የየመን ጊዜያዊ ሁኔታ | ዓለም | DW | 26.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የየመን ጊዜያዊ ሁኔታ

ሰሜናዊውን የመን ቀደም ሲል ፤ ከዚያም ካለፈው መስከረም አንስቶ መዲናይቱን ሰንዓን የተቆጣጠሩት ሁቲ አማጽያን፣ መላይቱን ሀገር ለመቆጣጠር ወደ ደቡብ በመዝመት የአደንን የወደብ ከተማ ለመያዝ በተጠጉበት ወቅት፤

የሳውዲ ዐረቢያ እና የሌሎች ጎረቤት ሀገራት የጦር አይሮፕላኖች በየመን ፕሬዚደንት አቤድ ራቦ ማንሱር ሀዲን አንፃር የሚዋጉትን እና የሁቲ ዓማፅያን ጦር ሠፈሮችን ትናንት ሌሊት መደብደባቸው ተገለጸ። በየመን ጦር እና ባይን እማኞች ዘገባ መሠረት፣ ጥቃት የጀመሩት የሳውዲ ተዋጊ ጄቶች ዒላማ ያደረጉት በመዲናይቱ ሰንዓ በሚገኙት የሁቲ ሚሊሺያዎችን ሠፈሮች ነው። ዐረባውያቱ ሀገራት በየመን ውዝግብ ጣልቃ የገቡት የየመን ፕሬዚደንት ከጥቂት ቀናት በፊት ያቀረቡትን የርዳታ ጥሪ በመቀበል መሆኑን በዩኤስ አሜሪካ የሳውዲ ዐረቢያ አምባሳደር አደል አል ሹቤይር አስታውቀዋል።

« ሕጋዊው የየመን መንግሥት እንዳይወድቅ እና ከውጭ ሚሊሺያዎችም አስጊ ሁኔታ እንዳይደቀንበት የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። በወቅቱ እያየነው ያለነው ሮኬቶች እና ከባድ የጦር መሳሪያ፣ እንዲሁም፣ የራሱ አየር ኃይል ያለው የሚሊሺያ ቡድንን ነው። ታሪክን መለስ ብዬ ስመለከት የራሱ አየር ኃይል ያለው ወይም አየር ኃይሉን የተቆጣጠረ የሚሊሺያ ቡድን አይቼም ሰምቼም አላውቅም። እና ይህ በጣም አደገኛ ሁኔታ ነው። በመሆኑም የየመንን ህዝብ እና ሕጋዊውን የየመን መንግሥትን ለመከለከል የሚቻለንን ሁሉ ማድረግ ይገባናል። »

የሁቲ ዓማፅያንን ትረዳለች የምትባለው ኢራን የሳውዲን እና የሌሎች የባህረ ሠላጤ ሀገራትን ጣልቃ ገብነት የየመንን የግዛት ሉዓላዊነት የሚጥስ ነው በሚል አሁኑኑ እንዲያቆም ማሳሰቧን እና ቀውሱን ለመቆጣጠር እንደምትጥር ማስታወቋን ዜና ምንጭ ሮይተርስ የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር መሀመድ ዣቫድ ዛሪፍን ጠቅሶ ዘግቦዋል። የዐረብ ሊግ የመንን ለማረጋጋት ለተጀመረው የጦር ጣልቃ ገብነት አስፈላጊውን ርዳታ ለማድረግ ቃል ቢገባም፣ ኢራቅ ጥቃቱን ተቃውማለች። ዩኤስ አሜሪካ መረጃ እና ትጥቅና ስንቅ በማቅረብ እንደምትረዳ አስታውቃለች። ጥቃቱን ተከትሎ የመን ዓበይት ወደቦችዋን መዝጋቷን ያካባቢ ምንጮች ገልጸዋል። የሁቲ ሚሊሺያዎች ባለፉት ወራት ብዙ የሀገሪቱን ከፊል ፣ መዲናዋን ሰንዓን ጨምሮ ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ ፕሬዚደንት ሀዲ ወደ ኤደን ሹ በኋላ አሁን ሪያድ መግባታቸው ተሰምቶዋል።

የየመን ይዞታ ከእርስ -በርስ ፍጥጫ ሌላ በውጭ ጣልቃ ገብነት፣ ይበልጥ የተመሣቃቀለ መስሏል።

ግሩም ተክለ ሃይማኖት

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic