የዩሮፖል የኢንተርኔት ጸረ-ሽብር ዘመቻ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 03.07.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የዩሮፖል የኢንተርኔት ጸረ-ሽብር ዘመቻ

የአውሮጳ ፖሊስ መሥሪያ ቤት በእንግሊዘኛ ምኅፃሩ Europol የአሸባሪ ቡድኖች እና የጽንፈኞች የኢንተርኔት ፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ለመመከት በተጠናከረ ኃይል መንቀሳቀስ መጀመሩ ተገለጠ። እራሱን «እስላማዊ መንግስት» እያለ የሚጠራው አሸባሪ ቡድን በማኅበራዊ መገናኛ ዘርፎች መስፋፋቱን ለመመከት ዩሮፖል እንቅሳቃሴ በአዲስ መልክ መጀመሩ ተጠቅሷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:08
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:08 ደቂቃ

የዩሮፖል የኢንተርኔት ጸረ-ሽብር ዘመቻ

ፕሮፓጋንዳ የማንኛውም ጦርነት አንድ አካል ነው። በተለይ ሽብርተኝነት መሠረቱን የሚያደላድለው ፍርሃትን የሚያነግሱ እና ጥላቻን የሚያሠርፁ መልእክቶች እንዲስፋፉ በማድረግ ነው። እራሱን «እስላማዊ መንግስት» እያለ የሚጠራው አሸባሪ ቡድን ማለትም IS ማኅበራዊ መገናኛ ዘርፎችን መዋቅሩን የበለለጠ ለመዘርጋት ተጠቅሞባቸዋል። በነዚህ የማኅበራዊ መገናኛ ዘርፎች ጥላቻ እና ፕሮፖጋንዳ በማሠራጨትም ቡድኑ አዳዲስ አባላቶችን በተለይም ወጣቶችን ለማማለል ይጠቀምበታል ተብሏል። አሜሪካ የሚገኘው ብሩኪንግስ ተቋም በIS የትዊተር አጠቃቀም ላይ ከዛሬ ሦስት ወራት በፊት ጥናት አከናውኖ ነበር።

በጥናቱ መሠረት እንደ ጎርጎሪዮሣዊው አቆጣጠር በ2014 የIS ደጋፊዎች የትዊትር ቁጥር 46 ሺህ ገደማ እንደሚደርስ ተገምቷል። እያንዳንዱ አባልም በስሩ እስከ አንድ ሺህ የሚደርሱ አባላት አሉት ተብሏል። እነዚህ አባላት ወጣት ሴቶችን ጨምሮ ታዳጊዎችን ለማማለል ጥረት ያደርጋሉ ሲል ጥናቱ አትቷል።

በቅርቡ እንኳን አንድ ታዳጊ ወጣት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በትዊተር ለIS የገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ ጥረት ሲያደርግ ተይዞ ፍርድ ቤት መቅረቡ ተዘግቦ ነበር። ይኽን መሰሉን በኢንተርኔት ለአሸባሪዎች የሚደረግ ድጋፍ የአውሮጳ ፖሊስ መሥሪያ ቤት፤ ዩሮፖል በተጠናከረ መልኩ መዋጋት እንደሚሻ ገልጧል። ሆኖም ለዚህ ተግባር የተሰየመው የዩሮፖል የኢንተርኔት ቡድን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ቪል ፋን ጌሜርት ቡድናቸው ተግዳሮት እንደሚገጥመው ሳይጠቅሱ አላለፉም።

«በእርግጠኝነት ለመናገር እያንዳንዱን መልእክት የማስወገዱ አቅም የለንም። ሆኖም እጅግ አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው ለማድረግ እንጥራለን። በዚህም መሠረት ምርመራዎችን ለመጀመር ብቃቱ አለ። እናም በርግጠኝነት የጽንፈኝነት ፍንጮች ወይንም የዓመፃ ድርጊቶች በአባል ሃገራት ውስጥ በቸልታ አይታለፉም»

የኢንተርኔት ላይ የሽብር ማስፋፋት ዘመቻዎችን እና ፕሮፓጋንዳዎችን ለመከታተል እና ለመመከት የተቋቋመው ቡድን ጂሐዲስቶች ላይ ጥብቅ ክትትል በማድረግ አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚከታቸውም አስታውቋል።

ቡድኑ የሽብርተኝነት እና የጽንፈኝነት አዝማሚያ የታየባቸው ግለሰቦችን ለመከታተል ሦስት አበይት ተግባራትን እንደሚያከናውን ይፋ አድርጓል።

«በመጀመሪያው ለዓመጻ እና ለጽንፈኝነት ጥሪ የሚያስተላልፉ የኢንተርኔት መልእክቶችን እንለያለን። በመቀጠል መልእክቱ የተላለፈበት የመገናኛ ተቋም የተላለፈው መልእክት ከተቋሙ መርኅ ውጪ መሆኑን እንዲያውቀው ይደረጋል። ከዚያም ከዚያ ገጽ ላይ መልእክቱ ይሰረዛል።»

ይኽም ብቻ አይደለም የዩሮፖል መርማሪዎች የኢንተርኔት መልእክቱን መሠረት በማድረግ ለክስ የሚያበቁ ምርመራዎችን እንዲጀምሩ ያስችላቸዋል ተብሏል።

እራሱን «እስላማዊ መንግስት» እያለ የሚጠራው አሸባሪ ቡድን በተለይ በትዊተር የመገናኛ ዘርፍ የሚያደርገው የሽብር እና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በኢንተርኔት የጸረ-ሽብር ዘመቻ ሊመከት ይገባዋል ሲል ዩሮፖል እንቅስቃሴውን በስፋት መያያዙ ተነግሯል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic