የየመን ጦርነት፤የዉጪ ኃይልና የአካባቢዉ ሠላም | ዓለም | DW | 22.08.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የየመን ጦርነት፤የዉጪ ኃይልና የአካባቢዉ ሠላም

ሳዑዲ አረቢያ እና ተባባሪዎቿ የመን ላይ የሚጥሉትን ቦምብና ሚሳዬል የምትሸጥላቸዉ፤ የጦርና የስለላ አማካሪዎችን ያዘመተችላቸዉ ዩናይትድ ስቴትስ ናት።የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ለመብት ተሟጋቾቹ ጥሪ፤ የሰጡት መልስ የመንን የሚደበድበዉን ጦር የሚያማክሩ የስለላና የጦር ባለሙያዎች ቁጥርን እንቀንሳለን የሚል ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:22

የየመን ጦርነት፤የዉጪ ሐይልና የአካባቢዉ ሠላም

የሪያድ ገዢዎች በ«ሰወስት ወር» ለማጠናቀቅ ቃል ገብተዉ የጀመሩት የአዉሮፕላን ድብደባ የመንን እያወደመ ነዉ።ዓመት ከመንፈቁ።የየመን ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ከሪያድ-እስከ ዤኔቭ፤ ከኦማን እስከ ኩዌይት ያደረጉት የሠላም ድርድር ያመጣዉ ዉጤት የለም።ዉጊያ ጦርነቱ ብሷል።የመን እየጠፋች፤ ሕዝቧ እያለቀ፤እየተራበ-እየተፈናቀለ ነዉ።የመብት ተሟጋቾች የሕዝቡ እልቂት፤ ስቃይ-ሰቆቃ እንዲቆም ይማፀናሉ።ሕዝቡም በአደባባይ ይሰለፋል።ሥለ-ሠላም ይጮሐል።ሰሚ ይኖረዉ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

የመኖች «ጉዞዉ ረጅም፤ አድካሚና አሰልቺ ቢሆንም ሰነዓ መድረስ ግድ ነዉ» የሚል የቆየ አባባል አላቸዉ።ከብዙ ዓመታት ዉዝግብ፤ ከደም አፋሳሽ ጦርነት፤ ፖለቲካዊ ሽኩቻ በኋላ ሰነዓን የተቆጣጠሩት የሁቲ ሸማቂዎች ያቺን ጥንታዊ፤ ታሪካዊ፤ዉብ ከተማን ሙጥኝ እንዳሉ ነዉ።ሰነዓንም ሥልጣናቸዉንም-ለሁቲዎች ጥለዉ የሸሹትን ፕሬዝደንት አብዱ ረቦ መንሱር ሐዲን በሐይል ወደ ሥልጣን ለመለስ የመንን በጦር ጄት የሚደበድቡት የሳዑዲ አረቢያ ነገሥታትና ተከታዮቻቸዉ በርግጥ መንገዱ ሳይረዝምባቸዉ አልቀረም።አስራ-ሰባት ወራቸዉ።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሸምጋይነት ከሪያድ እስከ ዤኔቭ፤ ከመስካት እስከ ኩዌት ያጓዘዉ ድርድር፤ ዉይይት የፖለቲካ ሽኩቻ፤ ሽጥርና ሴራም የሪያድ ገዢዎች እንዳሰቡት ሰነዓን መቆጣጠር አላስቻላቸዉም።

የየመን ሕዝብ በ2011 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ለተከታታይ ወራት ያደረገዉ የአደባባይ ሰልፍ-ተቃዉሞ ሰነዓ ላይ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመስረት ያለመ ነበር።ሕዝባዊዉ ሰልፍ አመፁ የዓሊ አብደላ ሳሌሕን አምገናዊ ሥርዓት አስወግዶ የያኔ ምክትላቸዉን አብድ ረቦ መንሱርን ከመተካት ባለፍ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ሰነዓ ላይ ማስፈን አልቻለም።ሰነዓዎች በራት ዓመታቸዉ እንደገና ተሰለፉ።ቅዳሜ።የሰነዓ አደባባዮችን ያጥለቀለቀዉ ሕዝብ ቁጥር የሰነዓዉ ተባባሪ ወኪላችን ግሩም ተክለ ሐይማኖት እንደታዘበዉ በየመን የቅርብ ዘመን ታሪክ ታይቶ አይታወቅም።

የሰልፉ ምክንያት፤ የሰልፈኛዉ ጥያቄና ፍላጎት ግን እንደየመኖቹ «አጃኢብ» ማሰኘቱ አልቀረም።ግሩም ይነግረናል።ዓሊ አብደላ ሳላሕ የዘይዲያሕ እስልምና ሐራጥቃ መከተላቸዉ የመንን ከሰላሳ ዓመታት በላይ በብረት ጡንቻ ከመግዛት አላገዳቸዉም ነበር።በዘመነ-ሥልጣቸዉ ከሐገራቸዉ ሐያል ጎረቤት ከሳዑዲ አረቢያ፤ ወይም ከምዕራባዉያን ጋር የተቀያየሙበት ጊዜ ከነበረ በ1990 ኢራቅ ስትወረር ወረራዉን መቃወማቸዉ ነበር።ቅያሜዉም ብዙም አልቆየ።ከኢራን ጋር የወገኑበት ወይም መወገናቸዉ የተነገረበት ጊዜም አልነበረም።

የቀድሞዉ የደቡብ የመን ጄኔራል አብድ ረቦ መንሱር ሐዲ የዓሊ አብደላ ሳላሕ ምክትል ለመሆን ወይም ሰነዓ ለመድረስ አድካሚዉን ጉዞ የጀመሩት የደቡብ የመንን ሶሻሊስታዊ ሥርዓት በማፈራረስ ነበር።ሐዲ ሶሻሊስት፤ ኮሚኒስት፤ የደቡብ ተወላጅ፤ወይም ሱኒ ሙስሊም መሆናቸዉ በዛይዲያሁ ዓሊ አብደላ ሳላሕ ለመታዘዝ ያገዳቸዉ ነገር አልነበረም።

በልማዱ የሁቲ አማፂያን ተብለዉ የሚጠሩት የዛይዲሕ ሐራጥቃ ፖለቲከኞች ሰነዓን ከተቆጣጠሩ በኋላ ዋና መሪ ያደረጉት ሳሌሕ ዓሊ አል-ሳማድን ነዉ።ዓሊ አብደላ ሳላሕ ከሥልጣን ተወግደዉ የፕሬዝደትነቱን ሥልጣን አብድ ረቦ መንሱር ሐዲ ከተረከቡ በኋላ፤አል ሳማድ፤ የአብድ ረቦ መንሱር ሐዲ ልዩ የፖለቲካ አማካሪ ነበሩ።

የሐይማኖት ሐራጥቃ፤የትዉልድ ሥፍራ፤ያለፈ ፖለቲካዊ ዳራ ሳይገድባቸዉ ባንድ ወቅት እንደ ፕሬዝደንት እና እንደ ምክትል ፕሬዝደት፤ እንደ ፕሬዝደንትና እንደ ልዩ አማካሪ ባንድ አብረዉ ሲሰሩ የነበሩት ፖለቲከኞች የገጠሙት ጠብ የሐይማኖት ሐራጥቃ ልዩነት መልክና ባሕሪ መላበሱ በርግጥ አደናጋሪ ነዉ።በአደናጋሪ ምክንያት የተቀጣጠለዉን ጠብ ሰወስቱ ፖለቲከኞች ማብረድ አለመቻላቸዉ ደግሞ ግራ አጋቢ።መርገብ የሚችለዉ ጠብ ተካርሮ ወትሮም ያልደላዉን ሕዝብ መፈጀት፤ ማስራብ፤ ማፈናቀሉ አሳዛኝ ሐቅ።

የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት ግን ለአሳዛኙ እልቂት የሚያደናግር፤ግራ የሚያጋባም ሚስጥር የለም።ምክንያቱም-ጦርነቱ የየመኖች ብቻ አይደለም።የሱኒ-ሺዓዎች ወይም የፋርስ-ዓረቦች ግጭት ብቻም አይደለም።የሞስኮ-ዋሽንግተን-

ብራስልሶች ጠብም ጭምር እንጂ።ባለፈዉ ቅዳሜ አደባባይ የወጣዉን ሕዝብ አቋም መፈክር የተከታተለዉ ጋዜጠኛ ግሩም ተክለ ሐይማኖትም እንደታዘበዉ ጦርነቱ ከየመኖች እጅ መዉጣቱን ሕዝቡን ሳይረዳዉ አልቀረም።ግሩም እንደሚለዉ በተለይ ምዕራባዉያን የመኖች እንዲታረቁ አይፈልጉም የሚሉ ሰልፈኞችም ነበሩ።

ዓሊ አብደላ ሳላሕ የሚመሩት አል ሞጠማር አ-ሻዕቢይ አል አም የተሰኘዉ የፖለቲካ ፓርቲ እና የሁቲ አማፂያን በቅርቡ የሽሽግግር ወይም ጊዚያዊ ያሉትን መንግሥት ወይም ምክር ቤት አቋቁመዋል።የየመንን ጉዳይ እንከታተላለን የሚሉት የአስራ-ስምንት ሐገራት የአምባሳደሮች ቡድን የምክር ቤቱን መመሥረት «የተናጥልና፤ ለሰላም የማይበጅ» በማለት ተቃዉሞታል።

በአብዛኛዉ ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራቸዉ የአዉሮጳና የአረብ መንግሥታትን የሚያስተናብረዉ ቡድን፤ ጋዜጠኛ ግሩም ተክለ ሐይማኖት እንደሚለዉ፤ የሽግግር መንግሥቱን ከመቃወሙ እኩል የመን ሕዝብ ላይ የሚፈፀመዉን ግድያም የተቀበለዉ ይመስላል።

ከአስራ-ስምንቱ ሐገራት አንዷ ሩሲያ ናት።ይሁንና ሩሲያ በዩክሬን ሰበብ ከምዕራባዉያን ጋር ከተቃቃረች ወዲሕ የምዕራባዉያን ጥቅም ዘንበል ባለበት ሥፍራ ሁሉ ገፋ-አድርጋ ጨርሶ ከመገልበጥ ወደ ኋላ አትልም።ምዕራባዉያንም፤ አረቦችም፤ ተከታዮቻቸዉም ሰነዓ የሚገኝ የኤምባሲ ፅሕፈት ቤቶቻቸዉን ሲዘጉ የሩሲያዉ እንዳለ ነዉ።የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ከቀድሞዋ ደቡብ የመን ጋር የነበራት ጠንካራ ግንኙነት ሞስኮዎች ሰነዓ ላይ የወዳጅነቱን ድር ለማድራት ጥሩ ወጋግራ ይሆናቸዋል።

ሥልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን የዋሽግተን-ሪያዶች ታማኝ ታዛዥ ይመስሉ የነበሩት ዓሊ አብደላ ሳላሕ በቀደም ለሩሲያ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት መግለጫ ቡድናቸዉ ወይም የመሠረቱት የሽግግር መንግሥት አሸባሪነትን ለመዋጋት ከሩሲያ ጋር መተባበር ይፈልጋል ብለዋል።ሩሲያ ከፈለገች የየመን አዉሮፕላን ማረፊዎችና ወደቦችን መጠቀም ትችላለች ብለዋልም።ሳላሕ ያሉትን ማድረግ መቻላቸዉ በርግጥ አነጋጋሪ ነዉ።

መልዕክቱ ግን የምዕራባዉያንና የአረብ ታዛዦቻቸዉን ጫና ለማስቆም ሞስኮዎች ይግቡልን ነዉ።በዚሕም ሰበብ የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት የየመኑ ጦርነት ይበልጥ እየተወሳሰበ ብዙ ወገኖች እያጣቀሰ ነዉ።ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር በየመን ላይ በሚፈፅመዉ የአየር ድብደባ አስር ሺዎች አልቀዋል።

መኖሪያ ቤቶች፤ ሐኪም ቤቶችን፤ ትምሕር ቤቶችን፤ መደብሮችና ሌሎች የሕዝብ አገልግሎት መስጪያ ተቋማት ወድመዋል።ድንበር የለሽ ሐኪሞች የተሰኘዉ ዓለም አቀፍ ግብረ-ሠናይ ድርጅት የሚያስተዳድረዉ ሆስፒታል በመዉደሙ በጦርነቱ የሚጎዱ ሰዎችን ማከሙን አቋርጦ ከየመን ወጥቷል።

በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀመዉ ግድያ እንዲቆም ሌሎች ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች እየጠየቁ ነዉ።ሳዑዲ አረቢያ እና ተባባሪዎቿ የመን ላይ የሚጥሉትን ቦምብና ሚሳዬል የምትሸጥላቸዉ፤ የጦርና የስለላ አማካሪዎችን ያዘመተችላቸዉ ዩናይትድ ስቴትስ ናት።የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ለመብት ተሟጋቾቹ ጥሪ፤ጥያቄና ጮኸት በቀደም የሰጡት መልስ የመንን የሚደበድበዉን ጦር የሚያማክሩ የአሜሪካ የስለላና የጦር ባለሙያዎች ቁጥርን እንቀንሳለን የሚል ነዉ።

በያዝነዉ ሳምንት አጋማሽ ሪያድን የሚጎበኙት የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ ለሪያድ ገዢዎች የሚሉትን አናዉቅም።ሪያዶችና ተባባሪዎቻቸዉ ግን ያቺ የኖሕ ልጅ ሼም መሠረታት የምትባለዉን ከተማ በዕለታት ዕድሜ ለአብድ ረቦ መንሱር ሐዲ እናስረክባለን እያሉ ነዉ።

ሰነዓ-በጣም የተከለለች ወይም በጠንካራ ምሽግ የታጠረች እንደማለት ነዉ።የአስራ-ሰባት ወራቱ ቦምብ ሚሳዬል እስካሁን ምሽጓን አልሰበረዉም-ከእንግዲስ ፉከራዉ ይይዝ ይሆን? ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic