የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሰሞኑ ክራሞት | ባህል | DW | 14.10.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሰሞኑ ክራሞት

ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ያለፈውን አመት ተረጋግተው አላሰለፉም፡፡ በየግቢዎቻቸው በሚቀሰቀሱ ተቃውሞዎች ምክንያት ጉዳት ሲደርስ፣ ተማሪዎች ሲታሰሩ እና ትምህርት ሲቋረጥ እየተመለከቱ ነው ዓመቱ በአዲስ ዓመት የተተካው፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:23
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:23 ደቂቃ

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

 

በተወሰኑ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች ግርግር ሽሽት ትምህርታቸውን ጥለው ወደየመጡበት እስከመመለስ ደርሰዋል፡፡ ገሚሶቹ ነገሮች እስኪረጋጉ በአቅራቢያቸው ባሉ ከተሞች ለመቆየት ተገድደዋል፡፡

በመንግስት ላይ የሚደረገው ተቃውሞ እምብዛም አልነካቸውም በሚባሉ ዩኒቨርስቲዎች ያሉ ተማሪዎች ሳይቀር በሌሎች ቦታዎች የሚካሄደውን በመስማት ተረጋግቶ የመማር ችግር እንዳጋጠማቸው ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ ጭንቀት ጥበቱ የበረታው ደግሞ “ልጆቼ ትምህርት ይቀስሙልኛል” ብሎ ስንቅ ቋጥሮ፣ ገንዘብ ቆርጦ በየክልሎቹ ወደሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የአብራኮቹን ክፋይ በሰደደ ወላጅ ላይ ነበር፡፡ “በሰቀቀን ከማለቅ ትምህርት ጥንቅር ብሎ ይቅር” ሲሉ ልጆቻቸውን ወደቀያቸው እንዲመለሱ ያደረጉ ወላጆችም አሉ፡፡

ስሟ እንዲጠቀስ የማትፈልገው የሐሮማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የባለፈው ዓመት የዩኒቨርስቲ ክራሞቷን እንዲህ ታጋራለች፡፡ ለደህንነቷ ስንል ድምጿን ቀይረነዋል፡፡

ክረምት ግም ሲል ያረፈ የመሰለው የወላጅ እና የተማሪ ልብ መስከረም መጥባቱን ተከትሎ ዳግም ይረበሽ ይዟል፡፡ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች በቴሌቪዥን እና ሬድዮ የሚያስተላለፉትን የተማሪዎች ቅበላ ማስታወቂያ ተከትሎ ወደ ዩኒቨርስቲዎቻቸው የተመለሱ ነባር ተማሪዎች እንዳሉ ሁሉ ይቅርብን ብለው የተውት አልጠፉም፡፡ ልባቸው አልቆርጥ ብሎ በያሉበት ሆነው የሚዋልሉም አሉ።

ዶይቼ  ቬለ ያነጋገራቸው እና ባለፈው ዓመት ወደዩኒቨርስቲ የሚያስገባቸውን ፈተና ወስደው ባለፉ ተማሪዎች ግን ግራ መጋባት ይስተዋላል፡፡ ገሚሶቹ የቤተሰብ ምክር በመስማት ወደ ተመደቡባቸው ዩኒቨርስቲዎች መጓዙን ትተው በየአካባቢያቸው ባሉ ዩኒቨርስቲዎች ተመዝግበዋል፡፡

ንጉስ ፋሲል ከእነዚህ አንዱ ነው፡፡ በፈተና ውጤት 380 ነጥብ በማስመዝገብ በዲላ ዩኒቨርስቲ የተመደበው ንጉስ ቤተሰቦቹ በቦታው ያለውን ግጭት በማገናዘብ ወደቦታው እንዳይሄድ ስለከለከሉት አዲስ አበባ ለመቅረት መገደዱን ይናገራል፡፡

ንጉስ እርሱ ብቻ ሳይሆን ሁለት ጓደኞቹም በተመሳሳይ ሁኔታ ወደተመደቡባቸው ዩኒቨርስቲዎች ላለመሄድ መወሰናቸውን ይናገራል፡፡ ሁለቱም ጓደኞቹ የኢንጂነሪንግ ትምህርት ለማጥናት የመረጡ ሲሆን አርባ ምንጭ እና መቀሌ ዩኒቨርስቲ ደርሷቸው ነበር፡፡ አማራጭ ያገኙት አዲስ አበባ ያሉ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመሆናቸው የፍላጎታቸውን ሳይሆን ሌላ የትምህርት አይነት እንዲያጠኑ ተገድደዋል፡፡ 

ከንጉሱ እና ጓደኞቹ በቤተሰብ ግፊት የተመኙትን ባያገኙም በሀዋሳ የሚገኙ ተማሪዎች ግን መላ ቢጤ ፈጥረው ወደተመደቡበት ቦታ ለመጓዝ ቆርጠው ቀናቸውን አየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡ ምደብ ቦታቸው ደግሞ ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል ለተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ቀዳሚ የነበረችው እና ብዙ ሁነት ያስተናገደችው ጎንደር ናት፡፡ በከተማይቱ ያለውን ሁኔታ ቀድመዋቸው ወደ ቦታው ከተጓዙ የአካባቢያቸው ነባር ተማሪዎች ይከታተላሉ፡፡ “ነገሮች ተረጋግተዋል” ብለው የሚያምኑት ወጣቶች ሰብሰብ ብለው ወደ ጎንደር ለመሄድ ተዘጋጅተዋል፡፡

ስሙን መግለጽ የማይፈልገው የተጓዡ ስብስቡ አባል ቡድን መመስረት ያስፈለጋቸው በመጓጓዣ በኩል ላለመቸገር እንደሆነ ያስረዳል፡፡  የሀዋሳው ወጣት “በቂ ሰላም አለ” ፣ “አሁን ያለው ሁኔታ የመማር ማስተማር ሂደቱን አያውክም” ብሎ ቢያንም የሐሮማያዋ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ግን በግቢዋ “አስፈሪ ድባብ” አለ ትላለች፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳለ የዩኒቨርሲቲው መምህር ተስፋዬ አለማየሁ ያስረዳል፡፡ በተማሪዎች ዘንድ ካለው ውጥረት ባሻገር በመምህራን ዘንድም “ሰላማዊ የትምህርት ከባቢ” ለመፍጥር ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አክሎ ገልጿል፡፡ 

የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀውስ  ስጋት እና ጭንቀትን እንደፈጠረ አለ፡፡ የመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ተጽእኖውን አሳርፏል፡፡ የመማሪያ፣ የጥናት እና የፈተና ጊዜን አስተጓጉሏል፡፡ ከሁሉ የከፋው ግን በተማሪዎች ላይ የሚፈጥረው የስነ-ልቦና ጭንቀት ነው፡፡ የሐሮማያ ተማሪዋ ጉዳቱን እንዲህ ታብራራዋለች፡፡

በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ የሚጓዙት ተማሪዎች ሌላ አሳሳቢ ጉዳይ ከፊታቸው ተደቅኗል፡፡ ሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጋ በበርካታ መብቶች ላይ እቀባ ጥላለች፡፡ በዘመነ ቴክኖሎጂ ያዩ የሰሙትን ማጋራት የሚቀናቸው የዘመኑ ወጣቶች ከማህበራዊ ድረ ገጾች ታግደው እርስ በእርስ መገናኛቸው ተበጥሷል ወይም በእጅጉ መንምኗል፡፡ በነጻነት የመናገር፣ የመሰብሰብ እና ሰላማዊ ሰልፍ የማካሄድ መብቶቻቸው ላይ የተጣሉ እገዳዎችን ይዘው የዘንድሮ የትምህርት ዓመትን “ሀ” ብለዋል- መጪውን በስጋት አሻግረው እያዩ፡፡  ሙሉ ዝግጅቱን ከድምፅ ዘገባዉ ያድምጡ። 

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic