የዩናይትድ ስቴትስና የሰሜን ኮሪያ ፍጥጫ | ዓለም | DW | 09.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የዩናይትድ ስቴትስና የሰሜን ኮሪያ ፍጥጫ

የኮሪያ ሕዝባዊ ጦር መግለጫ እንዳስጠነቀዉ ጦሩ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የሰፈረበትን ጉዋምን ለመምታት ሥልት እያጠና ነዉ።በመግለጫዉ መሠረት አንደርሰን የተባለዉ የአሜሪካ አየር ኃይል ሠፈርን ጨምሮ ጉዋምን ሕዋሶንግ-12 በሚባለዉ ሚሳዬል መምታት የሚቻልበት ሥልት ይቀየሳል

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በሰሜን ኮሪያ ላይ የሠነዘሩት ዛቻ ከሐገራቸዉ ፖለቲከኞች ነቀፋ፤ከሰሜን ኮሪያ ደግሞ አፀፋ ዛቻ ገጥሞታል።ትራምፕ ከሚዝናኑበት ሥፍራ ሆነዉ ሰሜን ኮሪያ አደብ ካልገዛች ዓለም ከዚሕ ቀደም አይቶት በማያዉቀዉ «እሳት እና እቶን ትጋያለች።» በማለት ዝተዋል።አሜሪካዉያን የፖለቲካ አዋቂዎችና ዲፕሎማቶች የፕሬዝደንታቸዉን የዛቻ ቃላት፤ ዓለም ሊከላከለዉ የሚጥረዉ ዓይነት እና ከፒዮንግዮንግ መሪዎች የተቀዳ በማለት ክፉኛ ነቅፈዉታል።በዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ምክር ቤት የቻይናና የኮሪያ ጉዳይ የቀድሞ ኃላፊ ለዉራ ሮዘንበርገር እንዳሉት የትራምፕ ዛቻ የኑኩሌር ቦምብ የታጠቀችዉ ሰሜን ኮሪያ እንዳይሆን የምንፈልገዉን ጥቃት እንድትከፍት የሚገፋፋ ነዉ።ትራምፕ ዓለም አይቶት የማያዉቀዉን እሳትና እቶን እንደሚያዘንቡ የዛቱት ዩናይትድ ስቴትስ በጃፓን ከተሞች ላይ በጣለችዉ የአቶሚክ ቦምብ በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ጃፓናዉያን ያለቁበት 72ኛ ዓመት በሚከበርበት ሳምንት ነዉ።የሪፐብሊካን ሴናተር ጆን መኬይን የትራምፕ ዛቻ አሜሪካንን ወደ ከፋ ግጭት የሚከት ነዉ ብለዋል።ትራምፕ የሚሉትን በቅጡ እንዲያጤኑ አንጋፋዉ ፖለቲከኛ መክረዋልም።

ሰሜን ኮሪያ የትራምፕን ዛቻ በጠንካራ አፀፋ ዛቻ ነዉ ያጣጣለችዉ።በሐገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ የተነበበዉ የኮሪያ ሕዝባዊ ጦር መግለጫ እንዳስጠነቀዉ ጦሩ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የሰፈረበትን ጉዋምን ለመምታት ሥልት እያጠና ነዉ።በመግለጫዉ መሠረት አንደርሰን የተባለዉ የአሜሪካ አየር ኃይል ሠፈርን ጨምሮ ጉዋምን ሕዋሶንግ-12 በሚባለዉ ሚሳዬል መምታት የሚቻልበት ሥልት ይቀየሳል።ሰሜን ኮሪያ ዩናይትድ ስቴትስ ያቀደችዉን የጠብ አጫሪነት እርምጃ በሙሉ ለማክሸፍ ዝግጁ ነች-እንደመግለጫዉ።«ዩናይትድ ስቴትስ  ያቀደችዉ «አስቀድሞ መምታት» የተሰኘዉ የጠብ ጫሪነት ጦርነት በሁሉም መስክ አፀፋ ይገጥመዋል።ፍትሐዊ በሆነ ግን ዩናይትድ ስቴትስ ግዛት ዉስጥ የሚገኙ የጠላት ጠንካራ ይዞታዎችን  በሚያጠፋ ሁሉን አቀፍ ዉጊያ ይመከታል።»የሌሎች ሐገራት መንግሥታት ዛቻ ፉከራዉ የምር እንዳይሆን አንዳዶቹ እየተማፀኑ፤ሌሎቹ እየመከሩ ነዉ።ጀርመን የኮሪያ ልሳነ ምድርን ወታደራዊ ፍጥጫ ለማስወገድ ሩሲያና ቻይና አስፈላጊዉን ጥረት እንዲያደርጉ አደራ ብላለች።ፈረንሳይ ሁሉም ወገኖች ኃላፊነት እንዳያጓድሉ ጠይቃለች።ቻይና፤ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ዉጥረቱን ከሚያቀጣጥል ዛቻ እንዲታቀቡ መክራለች።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

 

 

 

ተዛማጅ ዘገባዎች