የየመን ምሥቅልቅል | ዓለም | DW | 21.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የየመን ምሥቅልቅል

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠላም ማጣትዋ «አሳሰበኝ» ይልላታል።ዩናይትድ ስቴትስ የአል ቃኢዳ «አባላት» የምትላቸዉን ትገድልባታለች።ሳዑዲ አረቢያና ኢራን ይሻኮቱባታል ይባላል።አሸባሪዎች በቦምብ ያተራምሷታል፤የጎሳ ታጣቂዎች፤አማፂያን፤ እና ወታደሮች ይዋጉባታል።ደቡብ አረቢያዊቱ ሐገር እዉነት ዓለም ሊያተራምስ ይችላል እንደ ዩሱፍ ያሲን።

የየመን ሺዓ ሁቲ አማፂያን ትናንት የሠነዓዉን ቤተ-መንግሥት ከተቆጣጠሩ ወዲሕ ወትሮም ያልሠመረዉ የሐገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዞ ግራ አጋቢ ሆኖኗል።ዓማፂያኑ ርዕሠ-ከተማ ሠነዓን ጨምሮ ሥልታዊ አካባቢዎችን ቢቆጣጠሩም ሐገሪቱን እንደ መንግሥት የማስተዳደር ሐላፊነቱን ለመያዝ የፈለጉ አይመስሉም።ፕሬዝዳንት አብድረቦ መንሱር ሐዲ ሥላሉበት ሁኔታና ሥፍራ የሚወጡ ዘገቦችም ግራ አጋቢ ናቸዉ።የቀድሞዉ ፕሬዝዳንት ዓሊ አብደላ ሳሌሕ በበኩላቸዉ የመን ዉስጥ አዲስ ምርጫ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ሠነዓና ሠነዓዎች-ወኪላችን ግሩም ተክለ ሐይማኖት እንደሚለዉ አጃዒበኞች ናቸዉ።ርዕሠ ከተማይቱ ታንክ፤መድፍ፤ ቦምብ ያጓራ-ያስገመግምባት ይሆናል።ወይም መትረየሥ ጠመንጃ ያስካካ፤ ጥይት -ይንጣጣባት ይሆናል።ሰነዓዎች ግን በየመደብሩ ይገበያያሉ።ይሕ ነዉ ግሩምን የሚገርመዉ።

የሁቲ አማፅያን ትናንት ቤተ-መንግሥቱን ከተቆጣጠሩ በኋላ የፕሬዝዳንቱን መኖሪያ ቤት ለመያዝ ከፕሬዝዳንቱ ጠባቂዎች ጋር ሲዋጉ ነበር።ሌሊቱን ዉጊያዉ ቆመ።አሸናፊ-ተሸናፊዉ ግን አለየም።እንደገና ግሩም።

ፕሬዝዳንት አብድረቦ መንሱር ሐዲም ያሉበትን ሁኔታ በትክክል የሚያዉቅ የለም።ዛሬ ጠዋት ሰዉዬዉ ወደ ትዉልድ ሐገራቸዉ አደን ሸሽተዋል ሲባል ነበር።ቀትር ላይ ፕሬዝዳንቱ ቤታቸዉ ዉስጥ በሁቲ አማፂያን ታግተዋል የሚል ዘገባ ደረሰን።ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ከሁቲ አማፂያን መሪዎች ጋር እየተነጋገሩ ተባለ።

ፕሬዝዳንቱ ድምፃቸዉ ከመጥፋቱ በፊት ትናንት የመን እንደ ሐገር በመኖር እና አለ መኖር መሕል ተቃርጣለች ብለዉ ነበር።የፖለቲካ ተንታኝና ደራሲ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት ፕሬዝዳንቱ በርግጥ አላበሉም።የየመን ዕጣ ፈንታ ግራ አጋቢ፤ አሳካሪ፤ አስጊም ነዉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠላም ማጣትዋ «አሳሰበኝ» ይልላታል።ዩናይትድ ስቴትስ የአል ቃኢዳ «አባላት» የምትላቸዉን ትገድልባታለች።ሳዑዲ አረቢያና ኢራን የበላይነትን ለመያዝ ይሻኮቱባታል ይባላል።አሸባሪዎች በቦምብ ያተራምሷታል፤የጎሳ ታጣቂዎች፤አማፂያን፤ እና ወታደሮች ይዋጉባታል።ደቡብ አረቢያዊቱ ሐገር እዉነት ዓለም ሊያተራምስ ይችላል እንደ ዩሱፍ ያሲን።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ

Audios and videos on the topic