የዩሪ ጋጋሪን 50 ኛ ዓመት፤ የጠፈር ጉዞ መታሰቢያ፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 06.04.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የዩሪ ጋጋሪን 50 ኛ ዓመት፤ የጠፈር ጉዞ መታሰቢያ፣

ከትናንት ማክሰኞ አንስቶ እስከመጪው ማክሰኞ ሚያዝያ 4 ቀን 2003 ደረስ ፤ በኅዋ ሳይንስ ተመራማሪው ዓለም፣ በተለይም በሩሲያ ፣ አንድ ሰው፣ ከ 50 ዓመት በፊት ታሪካዊ ድርጊት ያከናወነበት ተልእኮ፣ በልዩ ትውስታ ሲዘከር ይሰንበታል።

default

የሩሲያ የጠፈር መንኮራኩር ማምጠቂያ «ሶዩዝ» ሮኬት፣ በባይኖኩር፤ ካዛኽስታን

ከትናንት ማክሰኞ አንስቶ እስከመጪው ማክሰኞ ሚያዝያ 4 ቀን 2003 ደረስ ፤ በኅዋ ሳይንስ ተመራማሪው ዓለም፣ በተለይም በሩሲያ ፣ አንድ ሰው፣ ከ 50 ዓመት በፊት ታሪካዊ ድርጊት ያከናወነበት ተልእኮ፣ በልዩ ትውስታ ሲዘከር ይሰንበታል። ጤናይስጥልኝ እንደምን ሰነበታችሁ? በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ዝግጅታችን፤ በዓለም ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ እ ጎ አ ሚያዝያ 12 ቀን 1961 ዓ ም ፣ ከባቢ አየርን ሰንጥቆ ፣ በኅዋ ፣ ዓለምን በመዞር ፤ የአንድ ሰዓት ከ 48 ደቂቃ በረራ ስላደረገው ሩሲያዊው ጠፈርተኛ (ኮስሞኖት) ዩሪ አሌክሴየቪች ጋጋሪን አጭር ትውስታ ይሆናል የምናቀርብላችሁ።

(ድምፅ)-------

ወደ ኅዋ በመጓዝ የመጀመሪያ ለሆነው ዩሪ ጋጋሪን ክብር ሲባል፣ ወይም 50ኛ ዓመት ታሪካዊ የኅዋ ጎዞውን በማስታወስ፤ ትናንት 3 ጠፈርተኞች፣ 2 ሩሲያውንና አንድ አሜሪካዊ ፣ ዩሪ ጋጋሪን ከተላከበት፣ በካዛኽስታን ከሚገኘው ባይኮኑር የጠፈር ጣቢያ በሶዩዝ የጠፈር መንኮራኩር ወደ ዓለም አቀፉ የጠፈር የምርምር ጣቢያ ተጉዘዋል። የሩሲያ የኅዋ ምርምር ድርጅት ዋና ኀላፊ አናቶሊ ፐርሚኖቭ፤ በቦታው በመገኘት፤ ጠፈርተኞቹን፣ አሌክሳንደር ሳሞኩታየቭ፤ አንድሬ ቦሪሴንኮንና አሜሪካውዊውን ሮናልድ ጌረንን፣ ጉዞው እንዲሳካላቸው በመመኘት ተሰናብተዋቸዋል። ጠፈርተኞቹ ፣ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ የሰጡትን ሃይማኖታዊ ስዕልና የመንኮራኩሯ መሪ የጠፈርተኛ ሳሞኩታየቭ ሴት ልጅ ያበረከተችውን የውሻ አሻንጉሊት ተቀብለው ወስደዋል።

ከ 50 ዓመት በፊት ጠፈርን ያሰሰው ዩሪ ጋጋሪን ፣ ከጠፈር ልብሱ ጋር ምስሉና ያኔ ለጉዞ ሲነሳ፤ የተናገረው መፈክር፣ «ፖየሐሊ!» የሚለው ቃል በተቀረጸበት ሶዩዝ መንኮራኩር የተጓዙት ጠፈርተኞች ዛሬ ሌሊቱን፤ ከዓለም አቀፉ የኅዋ ምርምር ጣቢያ ይደርሳሉ፤ ፖየሐሊ ማለት በሩሲኛ (እንሂድ! እንሥግስ) እንደማለት ነው። ከዩሪ ጋጋሪን በኋላ በዛ ያሉ ጠፈርተኞች፤ ቱሪስቶች ጭምር ኅዋ እየደረሱ ተመልሰዋል። ጋጋሪን ጠፈር ደርሶ ከተመለሰ

ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ፤ አላን ሼፐርድ ወደ ኅዋ በመውጣት የመጀመሪያው አሜሪካዊ ጠፈርተኛ ለመሆን በቅቷል። እ ጎ አ በ 1963 ፣ ሩሲያዊቷ ቫሌንቲና ቴሬሽኮቫ፤ ኅዋን የቃኘች በዓለም ውስጥ የመጀመሪያቷ ሴት ለመባል በቃች። አሜሪካዊው ኒል አርምስትሮንግ እ ጎ አ ሐምሌ---ቀን 1969 ዓ ም፤ ጨረቃ ላይ በማረፍ ዓለምን አስደመመ። ከጀርመናውያን ኅዋን የዳሰሰ የመጀመሪያው ጠፈርተኛ ፣ የያኔዋ የጀርመን ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ(ምሥራቅ ጀርመን) ተወላጅ ዚግሙንድ የን ነበር። በኅዋ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ የጠፈር ጣቢያ እ ጎ አ በ 2001 ዓ ም20 ሚሊዮን ዶላር ገደማ በመክፈል የጎበኙ የኅዋ ቱሪስት ዴኒስ ቲቶ የተባሉት ከበርቴ አሜሪካዊ መሆናቸው የሚታወስ ነው።

ህይወት ያለው ተንቀሳቃሽ ፍጡር፤ ከካባቢ አየር ውጭ ኅዋ ደርሶ ለመመለስ፤ ሰው ሳይሆን ቀዳሚው ውሻ ነበረ። እ ጎ አ በኅዳር ወር 1957 ዓ ም፤ የያኔዋ ሶቭየት ኅብረት፤ አሁን ሩሲያ ፣ ላይካ የተባላች ወሻ ወደ ኅዋ ልካ ነበር ። ይሁንና ውሻይቱ በህይወት አልነበረም የተመለሰችው። በዓመቱ በታኅሳስ የተላከች ጦጣም እንዲሁ በህይወት ጉዞዋን አላጠናቀቀችም። ከዚያ በኋላ፤ ትላትልና ዔሊ ጭምር ወደ ኅዋ መላካቸው ይታወሳል።

እጅግ ረዘም ላለ ጊዜ፣፤ ማለትም ከ 2 ዓመት በላይ በኅዋ የኖረው ሰርጌይ ክሪካልዮቭ የተባለው ሩሲያዊ ጠፈርተኛ ነው። 6 ጊዜ ወደ ኅዋ ተጉዞ፤ በዚያ 803 መዓልትና ሌሊት አሳልፏል። ያላማቋረጥ ለረጅም ጊዜ በኅዋ ጊዜውን ያሳለፈው፣ ማለትም MIR በተሰኘችው የሩሲያ የጠፈር ቤተ-ሙከራ የቆየው ሌላው ሩሲያዊ ኮስሞኖት ቫለሪ ፖልያኮቭ ነው። እ ጎ አ ከጥር ወር 1994 ዓ ም አንስቶ እስከ መጋቢት 1995 ዓ ም ድረስ በጠቅላላ 437 ቀን ከ 17 ሰዓት ነበረ ኅዋ ላይ የቆየው። ወደፊት ማርስ ደርሶ ለመመለስ ለሚደረግ ዝግጅት ፤ ሩሲያውያኑ ጠፈርተኞች የተሻለ ተመክሮ ያካበቱ ይመስላሉ።

በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ፣ የሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ ምርምርን ፣ አለቦታው ከርእዮት ልዩነት ጋር በማያያዝ ጭምር ይፎካከሩ የነበሩት ሩሲያና ዩናይትድ እስቴትስ፣ በአሁኑ ጊዜ በኅዋ ምርምር ረገድ በሰፊው ሲተባበሩ ነው የሚታዩት። ጠፈርተኞችን ከእንግዲህ ወዲያ ፣ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ወደ ዓለም አቀፉ የምርምር ጣቢያ የምታጓጉዝ የሩሲያ የጠፈር መንኮራኩር ሶዩዝ ብቻ ትሆናለች። የዩናይትድ እስቴትስ፣ የበረራ ምርምርና የኅዋ አስተዳደር መ/ቤት ( NASA) የራሱን የማጓጓዣ መንኮራክሮች ተልእኮ ከእንግዲህ የሚያቆም በመሆኑ፤ ወደፊት ለተጠቀሰው ዓይነት ጉዞ፣ በሩሲያ የጠፈር መንኮራኩር መመካት ግድ ሊሆንበት ነው። አሜሪካዊው ጠፈርተኛ ሮናልድ ገራን የሩሲያን የጠፈር መንኮራኩር አስተማማኝነት አስመልክቶ እንዲህ ብሏል።

5,«እንደሚመስለኝ፤ ሶዩዝ ሮኬትና የኅዋ መንኮራኩሮቹ አስተማማኝነታቸው ባለፉት ጊዜያት ከተከናወኑ ተግባሮች አኳያ በግልጽ የሚመሠከርላቸው ናቸው። በብዙ የመንኮራኩር የማምጠቅ ተግባር ያጋጠመው እንከን ጥቂት ነው። ችግር ሲያጋጥምም፤ ሩሲያውያኑ ወዲያውኑ መፍትኄውን ፈልገው ያገኙለታል። የመንኮራኩር የአሠራር ዘዴ በጣም አስተማማኝ ነው።»

በሞስኮ ለኅዋ ምርምርና ጉዞ ትምህርት በሚሰጥበት ከፍተኛ ተቋም የሚገኘው የ 19 ዓመቱ ተማሪ ኮንስታንቲን በበኩሉ እንዲህ ብሏል።

8,«ሩሲያ ፣ በሶቭየት የአገዛዝ ዘመን በነበረው ፣ ኮሮሊዮቭ በቀየሱት የሮኬትና መንኮራኩር ሥራዋ ልትኮራ ይገባል። ያኔ የነደፈው ሥነ ቴክኒክ እስከዛሬ ድረስ በማገልገልና የአሜሪካን የረቀቀ ሥነ ቴክኒክ የተቋቋመ ነው። ይሁንና አሁንም ሥነ ቴክኒኩን በተጨማሪ ማሻሻል ይኖርብናል። ይህን ካላደርግን በዚህ የምርምር መስክ ልንራመድ አንችልም።»

ትናንት ወደ ኅዋ የተጓዙት 3ቱ ጠፈርተኞች፤ ዓለም አቀፉ የኅዋ የምርምር ጣቢያ ውስጥ 6 ወራት የሚያሳልፉ ሲሆን፣ በዚያም ከሌሎቹ 3 ባልደረቦቻቸው፤ አሜሪካዊቷ ጠፈርተኛ ካትሪን ኮልማን ፤ ኢጣልያዊው ፓዖሎ ኔስፖሊና ሩሲያዊው ዲሚትሪ ኮንድራትየቭ ጋር ይገናኛሉ። ከ 50 ዓመት በፊት ፤ ከምድራችን ውጭ ሌሎች ዓለማትንም ሆነ የኅዋ አካላት መጎብኘት የሚቻልበትን ፈር የቀደደው ዩሪ ጋጋሪን በአንድ ጄት አኤሮፕላን ልምምድ ላይ ተጋጭቶ ፤ እ ጎ አ በ 1968 ዓ ም በ 34 ዓመት የጎልማሳ ዕድሜው ህይወቱን ማጣቱ የሚታወስ ነው።

ሩሲያ በኅዋ ምርምር ረገድ ምንጊዜም ሰፊ ምርምር ከማካሄድ እንደማትቦዝን ጠ/ሚንስትሯ ቭላዲሚር ፑቲን አስታውቀዋል ። ሩሲያ፣ ዘንድሮ ለኅዋ ምርምር ብቻ 2,8 ቢሊዮን ዩውሮ መድባለች። 50ኛውን ዓመት የዩሪ ጋጋሪንን ተልእኮ አስመልክተውም ፑቲን እንዲህ ነበረ ያሉት።

«ከኅዋ ጋር የተያያዘ ማንኛውም ነገር ለሩሲያ ከታሪኳ ጋር የተሣሠረ ብቻ ሳይሆን ፣ ብሔራዊ ኩራቷም ነው። የሀገራችን ተወላጆች፤ ኮንስታንቲን ሲሎኮቭስኪ፤ ሰርጌይ ኮሮሊዮቭና ዩሪ ጋጋሪን የአያሌ ሺ ዘመናት የሰው ልጆችን የኅዋ ጉብኝት ህልም እውን ለማድረግ አብቅተዋል። ለሳይንስና ሥነ ቴክኒክ እንዲሁም ለማኅበራዊ የኤኮኖሚ ልማት በአጠቃላይ የምድራችንን የሥልጣኔ አድማስ እጅግ እንዲሰፋ ለማድረግ አስችለዋል።»

ከ 50 ዓመት በፊት ፤ በዓለም ውስጥ የመጀመሪያው ሰው ወደ ኅዋ የተጓዘበት 50 ዓመት ሚያዝያ 4 ቀን 2003 ዓ ም(የፊታችን ማክሰኞ)በሚታሰብበት ክብረ-በዓል፣ ከ 40 የተለያዩ አገሮችና አካባቢዎች የኅዋ ምርምር ጣቢያዎች/መ/ቤቶች የተውጣጡ ኀላፊዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል። ዩሪ ጋጋሪን ወደ ኅዋ የተጓዘበት 50ኛ ዓመት ከተዘከረ በኋላ፣ በሣልስቱ ፤ የሩሲያው የኅዋ ምርምር መ/ቤት ኀላፊ አናቶሊ ፐርሚኖቭ ከዩናይትድ እስቴትሱ የበረራና የኅዋ ምርምር መ/ቤት (NASA) አስተዳዳሪ ቻርለስ ቦልደን ጋር ተገናኝተው ይመክራሉ። በሌላ በኩል፣ ምንም እንኳ ሩሲያ በኅዋ ምርምር ረገድ ብዙ የተሣካ ውጤት ብታገኝም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፣ መንኮራኩር የማምጠቂያ መርኀ ግብሮች በተደጋጋሚ የተሸጋሸጉበትና አንድ አስተማማኝ ያልሆኑ ሁኔታዎች የተከሠቱበት አጋጣሚ መኖሩን የጠቀሱ የኅዋው ምርምር መ/ቤት ባልደረቦች፤ አሁን የ 65 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ፐርሚኖቭ፤ ከእንግዲህ ከአመራር ሥራ ገለል ቢሉ ይሻላል በማለት ተቃውሞ ጭምር በማንጸባረቅ ላይ ናቸው።

«ኖቮስቲ ኮስሞናቭቲኪ» የተሰኘው መጽሔት ዋና አዘጋጅ ኢጎር ማሪኒንየኅዋ ምርምርና ጉዞ 2 ዐበይት ተጋርጠውበታል ባይ ናቸው።

7 «አንዱ ችግር አመራር ነው። ሠራተኞችን የሚያነቃቃ የሚያስደሥት አያያዝ አይደለም ያለው። አንድ ዐቢይ የሥራ አቅድ ወደ ማርስ በረራ ማድረግ ሊሆን ይችላል። ሁለተኛው ችግር የሠራተኞች አያያዝ ነው። የኅዋ ምርምር ሠራተኞች ጥሩ ደመወዝ ሊከፈላቸው ይገባል። በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ኢንጂኔሮች፤ ከሌሎቹ ሠራተኞች ከ 20 እስከ 30 ከመቶ ብልጫ ያለው ደመወዝ ይከፈላቸው ነበር። በሩሲያ የአስተዋይ ሰዎች እጥረት አጋጥሞ አያውቅም። አሁን ግን የኅዋ ምርምርና ጉዞ፣ ብዙ ሰዎችን እስከዚህም የሚያጓጓ አልሆነም»።

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ

ተዛማጅ ዘገባዎች