሪቃ ኅብረት መሪዎች ጋር በሚደረገዉ ዉይይት ፀጥታ እና ስልታዊ ጉድኝት አበይት መነጋገሪያዎች ቢሆኑም፤  የቲለርሰን የኢትዮጵያ እና የኬንያ ጉብኝት ግን ሃገራቱ ዉስጥ አሁን በሚታየዉ የግጭት ሁኔታ የሚወሰን ነዉ የሚሆነው። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣን መልቀቃቸዉን ባሳወቁ ማግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉን ከተቹት መካከል ቀዳሚዋ ዋሽንግተን ናት። ኬንያም እንዲሁ የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎችን ጠንካራ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ አስተናግዳለች። በተለይም ከአወዛጋቢዉ ምርጫ በኋላ ተሸናፊዉ ራይላ ኦዲንጋ በሕዝብ የተመረጠ ፕሬዝደንት ተብለዋል። ከዚህ ሌላም በያዝነዉ አስርት ዓመታት ማለቂያ ላይ 40 ከመቶ የሚሆነዉ የዓለም ሕዝብ የሚገኝባት አፍሪቃ የኤኮኖሚ እድገት እና ያለዉ ዕድል የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካን ቀልብ የሳበ ጉዳይ ነው። አብዛኛዉ ዜጋዋ ወጣት የሆነችዉ አፍሪቃን በተመለከተ ባራክ ኦባማ ያቋቋሙት «ወጣት የአፍሪቃ መሪዎች» የተሰኘዉ መርሃ ግብር ዩናይትድ ስቴትስ የምትሰጠዉን ትኩረት አመላካች መሆኑን ያማሞቶ ተናግረዋል። በዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉዞ የሚካተቱት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ናይጀሪያም በአህጉሪቱ ያሉ ሦስት የወሳኝ ኤኮኖሚ ባለቤት ሃገራት ናቸዉ። በዚህ ጉብኝታቸውም ቲለርሰን አሜሪካ ለአፍሪቃ ያላትን መልካም አመለካከት ለማሳየት እንደሚጥሩ ነዉ ካስተን ፎን ናህመን የሚገምተዉ፤
«ይህን አጋጣሚ የመልካም ምኞት ማመላከቻ አድርገዉ ለማሳየት ይሞክራሉ፤ በእርግጥ አፍሪቃ ያለምንም ጥርጥር አስፈላጊ ናት፤ ጥያቄዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት በዚያ መልኩ ያዩታል ወይ የሚለዉ ነው። በፕሬዝደንቱ ዙሪያ ያሉት የፀጥታ እና የዲፕሎማሲዉ ተቋማት አፍሪቃ አስፈላጊ ስለሆነች ትኩረት ሊሰጣት ይገባል ይላሉ። በአሜሪካን መንግሥት ወሳኝነት ያላቸዉ ፕሬዝደንቱ ግን  ለመቀበል አዝግመዋል። ለዚህም ነዉ ይቅርታ ሳይሆን ምን ያህል ለአፍሪቃ አክብሮት እንዳላቸዉ የሚገልፅ ደብዳቤያቸዉን የላኩት።» 

ሸዋዬ ለገሠ /ፊሊፕ ዛንድነር

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic