የየታዳሽ ኃይል-ምንጮች ዓለምአቀፍ ጉባኤ በቦን | ኤኮኖሚ | DW | 02.06.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የየታዳሽ ኃይል-ምንጮች ዓለምአቀፍ ጉባኤ በቦን

በጀርመን መንግሥት ጋባዥነት ለረዥም ጊዜ ሲዘጋጅ የቆየው፣ ታዳሽ የኃይል ምንጮችን የሚመለከተው ዓለምአቀፍ ጉባኤ ትናንት ቦን ውስጥ ተከፍቷል። በዚሁ ጉባኤ ላይ በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የኅብረተሰብእ ቡድኖች የተወከሉት ሀገራት ከ፩፻፶ ይበልጣሉ። በዓይነቱ መጀመሪያ፣ በይዘቱም እጅግ ግዙፍ በሆነው የዓለም ጉባኤ ላይ በጠቅላላው ፫ሺ የሚደርሱ ልኡካን ናቸው የሚሳተፉት። ዓርብ የሚፈፀመው የአራት ቀናቱ ጉባኤ የኃይል ምንጭ ጥያቄ ከተፈጥሮ ጥበቃ

default

�� ከልማትና ከዕቀዳ፣ በተለይ ደግሞ በድህነት አንፃር ከሚደረገው ትግል ጋር የሚመላከት ነው።

አማራጮቹና ታዳሾቹ የኃይል ምንጮች ፀሐይ፣ ነፋስ፣ ውሃ፣ ባዮማስ እና የምድር ሙቀት በመላው ዓለም ውስጥ በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውሉበትን መንገድ የሚጠቁመው ዓለምአቀፍ ጉባኤ በጀርመን የልማት ትብብር ሚኒስትሪት ሃይደማሪ ቪቾረክ-ትሶይል እና በጀር,መን የተፈጥሮ ጥበቃ ሚኒስትር ዩርገን ትሪቲን ሊቀመንበርነት ነበር የተመራው። ከመንግሥት ወኪሎች ጎን፥ ብሔራዊና ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የዓለም ባንክን የመሳሰሉ ዓለምአቀፍ ተቋማት፣ የተባ መ የተፈጥሮ ጥበቃ ድርጅት፣ የተባ መ የእንዱስትሪያዊ ዕድገት ድርጅት፣ የአማራጭ ኃይልምንጭ አራማጅ ኩባንያዎች፣ ሙያ-ማኅበራትና ሌሎችም ብዙ የኅብረተሰብእ ቡድኖች መድረክ ያገኙበት ጉባኤ ሊዘጋጅ የቻለው፣ የጀርመን መራሔ-መንግሥት ጌርሃርት ሽረደር በመሥከረም ፲፱፻፺፭ የዘላቂውን ልማት መንገድ የተመለከተው ዓለምአቀፍ ጉባኤ በጆሃንስበርግ/ደቡብ አፍሪቃ በተካሄደበት ወቅት ይህንኑ የታዳሽ ኃይልምንጮች ጉባኤ ለማስተናገድ በገቡት ቃል መሠረት ነው።

ጀርመናዊቱ የልማት ትብብር ሚኒስትሪት ሃይደማሪ ቪቾረክ-ትሶይል ጉባኤው በተከፈተበት ወቅት እንደገለፁት፣ አሁን እየናረ የተገኘው የነዳጅ ዘይት ዋጋ አማራጩ የኃይል ምንጭ በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውልበት ርምጃ ተፋጥኖ እንዲነቃቃ ግዴታ ያደርጋል። የምድርዘይት ንጣፍ እየተበዘበዘ የሚሟጠጥበትም ሂደት ነው የአማራጭና የታዳሽ ኃይልምንጮችን ልማት አጣዳፊ ጉዳይ የሚያደርገው። ከዚህም በላይ፣ ሚኒስትሪቱ እንደሚያስገነዝቡት፣ የፖለቲካ ውዝግቦችና ጦር’ነቶች የምድርዘይትን አቅርቦት ያፋልሱታል፥ ዋጋውን ያመጥቁታል፤ ይህም ነው አማራጩን የኃይል ምንጭ ግዴታ የሚያደርገው። የነዳጅዘይት ቀውስ በተለይም በሚደረጁት ሀገራት ኤኮኖሚዎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በቀላሉ የሚገመት አይሆንም። በተለይ ደግሞ፣ ሚኒስትሪቱ እንደሚሉት፣ የምድር ዘይትንና ከሰልን በመሳሰሉት የተፈጥሮ ቅሪቶች የሚሸፈነው የተለምዶው ኃይልምንጭ አዋዋል ለተፈጥሮ ጓዳ ከባድ ጭነት መሆኑም ነው አብሮ መታሰብ ያለበት። የምድርዘይትን፣ የምድር ጋዝንና ከሰልን የመሳሰሉት የተፈጥሮ ቅሪቶች በአየር ላይ ከባድ ብክለት ነው የሚያደርሱት፤ ያየር ብክለት ለሰው ጤንነት ከባድ ጠንቅ ነው የሚሆነው።

ስለዚህ፣ ነባሮቹ የኃል ምንጮች--የምድርዘይት፣ የምድርጋዝ፣ ከሰል እና የአቶም ኃይል ሙጋድ ኡራን ተፈጥሮን በማይበክሉት ታዳሽና ንፁሕ የኃይል ምንጮች--ማለት በፀሐይ ሙቀት፣ በነፋስና በውሃ ኃይል፣ በባዮማስ እና በምድር ሙቀት እርከን በእርከን መተካት ይኖርባቸዋል። ባሁኑ ስሌት መሠረት፣ አሁን ከጠቅላላው የኃይል ምንጭ ፍጆታ ወደ ፲፬ በመቶ የሚጠጋው የታዳሽ ኃይልምንጮች ድርሻ በሚቀጥሉት ፲፭ ዓመታት ውስጥ--እ ጎ አ እስከ ፪ሺ፳ ድረስ--ወደ ፳ በመቶ ከፍ የሚል እንደሚሆን ነው ተሥፋ የሚደረገው።

ለጉባኤው መድረክ እንደተመለከተው፣ ታዳሽ የኃይል ምንጮች በተለይም በሚደረጁት ሀገራት ገጠር አካባቢዎች በድህነት አንፃር ለሚደረገው ትግል ከፍተኛ ድጋፍ ሆነው ነው የሚታዩት። ይኸውም፣ የልማት ትብብር ሚኒስትሪቱ በጉባኤው መክፈቻ ሥርዓት ላይ እንዳስረዱት፣ በራስ ሀገር ውስጥ የሚገኙት ታዳሾቹ የኃይል ምንጮች ተነቃቅተው በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውሉበት አማራጩ ር’ምጃ ድሆቹ ሀገሮች ለውዱ የኃይል ምንጭ አቅርቦት በውጭ ሀገር የሚከሰክሱትን ግዙፍ ወጭ እየቆጠቡ በገጠሩ አካባቢ ለልማት መርሐግብር እንዲያውሉት፣ የኮሬንቲውን መረብ እንዲያስፋፉበት እና በድህነት አንፃር ለሚደረገው ትግል እንዲጠቀሙበት የሚያስችላቸው ይሆናል። ይኸው አማራጭ የኃይል ምንጭ መንገድ ጥንካሬ፣ የተፈጥሮ ጥበቃ ሚኒስትሩ ዩርገን ትሪቲንም እንደሚሉት፣ ዛሬ የኮሬንቲ ዕድል ለማያገኙት ፪ ሚሊያርድ ሕዝቦች የኑሮውን ብርሃን ያወጣላቸዋል።

ኢትዮጵያና ስለ አማራጭ የኃይል ምንጭ ግብዓታቸው ትርኢት ያቀረቡ ብዙ የአፍሪቃ ሀገሮችም በሚሳተፉበት ግዙፍ ጉባኤ ፍፃሜ ላይ “የቦን አዋጅ” የተሰኘ አንድ የጋራ ሠነድ እንደሚቀርብ ይጠበቃል። ስለዚህና ስለሌሎችም የጉባኤ ይዘቶች በሚቀጥለው ጊዜ ሰፋ ያለ ዘገባ እናቀርባለን።