የዩኤስ አሜሪካ መርሃግብር እና ኢትዮጵያውያን ወጣቶች | ባህል | DW | 01.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የዩኤስ አሜሪካ መርሃግብር እና ኢትዮጵያውያን ወጣቶች

ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ለአፍሪቃ እድገት እና ብልፅግና ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ያሏቸውን ከተለያዩ የአፍሪቃ ሀገራት የተውጣጡ 500 ወጣት አፍሪቃውያንን ዘንድሮ ወደ ሀገራቸው ጋብዘው ነበር።

የዮናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ለአፍሪቃ ጠቃሚ ድርሻ ሊያበረክቱ ይችላሉ የሚባሉ ወጣት አፍሪቃውያንን በአመራር ውስጥ ሊኖራቸው የሚችለውን ተሳትፎ ለማበረታታት እጎአ 2010 ዓም አንድ መርሃግብር መጀመራቸው ይታወሳል። በዚሁ አህጉሩን ይጠቅማል በሚባለው መርሃግብር ስር ዘንድሮም ከተለያዩ የአፍሪቃ ሀገራት የተውጣጡ ወጣት አፍሪቃውያን ለስድስት ሳምንታት ወደ ዮናይትድ ስቴትስ ጎራ ብለው ነበር። « በሀገራቸው ብቻ ሳይሆን በዓለማችን ዙሪያ ነገሮችን ወደ ተግባር የሚተረጉሙ እና ለመተግበር የተነሳሱ ወጣት አፍሪቃውያን ታስፈልጉናላችሁ በማለት ወጣት አፍሪቃውያኑ እንዲወዳደሩ ጥሩ ያደረጉት ኦባማ » ለወጣቶቹ ሀገራቸው አጋር ለመሆን እንደምትፈልግም ገልፀው ነበር። ይህም ብዙ ጆሮ ደርሶ ወደ 50 000 የሚጠጉ አፍሪቃውያን ወጣቶች የመወዳደሪያ ማመልከቻቸውን አስገብተዋል። ከናይይጀሪያ 15 000 ፣ ከኢትዮጵያ ደግሞ 2100 በውድድሩ ተሳትፈዋል።

የመመረጥ ዕድል ያጋጠማቸው ኢትዮጵያውያኑ በተለያዩ የዮናይትድ ስቴትስ ግዛቶች በ20 የከፍተኛ ተቋማት ውስጥ የስድስት ሳምንት ቆይታ አድርገዋል። ከሰኞ ጀምሮ ደግሞ ዋሽንግተን ዲሲ በመገኘት ፤ ፕሬዚዳንት ኦባማ ፣ ባለቤታቸው ሚሼል ኦባማ እና የሀገሪቱ ታላላቅ ባለስልጣናት ለነዚህ 500 አፍሪቃውያን ባደረጉት የሦስት ቀናት ጉባኤ ላይ ተካፍለዋል። በመርሃግብሩ የተሳተፉት እድሜያቸው ከ25-35 የሆኑ አምስት ሴት እና ሰባት ኢትዮጵያውያን ናቸው።

ከነዚህ ወጣቶች አንዷ የሆነችው ሀሌታ ግደይ የህግ ባለሙያ ናት። ከመደበኛ የስራ ሰዓቷ ውጪ ወንጀልን ፣ እንዲሁም ጥቃቶችን እንዴት መከላከል ይቻላል በሚሉ ጉዳዮች ላይ በየገጠሩ እና ት/ቤቶች እየሄደች ወጣቶችን እና ሴቶችን ታስተምራለች፤ ከዚህም ሌላ ያላትን ስልጣን ተጠቅማ ወንጀለኞችን ትከስ እና ታስቀጣ እንደነበር ገልፃልናለች። እሷም ሆነች አዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ቢሮ ውስጥ የምትሰራው ኢዳ ዘካርያስ እስካሁን ያገኙትን ተሞክሮ ይዘው ኢትዮጵያ ውስጥ በሴቶች ጉዳይ ላይ ለመስራት ወስነዋል።

እነዚህን እና ሌሎች ሶስት ወደ ዮናይትድ ስቴትስ የተጓዙ ወጣቶችን በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት አነጋግረናል። ሙሉ ዘገባውን በድምጽ ያገኙታል።

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic