የዩናይትድ ስቴትስ እቅድ፤ ኢራቅና አፍቃኒስታን | ዓለም | DW | 02.03.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የዩናይትድ ስቴትስ እቅድ፤ ኢራቅና አፍቃኒስታን

ኦባማ ሥልጣን በያዙ በሰላሳ ዘጠነኛ ቀናቸዉ አደረጉት።

default

ኦባማ

«ዛሬ እዚህ የመጣሁት የኢራቁ ጦርነት እንዴት እንደሚያበቃ ልነግራችሁ ነዉ።»

ፕሬዝዳንት ባራክ ሁሴይን ኦባማ።ከገቧቸዉ ብዙ ቃላት ያአንዱ ገቢራዊነት አንድ አለ።የኢራቅ። አርብ።ከአርብ-ከኢራቅም በፊት የአፍቃኒስታኑ ነበር።ቃል-ሁለት።ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።ጦርነት በሚያደቃቸዉ-ሐገራት ጦር የመቀነስ-መጨመሩ ተቃራኒ ቃል እቅድ ተቃርኖ እስከየትነት፣ የእዉነታዉ እንዴትነት የዉጤቱ ምንነት ያፍታ ቅኝታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁኝ ቆዩ።

ድምፅ

ድፍን አለምን አነጋግሯል።የአብዛኛዉ አለም ሕዝብን፣ የፍትሕ፣ የመብት ተሟጋቾችን ለተቃዉሞ ሠልፍ አሳድሟል።የሐገራት መሪዎችን ቅሬታ አስከትሏል።አንዱም ግን በጦር ከታበዩት ልብ የሚደርስ-እርምጃቸዉን የሚገታም አልነበረም።ስድስት አመቱ።ኦባማ ሥልጣን በያዙ በሰላሳ ዘጠነኛ ቀናቸዉ አደረጉት።

ድምፅ

«ተዋጊ ብርጌዶቻችንን በአመት ከመንፈቅ ጊዜ ዉስጥ እናስወጣ የሚለዉን የጊዜ ሠሌዳ መርጫለሁ።ሥለዚሕ ይሕን በተቻለች መጠን ሁሉ በግልፅ ልናገር።ኦገሰት ሰላሳ አንድ ሁለት ሺሕ አስር ኢራቅ የምናደርገዉ የዉጊያ ተልዕኮ ያበቃል።»

የኦባማ እቅድ አርብ እንደተሰማ አሜሪካዊዉ የፖለቲካ ሳይንስ አዋቂ ፔተር ፊቨር «ቡሽ ኢራቅ ዉስጥ በገነቡት ድልድይ» ይላሉ «ኦባማ ተሸጋገሩ-እና ድልድዩን አጋዩት»።ፊቨር እንደፃፉት የቡሽ መስተዳድር የአሜሪካ ጦርን በ2005-እና ስድስት (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከኢራቅ ለማስወጣት አቅዶ ነበር።

በሥድስት ዋና ዋና ምክንያቶች ያጠነጠዉ እቅድ-ሲከሸፍ ሌላ እቅድ ወጥቶ-እንደነበርም የሚያትቱት ፊቨር-ኦባማ አርብ ያወጁት እቅድ በቡሽ እቅድ ላይ የተመሠረተ ግን መሠረቱን የደነበቀ ነዉ-ባይ ናቸዉ።የቡሽ መስተዳድር አቅዶ ከነበር-እቅዱ እንደ ወረራዉ አላማ ሁሉ ዉሉን ከሳተ-አጠያያቂዉ ኦባማ ዉል አልባዉን እቅድ ከመዉረሳቸዉ ይልቅ እቅዱ የከሸፈበት ሰበብ-ምክንያት በሆነ ነበር።

የአለምን-ከአለምም የየመረጣቸዉን ሕዝብ ጩሐት ረግጠዉ፣ የአባት-ቀዳሚዎቻቸዉን መርሕ፣ የአለምን ሕግ ጥሰዉ፣ የባለሙያችን ጥቆማ፤ የወዳጆቻቸዉን ምክር ደፍልቀዉ በሐሰት መረጃ ሉአላዊ ሐገር ያስወረሩት የያኔዎቹ የዋሽንግተን-ለንደን መሪዎች ምግባር በጎ ሕሊና ባለዉ ዘንድ ዛሬ ከታወሰ ከካቡል-እስከ ባግዳድ፤ ከአቡ ግራይብ እስከ ዋንታናሞ በዋሉት ግፍ-በደል አለመጠያቀቸዉ እንጂ እቅዳቸዉ መሆኑ አጠራጣሪ ነዉ።

አርብ የታወጀዉ እቅድ በርግጥ በቡሽ-ብሌር እብሪት ያለቀዉን ሚሊዮን ኢራቃዊ፣ ኢራቅ በረሐ የቀረዉን አራት ሺሕ አምስት መቶ አሜሪካዊ ሕይወት አይመልስም።በመቶ ሺሕ የሚቆጠረዉን ቁስለኛ አይፈዉስም።በኢራቅ ከአራት ሚሊዮን ለሚበልጠዉ ስደተኛ ካሳ፣ ወደ ሐገሩ የመመለስ ዋስትና የጠፋችዉን ሐገር መጠገኛም በርግጥ አይሆም።

የባግዳዱ ነዋሪ እንዳለዉ ግን ለኢራቆች የነፃነት ምልክት ነዉ።

ድምፅ

«የአሜሪካ ወታደሮች መዉጣት የኢራቅ ሕዝብ ሙሉ ነፃነቱን ተጎናፀፈ ማለት ነዉ»

ወይም ሌላዉ ባግዳዴ እንዳለዉ ሌላ ይሆን ይሆናል።

ድምፅ

«ወታደሮቹ መዉጣታቸዉ ዩናይትድ ስቴትስ ኢራቅ ዉስጥ የገጠማትን ሽንፈት የሚያጎላ ነዉ»

በዚሕም ብሎ በዚያ የእልቂት ፍጅቱን ዑደት ለመቀነስ፣ የአለም ሕዝብን የስድስት አመት ጥያቄ ለመመለስ የመጨረሻዉ መጀመሪያ መሆኑ ግን አያነጋግርም።

ለኦባማ ደግሞ እቅዱን ከየትም ያምጡት ከየት የምርጫ ዘመቻ ቃላቸዉን የመጠበቃቸዉ ዋቢ፣ የቡሽ መስተዳድር ያጎደፈዉን ሐገራቸዉን ሥም ለማደስ፣ የወታደሮቻቸዉን ከንቱ ሞት ለመቀነስ፤ የሚከሰከሰዉን በትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ለመቆጠብ፣ የአፍቃኒስታኑን ዘመቻ ለማጠናከር ከልብ ለማለማቸዉ እማኝ ነዉ።

ድምፅ

«ከሁሉ በፊት ቅድሚያ የምሰጠዉ ኢራቅ የሚገኙት የወታደሮቻችንና ሰላማዊ ዜጎቻችን ደሕንነት ነዉ።ሥለዚሕ በጣም በጥንቃቄ እንቀሳቀሳለን።ሥለሁኔታዉ እዚያ ካሉት የጦር አዛዦቼ እና ከኢራቅ መንግሥት ጋር በቅብና በተደጋጋሚ እወያያለሁ።ይሕ እቅድ የጦር ሐይላችን ለኢራቅ ወዳጆቻችን የሚያስፈልጉትን ድጋፍ ለመስጠትና እንዲሳካለቸዉ ለማገዝ እንዲችል ያደርጋል።»

በእቅዱ መሰረት አብዛኛዉ ተዋጊ ጦር ከአመት ከመንፈቅ በሕዋላ ሲወጣ ከሰላሳ-አምስት እስከ ሐምሳ ሺሕ የሚደርሱ ወታደሮች እዚያ ቆይተዉ የኢራቅን ሐይል ያደራጃሉ።ይረዳሉም።በሁለት ሺሕ አስራ-አንድ ማብቂያ ሁሉም ወታደር ጠቅልሎ ይወጣል።

የፋርስ ባሕረ-ሠላጤን ፖለቲካዊ ዉጥንቅጥ የሚያስነትኑ አዋቂዎች በተደደጋጋሚ እንዳሉት ቡሽ-ብሌር ኢራቅን መዉረራቸዉ ከማንም በላይ የጠቀመዉ ኢራንን ነዉ።

Irak Iran Präsident Machmud Ahmadinedschad und Jalal Talabani in Bagdad

ጠላባኒ ከኢራኑ አቻቸዉ አሕመዲነጃድ ጋር

አብዛኞቹ አረብ ጎረቤቶቿ ሳዳምን አስቀድመዉ ስምንት አመት የወጓት፣ የቴል አቪቭ፤ የዋሽንግተን ለንደኖች ቀንደኛ ጠላት ፣የጆርጁ ቡሿ ሁለተኛ የሰይጣን ዛቢያ የደማስቆን ወዳጅነት ለማግኘት፣ በሒዝቡላሕ በኩል በሊባኖስ፣ በሐማስ በኩል በፍልስጤ ላይ ተፅኖዋን ለማሳረፍ ብዙ መድከም መልፋት ነበረባት።

ኢራቅን ግን ቡሽ-ብሌር ያዘመቱት ጦር የሳዳም ሁሴንን መንግሥት አስወገደላት።የሳዳምን ቤተ-መንግሥት ከኢራኖች ጋር የሺዓ እምነትን ለሚጋሩት፤ ኢራን ለኖሩ፤ ኢራን ለተማሩት፣ ሐይላት አስረከበላት።

የአዉሮጳ ሕብረት ዋና መንበሩን ኢራቅ ባደረገዉ ኢራን ሕዝባዊ ሙጃሒዲያን በእንግሊዝኛ ምፃሩ (PMOI) በተሰኘዉ የኢራን ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ላይ ጥሎት የነበረዉን ያሸባሪነት ፍረጃ ባለፈዉ ጥር አንስቷል።ሕብረቱ ለዘመናት የፀናዉን ፍረጃ ለማንሳቱ የሰጠዉ ሰበብ-እና እዉነታኛዉ ምክንያት በርግጥ ብዙ ያነጋግራል።

የሕብረቱ ዉሳኔ እንደተሰማ ግን የኢራቅ ጠቅላይ ሚንስትር የፀጥታ ጉዳይ አማካሪ ሙዋፍቅ አል-ሩባይ «እጃቸዉ በኢራኖች ደም የተነከረ» ያሏቸዉን የኢራን ደፈጣ ተዋጊዎች ከኢራቅ እንደሚባረሩ አስታወቁ።የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላሕ አሊ ሐማኒ ባለፈዉ ቅዳሜ ቴሕራን የገቡት የኢራቅ ፕሬዝዳት ጀላል ጠላባኒ ሙጃሒዲያኑን እንዲያስረክቧቸዉ ይሕ ቢቀር ከኢራቅ እንደሚያባርሯቸዉ እርግጠኛ ናቸዉ።

እስላማዊት ሪፐብሊካቸዉ አፍንጫ ሥር ላለፉት ስድስት አመታት የሰፈረዉ በእሳቸዉ ቋንቋ «የትልቋ ሰይጣን» ትልቅ ጦር ሙሉ በሙሉ ለቅቆ መዉጣቱን ግን ይጠራጠራሉ።ሐማኒ ለጎረቤት እንግዳቸዉ እንደነገሩት የባግዳድ መሪዎች ዩናይትድ ስቴትስ ጦርዋን አርብ ካስታወቀችዉ ጊዜ ቀደማ እንድታስወጣ መገፋፋት ቋሚ የጦር ሠፈር እንዳትከፍት መከልከል አለባቸዉ።

ጀላል ጠላባኒ-የቴሕራን መሪዎችን ትዕዛዝ አከል ጥያቄ ሲያደምጡ ቅዳሜ እንደ ጠላባኒ ሁሉ ከግን ከሳቸዉ አመት ከመንፈቅ ቀድመዉ አሜሪካኖች ካቡል ቤተ-መንግሥት የዶሏቸዉ ሐሚድ ካርዛይ በሕግ-ከተያዘዉ ጊዜ በፊት ምርጫ ጠርተዋል።

ኻርዛይ የለጋ ዲሞክራሲያዊት አፍቃኒስታን ዲሞክራሲያዊ መሪ፣ እየተባሉ በቡሽ ሲንቆለጳጰሱ፣ ሲነደነቁ-ሲወደሱ ድፍን ሰባት አመት ከመስማት ማየታችን በስተቀር የአፍቃኒስታን ፀጥታ ለማሻሻል፤ የሕዝባቸዉን ኑሮ ለመለወጥ፤ የመንግሥታቸዉን መዋቅር ለማስፋፋት የተከሩት ብዙ የለም።

Sicherheitskonferenz München Hamid Karzai

ካርዛይ

የመከላከያ ሚንስትር ጄኔራል አብዱልረሒም ዋርዳክ የኻርዛይ መንግሥት በተለይ ፀጥታ ለማስከበር ብዙም አልጣረም የሚለዉን ወቀሳ አይቀበሉትም።

ድምፅ

«የአፍቃኒስታን ብሔራዊ ጦር ባለፉት ሰወስት አመታት ከተመዘገቡ የተሳኩ ታሪኮች አንዱ ነዉ።የለዉጥና የጥንካሬ ምሳሌ ሆኗል።የአዲስቱ አፍቃኒስታን ብቃት ማሳያ፥ ሐገሪቱ ራስዋን የመምራት አቅም እንዲኖራት የሚደረገዉ ጥረት ተጨባጭ አብነት ነዉ።»

ኻርዛይና ባለሥልጣኖቻቸዉ ግን ማድረግ የሚገባቸዉን ላለማድረጋቸዉ ሁሌም-ሁለት ሰበብ አያጡም።የአለም አቀፉ ማሕበረሰብ ድጋፍ ማነስ-አንድ፥ የፓኪስታን መንግሥት ሐገሩ የሸመቁ የታሊባን ደፈጣ ተዋጊዎችን አለመቆጣጠሩ-ሁለት።የፕሬዝዳት ኦባማ መስተዳድር አስራ-ሰባት ሺሕ፥ ሌሎቹ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ አባላት ደግሞ በሺ የሚቆጠር ተጨማሪ ወታደር ለማዝመት መወሰናቸዉ ለካቡል ባለሥልጣናት የመጀመሪያ ሰበብ በቂ መልስ ነዉ።

የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕክተኛ ሪቻርድ ሆል ብሩክ ደግሞ በቅርቡ አካባቢዉን መጎብኘታቸዉ፥ የአፍቃኒስታንና የፓኪስታንን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ዋሽግተን ጋብዘዉ ማነጋገራቸዉ ሁለተኛዉን ለማስወገድ ማለሙን ከአፍቃኒስታኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ከዶክተር ራንጊን ዳድፋር ስፓታ የቀረበ እማኝ በርግጥ አያስፈልግም።

ድምፅ

«ከፓኪስታን ጋር ሥላለን የጋራ ግንኙነት ያለዉ የምሥራች ዜና በአዲሱ የፓኪስታን ሲቢላዊ መንግሥትና በአፍቃኒስታን መንግሥት መካካል መተማመን መፈጠሩ ነዉ።ይሕ በኛ የጋራ ግንኙነት ታሪክ አዲስ ክስተት ነዉ»

የምሥራቹ ዜና እንዴትነት፥ የተጨማሪ ጦር ዘመቻ ተልዕኮ እስከምንነት አነጋግሮ ሳያበቃ ፕሬዝዳት ካርዛይ ለሐምሌ የተያዘዉን ምርጫ ሚያዚያ እንዲካሔድ ማወጃቸዉ ነዉ-ግራዉ።

==============

የኦባማ መስተዳድር መንታ-እቅድ የምርጫ ዘመቻ ቃልን ከመጠበቅ፥ ወጪን ከመቀነስም በላይ ለዩናይትድ ስቴትስ እና ለሁለቱ ሐገራት ሕዝብ የሰላም ተስፋ፥ ለአለም በጎ መልስ ሰጪ ነዉ። የኢራኖች እሽቅድምድም፥ ወረራ-ጦርነቱን ላለፉት ሰባት አመታት የመሩት ሐይላትና የደጋፊዎቻቸዉ ተቃዉሞ፥ በቡሽ መስተዳድር የተሾሙት የካቡልና የባግዳድ መሪዎች የብቃትና ፍላጎት እጠት ተስፋዉን እንዳያጨናጉለዉ እንጂ -ሥጋቱ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ZPR (Ö-Töne),Reuters,Afp,Wikipedia

Negash Mohammed,

Tekle Yewhala

►◄

ተዛማጅ ዘገባዎች