የዞን ዘጠኝ የኢንተርኔት ጸሓፍት ሽልማት | ኢትዮጵያ | DW | 16.09.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የዞን ዘጠኝ የኢንተርኔት ጸሓፍት ሽልማት

በኢትዮጵያ መንግስት የጸረ-ሽብር ህግ ክስ የተሰመሰረተባቸው የዞን ዘጠኝ የኢንተርኔት ጸሓፍት የዓለም አቀፍ የፕሬስ ነጻነት ሽልማት አሸናፊ ሆኑ። ከጦማርያኑ መካከል አራቱ አሁንም በእስር ላይ ሲሆኑ ሁለቱ መፈታታቸው አይዘነጋም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:09
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:09 ደቂቃ

የዞን ዘጠኝ የኢንተርኔት ጸሓፍት ሽልማት

በኢትዮጵያ መንግስት የጸረ-ሽብር ህግ የተከሰሱት የዞን ዘጠኝ የኢንተርኔት ፀሃፍት የዓለም አቀፍ የፕሬስ ነጻነት ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል። ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት(CPJ) ተለምዷዊው ሚዲያ በፋይናንስ እጦት፤በመንግስት ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ጫና በተዳከመበት አገር ውስጥ ለተጫወቱት አዎንታዊ ሚና ፀሃፍቱን እንደሚሸልም አስታውቋል። በዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት የምሥራቅ አፍሪቃ ተወካይ ቶም ሮድስ በሽልማቱ የዞን ዘጠኝ ፀሃፍት ሃሳብን ለመግለጽ ነጻነት ላበረከቱት አስተዋጽዖ እውቅና ከመስጠት ባሻገር በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለማሳየት መታቀዱን ተናግረዋል። እንደ ቶም ሮድስ ከሆነ የዚንተርኔት አምደኖቹ በወጣት ኢትዮጵያውያን ዘንድ ያሳደሩት አዎንታዊ ተጽዕኖም ከፍተኛ ነው።

« ሰዎች የኢንተርኔት ፀሃፍቱ የሚሰሯቸውን ስራዎችና ፅሁፎቻቸውን ይከታተላሉ። በኢትዮጵያ ነጻ ሚዲያ በተለይም ደግሞ ነጻ የድረ-ገጽ ሚዲያ እንዲኖር የሚያደርጉትን ጥረት ይደግፋሉ።»

ከዞን ዘጠኝ የኢንተርኔት አምደኞች በተጨማሪ ከማሌዥያ ዙልኪፍለ አንዋር፤ከፓራጓይ ካንዲዶ ፊጌሬዶና በሶርያ በድብቅ የሚሰራው የራቃ ማህበረሰባዊ ጋዜጣ ስብስብ በመጪው ሕዳር14 ቀን2008 ዓ.ም. ኒውዮርክ ውስጥሽልማት ይበረከትላቸዋል።

የዞን ዘጠኝ የኢንተርኔት አምድ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፤ማህበረሰባዊ፤ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ርዕሰ ጉዳዮችን እያነሳ ይፈትሻል። የጉዞ ማስታወሻዎች፤ሳምንታዊ የኢትዮጵያ ጋዜጣና መጽሄቶች ስራ ዳሰሳዎችም ይቀርቡበት ነበር።

ከሶልያና ሽመልስ በስተቀር ስድስቱ በቀረበባቸው ክስ ለእስር ሲዳረጉ አራቱ አሁንም አልተፈቱም። በዞን ዘጠኝ ፀሃፍት ላይ የቀረበው የክስ መዝገብ ላይ በቀዳሚነት የሰፈረው የሶልያና ሽመልስ ስም ነው። «ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነጻነት ሽልማትን ማግኘት ትልቅ እውቅና ነው።» ስትል በሽልማቱ ላይ አስተያየቱን የሰጠችው ሶልያና «በተለይ በእስር ላይ ለሚገኙ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎችና ሌሎች ሃሳብን በነጻነት ከመግለጽ መብት ጋር በተያያዘ ዋጋ እየከፈሉ ላሉና ለከፈሉ ሰዎች ኢትዮጵያ ያለው የፕሬስ ጉዳይ በጣም አፋኝ እንደሆነና አስቸጋሪ እንደሆነ እውቅና መሰጠቱ ጥሩ ነው።» ብላለች።

በዘጠኝ ወጣቶች በኢ-መደበኛነት የተመሰረተው ስብስብ በግንቦት 2004 ዓ.ም. በኢንተርኔት አምዱ ካሰፈራቸው ቀዳሚ አረፍተ ነገሮች መካከል «ለኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚበጁ ምክረ ሐሳቦች ይነሳሉ፤ ይጣላሉ፡፡ መንግስት ይወቀሳል፣ ይተቻል፣ ይከሰሳል፡፡» የሚል ነበር። «ስለሚያገባን እንጦምራለን።» የሚል መፈክር ላነገቡት የዞን ዘጠኝ የኢንተርኔት አምደኞች ሊበረከት የተዘጋጀው ሽልማት ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት መብት በኢትዮጵያ የተጋረጠበትን ፈተና እንደሚያሳብቅ ሶልያና ታምናለች።

በዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት የምሥራቅ አፍሪቃ ተወካይ ቶም ሮድስ በኢትዮጵያ ያለው የኢንተርኔት ተደራሽነት አሁንም ውስን ቢሆንም በመጪዎቹ አመታት ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት በሚችል ደረጃ ያድጋል የሚል እምነት አላቸው።

«ነጻ የህትመት ውጤቶች በመዘጋታቸውና የነጻ ሚዲያ በመጥፋቱ የኢንተርኔት የዜና አቅርቦት በተለይ በውጭ አገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ እያደገ ነው። የዞን ዘጠኝ የኢንተርኔት አምደኞች በወጣቶችና በውጭ አገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ያገኙትን ተቀባይነት ስንመለከት የድረ-ገጽ መገናኛ ብዙሃን በመጪዎቹ አመታት ከዚህ በላይ ያድጋሉ። ለዚህም የዞን ዘጠኝ አባላት ላበረከቱት አስተዋጽዖ ምስጋና ይገባቸዋል።»

የዞን ዘጠኝ የኢንተርኔት አምድ አሁን አሁን እንደወትሮው የበይነ-መረብ ዘመቻዎች ማካሄዱን፤የጉዞ ማስታወሻም ይሁን የኢትዮጵያ ጋዜጦች ምን ጻፉ ብሎ መፈተሹን አቁሟል። ሶልያና ሽመልስ አሁን በእስር ላይ የሚገኙትን አራት የዞን ዘጠኝ አባላት ላይ ያተኮረው ስራ ወደ ፊትም እንደሚቀጥል ተናግራለች።

እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሰ

Audios and videos on the topic