የየካቲት 27/2013 ዓ/ም የዓለም ዜና | ዓለም | DW | 06.03.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የየካቲት 27/2013 ዓ/ም የዓለም ዜና

የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ጉዳይ ላይ ለመወሰን ለሁለኛ ጊዜ ያደረገው ሙከራ ያለስምምነት ተበተነ። ምክር ቤቱ በአየርላንድ አቅራቢነት በትግራይ ክልል ግጭቱን ለማስቆም ጣልቃ መግባትን በሚጠይቀው ረቂቅ ላይ ህንድ ፣ ሩስያ እና በተለይም ቻይና በድጋሚ ተቃውመውታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:52

የየካቲት 27/2013 ዓ/ም የዓለም ዜና

የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ጉዳይ ላይ ለመወሰን ለሁለኛ ጊዜ ያደረገው ሙከራ ያለስምምነት ተበተነ። ምክር ቤቱ በአየርላንድ አቅራቢነት በትግራይ ክልል ግጭቱን ለማስቆም ጣልቃ መግባትን በሚጠይቀው ረቂቅ ላይ ህንድ ፣ ሩስያ እና በተለይም ቻይና በድጋሚ ተቃውመውታል። ትናንት ዓርብ ምሽት ያለውጤት የተቋጨው የምክር ቤቱ ሁለተኛ ቀን ስብሰባ ከስምምነት ተደርሶ ቢሆን በኢትዮጵያ ላይ ጠንከር ያለ መግለጫ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ያወጣ እንደነበር የሶስቱ ሀገራት ዲፕሎማቶች አስታውቀዋል። በአየርላንድ የቀረበው መግለጫ ጣልቃ ገብነት አልያም ማዕቀብ እንዲጣል መጠየቅ በውል የለየ አልነበረም ሲል  የአሶሽየትድ ፕረስ ዘግቧል። ነገር ግን በትግራይ ክልል የሰፈነው አመጽ እና ግጭት እንዲያበቃ ጥሪ መቅረቡን ገልጿል። ቻይና አመጽ እና ግጭትን ማስቆም በሚል በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ሊገባ አይገባም ብላለች ። የሰብአዊ ድጋፎችን ማድረስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ማተኮር እንደሚገባ ለምክር ቤቱ ማሳወቋን እንዲሁም ህንድ በኋላ ላይም ሩስያ የቻይናን ሃሳብ መደገፋቸውን ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ዲፕሎማቶች ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

የግብጹ ፕሬዚዳንት አብደል ፈታህ አል ሲሲ ለይፋዊ ጉብኝት ዛሬ ወደ ሱዳን ካርቱም ተጉዘዋል። አል ሲሲ በሱዳን በሚኖራቸው ቆይታ በሁለቱ ሀገሮች ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ግንኙቶችን ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ያተኩራሉ ተብሏል። ካይሮ እና ካርቱም በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ላይ በማተኮር እንደሚወያዩ አልሲሲ አስታውቀዋል። ፕሬዚዳንቱ  የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር ከስልጣን ከተወገዱ ወዲህ የመጀመርያ በሆነው በዚሁ የካርቱም ጉብኝታቸው የሱዳኑ ሉዓላዊ የሽግርር ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን በብሔራዊ ቤተ መንግስት ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ፕሬዚዳንታዊ ጉብኝቱ ሁለቱ ሀገራት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መቀራረብ ማሳየታቸውን ተከትሎ መካሄዱን የአሶሽየትድ ፕረስ ዘግቧል። በቀድሞው የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሀሰን ኦማር አልበሽር የስልጣን ዘመን በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው ግንኙነት በሀገራቱ አዋሳኝ አካባቢዎች በሚገኘው እና ሁለቱም ሀገሮች ይገባናል በሚሉት  የሀላየብ ሶስት ማዕዘን ምክንያት በውጥረት የተሞላ ነበር። ሃላየብ አሁን በግብጾች ቁጥጥር ስር ይገኛል። ሃገራቱ ያለፉትን አስር አመታት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ሲያደርጉ የነበረው ውይይት ኢትዮጵያ ጥቅሟን ለማስጠበቅ በያዘችው ጽኑ አቋም ከስምምነት ሳይደርሱ መዝለቃቸው ምናልባትም ችግሮቻቸውን ወደ ጎን ትተው ወደ ትብብር ለመምጣታቸው ማሳያ ሳይሆን እንዳልቀረ ተዘግቧል።

በሶማሊያ የአሸባብ ታጣቂዎች በሞቃዲሾ ባደረሱት የቦምብ ጥቃት የሟቾች ቁጥር 20 ደረሰ። ታጣቂዎቹ ትናንት ዓርብ ምሽት በአንድ ምግብ ቤት ላይ ባደረሱት ጥቃት ከሞቱት ውጭ 30 ሰዎች መሞታቸውን መንግስታዊው የሶማሊያ ዜና ምንጭ ዘግቧል። ታጣቂዎቹ በመዲናይቱ ሞቃዲሾ ተወዳጅ የሆነውን የሉል ያማኒ ምግብ ቤትን ኢላማ ያደረገ የቦምብ ጥቃት ማድረሳቸውን የሀገሪቱ ፖሊስ ቃል አቃባይ ሳዲቅ አሊ አዳን ተናግረዋል። በምሽቱ ጥቃት ምግብ ቤቱን ጨምሮ በአቅራቢያው በሚገኙ መኖርያ ቤቶች ላይ ብርቱ ጉዳት የደረሰ ሲሆን የሟቾች ቁጥርም መጨመሩ ተዘግቧል። በሶማሊያ ሊደረግ ታቅዶ የነበረው ሀገር አቀፍ ምርጫ መዘግየቱን ተከትሎ በመዲናዋ ሞቃዲሾ ለዛሬ የተቃውሞ ሰልፍ ተጠርቶ ነበር። በዚህም የጸጥታ ችግር ሊከሰት ይችላል በሚል ስጋት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደራዊ ሃይል በከተማዋ ተሰማርቶ እንደነበር የፈረንሳይ ዜና ምንጭ ዘገባ ያመለክታል። ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ የተቃውሞ ሰልፉ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል። በሶማልያ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው የተነገረለት አሸባብ ትናንት በቦሳሶ አንድ ማረሚያ ቤት ወሮ ሰባት የመንግስት ወታደሮችን ገድሎ በርካታ ታሳሪዎችን ከእስር ማስመለጡ ተዘግቦ ነበር።

በየመን በመንግስት ደጋፊዎች እና በኢራን በሚደገፉ የሀውቲ (ሁቲ) አማጽያን መካከል በተደረገ ውግያ በትንሹ 90 ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ የመንግስት ወታደራዊ ምንጮች አስታወቁ። ባለፈው 24 በተደረገው በዚሁ ውጊያ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች መቁሰላቸውም ተነግሯል።  የሺዓ አማጽያን በሳዑዲ መራሹ ወታደራዊ ጥምረት በሚደገፈው የየመን መንግስት ጠንካራ ይዞታ እንደሆነች የተነገረላት ማሪብን ለመቆጣጠር ካለፈው ወር ጀምሮ ጠንከር ያለ ጥቃት ከፍተዋል። የማሪብ ከተማ በአማጽያኑ እጅ ከወደቀች ለመንግስት ከፍተኛ ኪሳራ ነው ያለው የፈረንሳይ ዜና ምንጭ ዘገባ በከተማው አቅራቢያ በረሃማ አካባቢዎች ለሰፈሩ ተፈናቃዮች ሕይወት እጅጉን አስጊ ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል። የዩናይትድስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን በለጋሾች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር በማሪብ ዙርያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የ191 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ መፈቀዱን አስታውቀው የሀውቲ አማጽያን በአካባቢው የሚያደርጉትን ጥቃት እንዲገቱ ጠይቀዋል።

ሩስያ በሰሜናዊ ሶርያ በአማጽያን ቁጥጥር ስር በነበረ አንድ ነዳጅ ማጣርያ ላይ በፈጸመችው የሚሳኤል ጥቃት አራት ሰዎች  ተገደሉ፤ ከ20 የሚልቁት ቆሰሉ። ፕሬዚዳንት በሽር አልአሳድን የምትደግፈው ሩስያ ትናንት አርብ ምሽት ከጦር መርከብ በተኮሰችው ሚሳኤል አሌፖ አቅራቢያ የሚገኙ በደርዘን የሚቆጠሩ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ጉድጓዶችን በእሳት ማጋየቷን የሶርያ የሰብአዊ መብቶች ታዛቢ ቡድን አስታውቋል። መቀመጫውን ብሪታንያ ያደረገው የታዛቢ ቡድኑ እንዳለው በጃራቡስ እና አልባብ ከተሞች  አቅራቢያ በደረሰው ጥቃቱ ከሟቾች አንዱ ብቻ የሶርያ አማጽያን ቡድን አባል ነበር ብሏል። የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በእሳት የተያያዘውን አካባቢ ወደ ሌሎች የነዳጅ ጉድጓዶች ከመዛመቱ በፊት በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት መጀመራቸው ተነግሯል። ቱርክ በምትቆጣጠራቸው የአሌፖ አካባቢዎች ከቅርብ ወራት ወዲህ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እየደረሰባቸው ሲሆን ከሞስኮም ሆነ የሶርያ መንግስት በኩል ግን ሃላፊነት ሲወስዱ አልተደመጡም። አስር ዓመታትን ያስቆጠረው የሶርያው የእርስ በእርስ ጦርነት ከ 387,000 በላይ ሰዎችን ህይወት ሲቀጥፍ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ደግሞ ከመኖርያ ቄዬኣቸው አፈናቅሏቸዋል።

 

Audios and videos on the topic