የዩኒቨርሲቲዎች ሁኔታ በኢትዮጵያ  | ኢትዮጵያ | DW | 21.12.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የዩኒቨርሲቲዎች ሁኔታ በኢትዮጵያ 

በኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በላይ የዘለቀዉ የፖለቲካ ቀዉስ የማኅበረሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ከማወኩም በተጨማሪ በየደረጃዉ የመማርና ማስተማር ሂደቱ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ እየታየ ነዉ። ተማሪዎች በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ትምህርት ገበታቸዉ በመመለስ ላይ መሆናቸዉ ቢገለፅም በሌላ በኩል ግን አሁንም «የመማሪያ ክፍሎች  ባዶ»  መሆናቸዉ ተሰምቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:54

የመማር ማስተማሩ ሒደት መስተጓጎል

የመንግሥትም ሆነ ለመንግሥት ቅርበት ያላቸዉ መገናኛ ብዙሃን የሚፋለሱ መረጃዎችን እያወጡም ይገኛሉ። ለምሳሌ ትናንት ራዲዮ ፋና «በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ተቋርጦ እንደማያውቅ» የዩኒቨርሲቲውን ዓለም አቀፍ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ዶክተር ዓለማየሁ ዘውዴ ጠቅሶ ዘግቧል። ኢቢሲ ደግሞ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተገኝቶ «ባደረገው ቅኝት የመማር ማስተማር ሂደቱ መቋረጡን» ከተማሪዎች ለመረዳት መቻሉን ዛሬ ገልጿል። 

በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አሁንም ትምህርት እንደሌለ ቢገለፅም አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ግን ቀስ በቀስ ወደ መማርና ማስተማሩ ሂደት እየገቡ እንደሆነ የአገር ዉስጥ ዘገባዎች ያመለክታሉ።

የፖለቲካ አለመረጋጋቱ ተፅዕኖዉን ካሳረፈባቸዉ ዩኒቨርሲቲዎች ዉስጥ ሃሮማያ፣ መቱ፣ ወለጋ፣ አምቦ፣ አዳማ፣ ወልድያ፣ ጎንደር፣ ባህርዳር፣ አዲግራት ዩኒቨርሲቲዎች ይጠቀሳሉ። በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ በሁሉም ግቢዎች ትምህርት መጀመሩን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳን ጠቅሰዉ የአገር ዉስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።  በተቃራኒዉ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አሁንም «የመማሪያ ክፍሎች  ባዶ ሆነው የመማር  ማስተማሩ ሂደትም እንደተቋረጠ መቀጠሉን» ዘገባዎቹ አክሎበታል።

ከ14ሽ በላይ ተማሪዎችን በሚያስተናግደው አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል ግጭት ከተከሰተ በኋላ ተማሪዎችን ሰብስቦ በማነጋገር የጋራ መግባባት ስለተፈጠረ ተማሪዎቹ ከዛሬ ሳምንት ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ወደ መማር ማስተማር ተመልሰዋል የሚሉት የዩኒቨርሲቲዉ የሕዝብ ግኑኝነት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ከበደ ናቸዉ።

ከባለፈዉ ማክሰኞ ጀምሮ ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ገሚሹ ተማሪ ወደ ቤተሰብ ተመልሷል የሚሉት የዩኒቨርሲቲዉ ተማሪ ናቸዉ። የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዉ በትናንትናዉ ዕለት የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ትምህርት መጀመራቸዉን እንደሰሙና እንዲሁም ወልድያም ቀስ በቀስ ወደ ትምህርት እየተመለሱ እንደሆነ መስማታቸዉን ይናገራሉ። 

በኢትዮጵያ ከ30 በላይ የሕዝብ ዩኒቨርሲቲዎች ሲኖሩ በዚህ ዓመት ብቻ 137, 137 አዲስ ተማሪዎችን መቀበላቸዉን የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንስ መረጃ ያመለክታል።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic