የዩናይትድ ስቴትስ የፀረ ሚሳዬል ሚሳዬል እቅድና ምላሹ | ዓለም | DW | 21.09.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የዩናይትድ ስቴትስ የፀረ ሚሳዬል ሚሳዬል እቅድና ምላሹ

የሚሳዬል-ተከላ ነቀላዉ ፦ የተፈጥሮ ሐብት ልማት ጥፋቱ ለአለም ሰላም፦ ደሕንነት መጥቀም መጉዳቱ ግን ያዉ ሜድቬዴቭ እንዳሉት በነሱዉ የሚወሰን ነዉ።

default

21 09 09

የፖላንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ዶናልድ ቱስክ-እንደሚሉት ባለፈዉ ሮብ ያላደረጉትን ያላደረጉት የቡሽን የሚሳዬል እቅድ-ኦባማ በመሻራቸዉ ተቆጥተዉ ሳይሆን ፕሮቶኮል በመጓደሉ አኩርፈዉ ነበር።ያአንጋፋ ፖለቲከኞቻዉ አቋም ግን ተቃራኒዉን መስካሪ ነዉ።የቼክ ሪፐብሊክ ያሁን መሪዎች በሆነዉ መደሰት-መከፋታቸዉን ከመግለጥ ይልቅ በሚሆነዉ እየተፅናኑ ነዉ።የኦባማ ዉሳኔ ዩናይትድ ስቴትስ-ፖለቲከኞችን በፓርቲ፣ የጦር አዛዦችን በክፍል እሁለት ገመሷል።ለብራስልስ ደንገዝ፣ ለበርሊን ፈካ፣ ለሞስኮ ሞቅ-ደመቅ ያለ ደስታ ነዉ።-ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።የዉሳኔዉን መሠረት፤ የምላሹ መቃረን ምክንያት፣ ለአለም ሰላም የሚኖረዉ ዉጤት ያፍታ ቅኝታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁኝ ቆዩ።

የፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ መስተዳድር ፖላንድ ላይ የፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬል፣ ቼክ ሪፐብሊክ ሬዳር ለመትከል የወሰነዉ ራሳቸዉ ቡሽና ባለሥልጣኖቻቸዉ በተደጋጋሚ እንዳሉት ኢራን አዉሮጳን እንዳትደበድብ ለመከላከል ነዉ።የዉሳኔዉን አስጊነት፣ የምክንያቱን መሠረተ-ቢሥነት፣የእዉነተኛ አለማዉን ምንነት ለመረዳት ብዙዎች የኢራንን አቅም፣ ከአዉሮጳ ጋር ያላትን ቅራኔ፣ አዉሮጶች ኢራንን የሚፈሩበትን ደረጃ ማስተንተን ብዙ አላስፈለጋቸዉም ነበር።

ኦባማም-በቀደም የቡሽን እቅድ ሲሽሩ-ወትሮም ጠንካራ ምክንያት አልባዉን ሰበብ ማፍረስ ብዙ አላስጨነቃቸዉም።የኦባን የዉሳኔ መሠረት-ትክክለኛነቱንም ለመመስከር ደግሞ የቡሽም፥ የኦባም መከላከያ ሚንስትር ከሆኑት ከሮበርት ጌትስ-የቀረበ የቀደመም የለም።

«የስለላዉ ማሕበረሰብ ጥናት እንደሚያመለክተዉ ሻሐብ-3ን የመሰለዉ የኢራን የአጭርና የመካከለኛ ርቀት ተምዘግዛጊ ሚያሳዬል የሚያሳድረዉ ሥጋት በፊት ከተገመተዉ ይበልጥ በፍጥነት እያደገ ነዉ።ይሕ አዉሮጳ በሰፈረዉ ሐይላችን እና በወዳጆቻችን ላይ የባሰና አጣዳፊ ሥጋት ያሳድራል።በሌላ በኩል የስለላዉ ማሕበረሰብ ጥናት ኢራን ክፍለ-አለም አቋራጭ ተምዘግዛጊ ሚሳዬል የመሥራት አቅሟ በሁለት ሺሕ ስድስት ከተገመተዉ አዝጋሚ እንደሆነም ያመለክታል።»

የኢራንን ሚሳዬል ያከሽፋል የተባለዉ ፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬል በሩሲያ ላይ ማነጣጠሩን ለመረዳት ሞስኮዎች ሁለቴ ማሰብን አልጠየቃቸዉም።

ሩሲያ ሥልታዊ ተቋም፣ አካባቢዎቿን የሚመታ፣ ወታደራዊ እንቅስቃሴዋን የሚቆጣጠር ሚሳዬል-ሬዳር አፍንጫዋ ሥር እንዲተከል በመወሰኑ ፈርታ ለዋሽግተን ባደሩት ጀርጂያና ዩክሬንና በመሳሰሉት የቀድሞ የሶቬት ሕብረት ሪፐብሊኮች ላይ የምታደርገዉን ተፅዕኖ ታቆማለች፣ ምናልባት ኢራንን ለመኮርከም፤ ሰሜን ኮሪያን አደብ ለማስገዛት ከአሜሪካኖች ጋር ትተባባራለች ብለዉ የገመቱ በርግጥ አልጠፉም ነበር።

Symbolbild Raketenabwehrsystem

ፕሬዝዳት ቭላድሚር ፑቲን ግምቱን ግን አምክነዉ-የገማቾቹን የዋሕነት ለማፍጋት ጊዜ አልፈጀባቸዉም።ፑቲን ከንቀት የቆጠሩትን የቡሽን እቅድ የግልብጥ ለማስኬድ የሐገራቸዉን የነዳጅ-ጋዝ-ሐብት፣ መልከአምድራዊ አቀማመጡ፣ የጦር ሐይል-ጉልበት እዉቀት፣ ሽያጭ፤ የፖለቲካ-ዲፕሎማሲዉ ጡንቻ-ሁሉም ነበረላቸዉ።አጠቃቀሙንም አላጡበትም።

ሞስኮዎች የሚሳዬል-ሬዳር ዛቻዉን-በሚሳዬል ዛቻ ሲበቀሉት።የፕሬዝዳንት ቡሽ እቅድ ከማንም በላይ-ያስጨነቀ፣ ያስደገጠ፣ ያሰጋ፣ ግራ ያጋባዉ ቡሽ ከኢራን ጥቃት አድንሐለሁ ያሉት አዉሮጳዊ መሆኑ ነዉ-የወለፊንዱ ሐቅ።የዋሽግተን-ሞስኮዎች የሚሳዬል ተከላ እቅድ-አፅፋ እቅድ ንረት ወትሮም በቅጡ ያልጠናዉን የሁለቱን ሐያላን ያጭር ዘመን ወዳጅነት አወለካክፎ-አለምን ከአስራ-ስድስት አመት በፊት ወደነበረችበት የቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍጥጫ ይዶላል ነበር-የሥጋቱ ሥጋት።

የጀርመንዋ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል እንደሚያምኑት የቡሽ እቅድ መሰረዙ አዉሮጶችን ጭንቀት፥የአለምን ስጋት፥የዋሽንግተን-ሞስኮዎችን የጠብ ንረት ከማስወገድ አልፎ-ኢራንንም ለመግራት ጠቃሚ ነዉ።

«ዉሳኔዉ ከሩሲያ ጋር ያለዉን ችግር ለማስወገድ እንደ አንድ ትልቅ ተስፋሰጪ ምልክት ነዉ-የማየዉ።ኢራን የምታሳድረዉን ሥጋት በጋራ ለመታገል የሚረዳ የትብብር ሥልት ለመቀየስም ጠቃሚ ነዉ።የአሜሪካ መንግሥት ዉሳኔ ከኢራን ጋር በጋራ እንድንነጋገር ይረዳል የሚል ተስፋም አለኝ።ድርድሩ ለዉጤት ካልበቃ ደግሞ ማዕቀብ ለመጣል ይጠቅማል።እና እኔ እስካሁን እንደማየዉ ለአለምአቀፍ ትብብር ሙሉ ተስፋ ነዉ።»

ፕሬዝዳት ቡሽ ይወክሉት ከነበረዉ የሪፐብሊካን ፓርቲ ፖለቲከኞች አንዳዶቹ እንደሚተቹት ግን ኦባማ-በቀደም የወሰኑትን የወሰኑት ሩሲያን ፍራቻ ነዉ።ሌሎቹ የአሜሪካ ክብር-እንደተነካ ቆጥረዉታል።

ለዲሞክራቶቹ ባንፃሩ የኦባማ ዉሳኔ ከፖለቲካዊ፥ ወታደራዊ ጥቅሙ ባሻገር ምጣኔ ሐብታዊ ፋይዳዉም እጅግ ነዉ።የዩናይትድ ስቴትስ ምጣኔ ሐብት የአለምን አስከትሎ ቁል ቁል በሚንደረደርበት፤ የኢራቅና የአፍቃኒስታኑ ጦርነት የሐያል-ሐብታሚቱን ሐገር ሐብት-እዉቀት፣ የወጣቶቿን-አካል-ሕይወት በያጭድበት በዚያ ወቅት 4.5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሚሳዬል-ራዳር እንዲተከል ቡሽ መወሰናቸዉ ዲሞክራቶቹን ወትሮም አላስደሰተም ነበር።

የአላስካዉ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ሴናተር ማርክ ቤጊች የኦባማን ዉሳኔ የሚደግፉበት ከብዙዎቹ ባልደረቦቻቸዉ በተለየ ምክንያት ነዉ።ምሥራቅ አዉሮጳ ሚሳዬል መተከሉ ከተሰረዘ-ኤፍ ቲ ግሪሌይ-አላስካ የሚገኘዉ የሚሳዬል ጣቢያን መጠናከር አለበት።ጣቢያዉን ለማጠናከር ማዕከላዊዉ መንግሥት ብዙ ገንዘብ ሲመድብ-የሴናተር ቤጊች መራጭ ሕዝብ ብዙ ሥራ፥ ብዙ ገንዘብ ያገኛል-ሴናተሩም ለሚቀጥለዉ ምርጫ ብዙ-ድምፅ።

ፕሬዝዳት ኦባማ የቡሽን እቅድ ሲሰርዙ የኢራንን ሥጋት ለማስወገድ ዉጤታማ ያሉትን የራሳቸዉን አዲስ እቅድ አዉጀዋል።

«የአዉሮጳዉ አዲሱ የሚሳዬል መከላከያችን የአሜሪካ ሐይልና ወዳጆችን ከጥቃት ለመከላከል ጠንካራ፥ ቀልጣፋና ፈጣን ነዉ።ከቀድሞዉ ብዙ ነገሮችን ያጠቃለለ መርሐ-ግብር ነዉ።ብቃቱ የሚያስተማምን፥ ዋጋዉ ምጥን፥ዩናይትድ ስቴትስን ከረጅም ርቀት ሚሳዬሎች ሥጋት ለመከላከል ባለን ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ነዉ።የኔቶ ወዳጆቻችንን በሙሉ ካደጋ ለመከላከል የሚያስተማምን ነዉ።»

አዲሱ ፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬል ከመሬት ይልቅ መርከብ ላይ የሚተከል ነዉ።እቅድ-ዉሳኔዉ የአሜሪካ የባሕር ጦርን ይበልጥ-ሲያጠናክር የምድር ጦሩ የመጠናከር ፍላጎት ገድቦታል።የባሕር ጦር አዛዦች ሲደሰቱ-የምድሮቹ ባይከፉ-ቅር ተሰኝተዋል።የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ ዋና ፀሐፊ አንደርስ ፎግሕ ራስሙሰን የኦባማን ዉሳኔ ከጥንቃቄ ጋር ግን በደስታ ተቀብለዉታል።

የፖለንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ዶናልድ ቱስክ ከዋሽግተን የተደወለላቸዉ ሐገራቸዉ ከሶቬት ሕብረት ወረራ ነፃ በወጣችበትን ሰባኛ አመት በአል-ላይ በተለይ ሥለ ሞስኮ አገዛዝ-የሚናገሩትን በሚያሰላስሉበት መሐል-ነበር።ሮብ።-ማታ።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊተን ናቸዉ።መልዕክቱን አላጡትም።የአሜሪካን ዉሳኔ ማስቀር-እንደማይችሉም ያዉቁታል።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሪቱን አላናግርም-አሉ።

ምክንያት የሥልጣን ተዋረድ መጠበቅ አለበት።የፕሬዝዳት ሌሕ ካሲያንስኪ የቅርብ አማካሪ ቪቶልድ ቫስያኮቭስኪ ግን ቁጣቸዉን እንደጠቅላይ ሚንስትሩ አልሸፋፈኑትም።

«ዛሬ የሐዘን ቀን ነዉ።ምክንያቱም ለደሕንነታችን የነበረንን ዋስትና በማጣታችን»

ከትንሺቱ የቼክ ሪፐብሊክ ሕዝብ ሰባ-ከመቶ ያሕሉ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር መሳሪያ በሐገሩ መተከሉን ይቃወም ነበር።አሁንም ይቃወማል።የቀድሞዉ የሐገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሚራክ ቶፖላንከ ግን የጦር መሳሪያዉ አለመተከሉ ለቼክ ሕዝብ የስጋት ምንጭ ነዉ።አሜሪካም-ከራስዋ ጥቅም ሌላ የሌሎች የማይታያት ሐገር።ያሁኑ ጠቅላይ ሚንስትር ያን ፊሸር-ግን የሐገራቸዉና የዩናይትድ ስቴትስ መልካም ግንኙነት አይታጎልም ባይ ናቸዉ።

ዉሳኔዉ ለሩሲያዉ ፕሬዝዳት ለዲሚትሪ ሜድቬዴቭ አስደሳች ነዉ። ተባብሮ-ለመስራት ጠቃሚ።

«የሚሳዬል ግንባታዉ ያለዉን ችግር ከፕሬዝዳት ኦባማ ጋር ለንደንም ሞስኮም የተገናኘን ጊዜ አስረድቼቸዋለሁ።የሚሳዬል ግንባታ በአለም ላይ ሊያደርስ የሚችለዉን አደጋ ለመከላከል ሩሲያና ዩናይትድ ስቴትስ ተባብረዉ የመስራት የጋራ አለማ እንዳላችዉ ተግባብተናል።ይሕ በመግለጫችንም የተካተተ ጉዳይ ነዉ።ሐሙስ ዋሽግተን ዉስጥ የተሰጠዉ መግለጫ ለእንዲሕ አይነቱ የትብብር ሥራ የሚያነቅፍ ነገር የለዉም።»

ከነገ-ጀምሮ የበርካታ ሐገራትን መሪዎች የሚያነጋግሩት ፕሬዝዳት ባራክ ኦቦማ የሚሳዬል፥ ተፈጥሮ ጥበቃ፥ የፍልስጤም-እስራኤሎች ድርድር ዋና ርዕሳቸዉ ነዉ።የሚሳዬል-ተከላ ነቀላዉ ፦ የተፈጥሮ ሐብት ልማት ጥፋቱ ለአለም ሰላም፦ ደሕንነት መጥቀም መጉዳቱ ግን ያዉ ሜድቬዴቭ እንዳሉት በነሱዉ የሚወሰን ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic