የየመን አደረጃጀት እቅድና ተቃዉሞዉ | ዓለም | DW | 12.02.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የየመን አደረጃጀት እቅድና ተቃዉሞዉ

የመንን ለማረጋጋት በመንግስት የቀረበዉ አዲስ የአደረጃጀት እቅድ ተቃዉሞ ገጥሞታል። ሀገሪቱ በጎሳዎች ግጭት፤ በመገንጠል ንቅናቄና በአሸባሪዎች እንቅስቃሴ መናጧ ቀጥሏል።

እስከ1990ዎቹ ዓ,ም ድረስ የመን ለምዕራቡ ዓለም ቅርበት ባለዉ የሰሜኑ ክፍልና የሶቭየት ኅብረትን ስልት በሚከተለዉ ደቡቡ ግዛት በሚል ተለያይታ ኖራለች። ሰሜንና ደቡቡ ተቀላቅለዉ መኖር ከጀመሩ በኋላም የነበረዉ የሞቀ ስሜታዊ ቅርርብ ብዙም ሳይዘልቅ ቀዘቀዘ። ሰሜኑና ደቡቡ አሁን ዳግም በጥላቻ መተያየት ጀምረዋል። የሰንዓዉ ማዕከላዊ መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የጎሳ ግጭቶችና እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር አቅም አጥቷል፤ ሀገሪቱ ከዉጭ የሚመጡ አሸባሪ ቡድኖች መሸሸጊያ መሆኗም ሌላዉ ራስ ምታቱ ነዉ። እገታዎች እና ግድያዎች የመን ዉስጥ የየዕለት ገጠመኞች ከሆኑ ዉለዉ አድረዋል። የተለያየ ሃሳብ የሚያራምዱት ወገኖች ላለፉት አስር ወራት ያካሄዱት ዉይይት ካለ ዉጤት ከቀረ ከወራት በኋላ ነዉ በፕሬዝደንት አብዱራቡህ ማንሱር ሃዲ የሚመራዉ ኮሚቴ የመንን በስድስት ፌደራል ግዛቶች የማወቀር እቅድ ይፋ ያደረገዉ። እንደእቅዱ አራት ፌደራል ግዛቶችን በሰሜን ሁለት ደግሞ በደቡብ ለማድረግ ነዉ የታሰበዉ። ሰንዓ ደግሞ በዚህ ሳትካተት የተለየ ይዞታ ይኖራታል። ይህ ግን ከዉህደቱ በፊት የነበራቸዉን ነጻነት ዳግም የሚመኙትን ለደቡቡ መገንጠል የሚታገሉትን ወገኖችም ሆነ በሰሜኑ ተራራማ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱትን ዛይዲ ሺያት አማፅያንንም አላስደሰተም። ተቃዉሟቸዉን ወዲያዉ ነዉ ያሰሙት።

አንሳሩላህ ማለትም ለአምላክ የሚያደላ የተሰኘዉ የዛይዲ አማፅያን ቃል አቀባይ፤ የክልል ድንበሩ የአማፅያኑን ጠንካራ ግዛት ሳዳን ጨምሮ አራቱ የዛይዲ ዋና ክፍለ ሃገራት የባህር መዳረሻም ሆነ ይህ ነዉ የሚባል የተፈጥሮ ሃብት የለዉም ሲሉ ቅሬታቸዉን ገልጸዋል። እስቸዉ እንደሚሉትም ቡድናቸዉ ይህን እቅድ የማይቀበለዉ፤ አደረጃቱ የመንን በድሃና የበለፀገ ክልል ይከፍላታል በሚል ነዉ። ደቡቡን ለመገንጠል የሚሻዉ ቡድንም እንዲሁ እቅዱ የአካባቢዉን ህዝብ ፍላጎት አያሟላም ባይ ነዉ። ቀደም ሲል በዉይይቱ የተካፈለዉና በኋላ ተቃዉሞዉን በማሰማት የተለየዉ የለዘብተኛዉ የመገንጠል ንቅናቄ መሪ ሞሐመድ አሊ አህመድ፤ ደቡቦቹ የመወሰን መብትና የሉዓላዊ ግዛትነት ጥያቄ እንዳላቸዉ ነዉ ያመለከቱት። በአንፃሩ ሰንዓ ዉስጥ ሃሳቡን በመደገፍ ጎዳና በመዉጣት ድምፃቸዉን ያሰሙ ወገኖች አሉ።
ላለፉት ሁለት ሳምንታት የመከረዉና ባለጉዳዮቹ የተሳተፉበት ጉባኤ ይህ እቅድ በሀገሪቱ አዲስ ሕገ መንግስት እንዲካተት ነዉ ያሰበዉ። ለዚህም የዜጎቹን ስምምነት ይሻል። አብዛኞቹ የመናዉያን በፌደራል ግዛቶች መከፋፈሉ መልካም ቢሆንም የቀድሞዉን ደቡብ ከሰሜን የሚለይ ድንበር የመከለል ስሜት እንዳይከተል ይሰጋሉ። ከእነሱ ሞሃሰብ ሞሐመድ አንዱ ነዉ፤


«ስድስት ፌደራል ግዛቶች የሚለዉ በጣም ግሩም ነዉ። ነገር ግን ደቡባዊና ሰሜናዊ ክፍለ ሃገራት እንዳይከፋፈሉ የሚያደርግ ከሆነ ማለት ነዉ። የአስተዳደር መከፋፈል ሲኖር የአካባቢዉ አስተዳደር እንዲጠናከር የሚያደርግ ከሆነ እቅዱን እንደግፋለን። አንደኛዉ አካባቢ ከሌላዉ እንዳይለያይም በሕገ መንግስቱ ላይ መረጋገጥ ይኖርበታል።»
በሌላ በኩል ተንታኞች የጎሳ ግጭት፤ የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ እንዲሁም የእገታ ድራማ ባላባራባት የየመን የአሁን ይዞታ፤ በክልሎች የማደራጀቱ እቅድ ወትሮዉም የመገንጠል ሃሳቡ ላለዉ ወገን ጥሩ አጋጣሚ ይከፍታል ባይ ናቸዉ። ዛሬም ሂራኪ የተሰኘዉን የመገንጠን እንቅስቃሴ አራማጅ ቡድን የሚመሩት ናስር አል ናዋባ፤ በጥያቄያቸዉ እንደሚገፉበት ነዉ ይፋ ያደረጉት። ቢቻል በሰላማዊ መንገድ ትግላችን ይቀጥላል ነዉ ያሉት። እንዲያም ሆኖ ግን የመንን ከሃገርነት ወደተለያዩ ግዛቶች የማደራጀቱ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር መሠረት ለመጣል እንደተሞክረ ታዛቢዎች ይስማማሉ። ይህ ግን የመንን ከመበታተን ያድናት እንደሁ ገና አለየለትም።

ካርስተን ኩኸንቶፕ/ ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic