የዞንዶ ኮሚሽን የዓመት ጉዞና ጃኮብ ዙማ | አፍሪቃ | DW | 20.08.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የዞንዶ ኮሚሽን የዓመት ጉዞና ጃኮብ ዙማ

«ዞንዶ ኮሚሽን» በሚል የተሰየመዉ ልዩ አጣሪ ኮሚሽን የቀድሞዉ አፍሪቃ ፕሬዚዳንት የጃኮብ ዙማ መንግሥት ዘርግቶት የነበረዉን ጥልቅ የሙስና አዉታር መረብ አንድ በአንድ መበርበር እና መፈተሽ ከጀመረ አንድ ዓመትን አስቆጠረ። እንድያም ሆኖ የኮሚሽኑ ስራ ለአብዛኞች ደቡብ አፍሪቃዉያን በቂ አልሆነም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:39

ጃኮብ ዙማ በሃገሪቱ ያበበዉን ዴሞክራሲ አንኮታኩተዉታል

«ዞንዶ ኮሚሽን» በመባል የሚታወቀዉና በሃገሪቱ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ዋና ሊቀመንበር ስም የተሰየመዉ ልዩ አጣሪ ኮሚሽን የቀድሞዉ አፍሪቃ ፕሬዚዳንት የጃኮብ ዙማ መንግሥት ዘርግቶት የነበረዉን ጥልቅ የሙስና አዉታር መረብ አንድ በአንድ መበርበር እና መፈተሽ ከጀመረ አንድ ዓመትን አስቆጠረ። እንድያም ሆኑ የጃኮብ ዙማን አስተዳደር የሙስና መረብ የሚፈትሸዉ አጣሪ ኮሚሽን እየሰራ ያለዉ ተግባር ለአብዛኞች ደቡብ አፍሪቃዉያን በቂ ሆኖ አልተገኘም። እንደ አብዛኞች ፍላጎት ሙሰኞች እና በስልጣናቸዉ የባለጉት ጃኮብ ዙማ እና ተባባሪዎቻቸዉን ሁሉ ሕግ ፊት ቀርበዉ ማየትን ይሻሉ። ይሁንና እና ከአንድ ዓመት ጀምሮ ሙስናን እንዲመረምር የተቋቋመዉ አጣሪ ኮሚሽን ተግባር የሙስና መረቡን በመከታተል የዓይን እማኞችን ከማዳመጥ እና ሁኔታዉን ይፋ ከማድረግ በቀር ፍርድ ፊት የማቆም ኃላፊነት የለዉም። በመጭዉ የጎርጎረሳዉያን 2020 በሃገሪቱ የሕገ-መንግሥት ፍርድቤት ሊቀመንበር በራይሞንድ ዞንዶ የሚመራዉ የሃገሪቱ የፍትህ አካላት አጣሪ ኮሚሽን የደረሰበትን የምርመራ ዉጤት ማየት እንደሚፈልጉ አሳዉቀዋል። ኮሚሽኑ እስካሁን ምን ዉጤትን አግኝቶ ይሆን?      

በዙማ አስተዳደር የነበረዉ ፖለቲካ በራሱ ትክክለኛ አልነበረም የሚሉት ደቡብ አፍሪቃዊዉ የፖለቲካ ተንታኝ ራልፍ ማትኬጋ ባለስልጣናቱ ኃላፊነቱን መዉሰድ አለባቸዉ ባይ ናቸዉ።

 

«ይህ አጣሪ ኮሚሽን ተጠያቄዎችን ነጥሎ አዉጥቶ ሕግ ፊት የማቆም ኃላፊነት ባይኖረዉም፤ ሁኔታዉ አሁን ምን እንደሆን ግልፅ አድርጓል። በዚህ አስተዳደር ብዙ ነገሮች ተበላሽቷል። ግን ባለስልጣናቱ ኃላፊነትን ካልወሰዱ፤ ማን ሊወስድ ነዉ?»  የፖለቲካ ጉዳይ ተንታኙ ራልፍ ማትኬጋ በዙማ አስተዳደር የነበረዉን ሙስና አንድ በአንድ የሚያጣራዉን ኮሚሽን የአንድ ዓመት የሥራ ዉጤት ተመልክተዉ አወንታዊ ዉጤት ሲሉ ተቀብለዉታል። « ሕዝብ የመረጣቸዉ ፖለቲከኞች ምን ሲሰሩ እንደነበር ለሕዝቡ በይፋ ሲቀርብ በማየቴ እንደ ትልቅ ስኬት እወስደዋለሁ። የመርማሪ እና አጣሪ ኮሚሽኑን ዘገባን የተከታተሉ መራጮች ስሜታቸዉ ጉዳዩን ከተከታተሉት እንደሚለይ እሙን ነዉ» 

በጎርጎረሳዉያኑ 2017 የመንግሥት ባለስልጣናት እና መስሪያ ቤቶች ላይ የሚጣል ክስን ይከታተሉ የነበሩት ደቡብ አፍሪቃዊትዋ ቱሊ ማዶንሴላ፤ የሙስና ክስ ይቀርብባቸዉ የነበሩት የቀድሞዉ የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ፍተሻና ምርመራ እንዲካሄድ ትእዛዝ እንዳስተላለፉባቸዉ ይታወሳል። ይህ ትዕዛዝ የተላለፈባቸዉ የዝያን ጊዜዉ ፕሬዚዳንት ዙማ በበኩላቸዉ ወዳጅ በሚልዋቸዉ ሚኒስትሮቻቸዉ የደቡብ አፍሪቃ ቱጃር ነጋዴዎች እና የግዙፉ «ጉፕታ» የተሰኘዉ የአንድ  ቤተሰብ ኩባንያ ርዳታ ከፍተኛ መጠን ያለዉ ገንዘብ ሳያጭበረብሩ እንዳልቀረ ተነግሮአል። በዙማ አስተዳደር ላይ የተመሰረተዉን ከፍተኛ የሙስና እና የስልጣን መባለግ ክስን ለመርመር የተሰየመዉ «ዞንዶ አጣሪ ኮሚሽን» በጎርጎረሳዉያኑ 2018 የማጣራት ስራዉን ሲጀምር ከፍተኛ የደቡብ አፍሪቃ ፖለቲከኞችን ቃል አዳምጦአል። ከነዚህ መካከል ለምሳሌ ሞሲብሲ ጆንስ አንዱ ናቸዉ።

ትዉልደ ሕንድ የሆኑትና ከ1993 ዓም ጀምሮ በደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩት« ጉብታ» የተሰኘዉ ቱጃር የቤተሰብ ኩባንያ ባለቤቶች፤ በጎርጎረሳዉያኑ 2016 ደቡብ አፍሪቃዉን ፖለቲከኛ ሞሲብሲ ጆንስ የሃገሪቱን የገንዘብ ሚኒስትርነት ሹመት እንዲወስዱ በተጨማሪ 600 ሚሊዮን የደቡብ አፍሪቃ ራንድ ወይም ወደ «35 ሚሊዮን ይሮ» እንደሚሰጥዋቸዉ ቃል ገብቶላቸዉ እንደነበር አጋልጠዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ ምክትል የሙሉ ሚንስትርነት ስልጣኑን እንደሚረከቡ ቃል እንደተገባላቸዉ፤ ፕሬዚደንት ጃኮብ ዙማ በሚኒስትርነት ሲያገለግሉ የነበሩትን ግለሰብ ያለምንም ምክንያት ከስራቸዉ እና ከስልጣናቸዉ አባረዋቸዉ። ስልጣኑን እንዲረከቡ የተነገራቸዉ የገንዘብ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር፤ ይህን ጉዳይ ይፋ ታወጣና በሕይወትህ ፈርደሃል ሲባሉም ከዚሁ ኩባንያ ቱጃር ቤተሰብ አባላት ማስፈራርያ እንደደረሰባቸዉ አጋልጠዋል።

በፕሬዚዳንት ጃኮብ ዘመነ ስልጣን የደቡብ አፍሪቃ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ የነበሩት ቴምባ ማሴኮ በበኩላቸዉ፤ «ጉብታ» የተባለዉ ቱጃር የቤተሰብ ኩባንያ በንግድ የሚረዳኝ ነዉ ሲሉ ዙማ ነግረዉኛል ሲሉ ቃላቸዉን ሰጥተዋል። ይህን በይፋ ተናግረዉ በገዛ ፈቃዳቸዉ ስልጣናቸዉን መልቀቃቸዉ ይታወቃል። የደቡብ አፍሪቃ ምክር ቤት አባል የነበሩት ቪቲጄ ሜንቶር፤ የካቢኔ ስልጣን እንደሚሰጣቸዉ፤ የተለያዩ የባንኮች ኃላፊዎች፤ ቆየት ብሎም የፊናንስ ሚኒስትሩ ከቀድሞዉ ፕሬዚደንት ዙማና ታማኞቻቸዉ የተለያየ የስልጣን ርከን ይሰጣችኋል፤ ይህን አድርጉ መባላቸዉን በይፋ ተናግረዋል። ጃኮብ ዙማ የገዛ ኪሳቸዉን ለማደለብ እና በንዋይ መሽቆጥቆጥን መርጠዉ፤ የመንግሥት ስልጣንን  ብሎም የሃገሪቱን ገንዘብ ጥቅም ላይ አዉለዋል፤ በስልጣን ባልገዋል። ይህ ድርጊታቸዉ በደቡብ አፍሪቃ አብቦ የነበረዉን የዴሞክራሲ ጎዳና አንኮታኩተዉታል። ዙማ ለደቡብ አፍሪቃ የነጻነት ትግል ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረጉ የሚታወቀዉን እና ሰፊ ተቀባይነት ያለዉን የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት  « ANC » ፓርቲን አሸማቀዉታልም። 

ጃኮብ ዙማ የደቡብ አፍሪቃ የፕሬዚዳንትነት መንበርን ተቆናጠዉ የፈፀሙትን  በስልጣን መባለግና የሙስና ቅሌት የሚመረምረዉ ኮሚሽን ፊት ለፊት ላለመጋፈጥ ብዙ ታትረዋል። ይሁንና ባሳለፍነዉ ሐምሌ ወር አጋማሽ የ 77 ዓመቱ ጃኮብ ዙማ፤ የአጣሪ ኮሚሽኑን መረጃን አዳምጠዉ «ሃሰት ይህን እኔ አልፈፀምኩም ሲሉ» አስተባብለዋል። በአንፃሩ ጃኮብ ዙማ ይህ ሁሉ የኔን ዉድቀት የፈለጉ የሸረቡብኝ ነዉ ነዉ ያሉት። በዚሁ ምክንያት ስልጣኔን አጥቻለሁ፤ ስሜም ጠልሽቶአል ሲሉ አቤቱታቸዉን ሰምተዋል። እንደዉም ዙማ እንደተናገሩት፤ የኔን የፖለቲካ አቋም የሚጻረሩ ሁሉ « የሙስናዉ ንጉስ» ሲሉ ማጣላቸዉን ቀጥለዋል ብለዋል። ይባስ ብሎ ዙማ ስልጣን ላይ የሚገኙት የመንግሥት ፖለቲከኞች የቀድሞዉ የአፓርታይድ ስርዓት ሰላዮች ናቸዉ ሲሉ መክሰሳቸዉ ሁሉ ተሰምቶአል።     

ዙማ በፕሬዚደንት ስልጣን ላይ ሳሉ በጎርጎረሳዉያኑ 2018 መጀመርያ ወር፤  አጣሪ ኮሚሽኑን አዋቅረዉ  የሰየሙት ራሳቸዉ ነበሩ። በዚሁ የጎርጎረሳዉያን 2018 ዓመት መጨረሻ ወር ላይ ፕሬዚዳንት ዙማ በደቡብ አፍሪቃ ገዥ ፓርቲ « ANC » አስገዳጅነት ከስልጣናቸዉ በገዛ ፈቃዳቸዉ እንዲለቁ መደረጉም የሚታወስ ነዉ። ዙማን ተክተዉ የቀድሞዉ ተለዋጫቸዉ ምክትል ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፖዛ፤ በጥቂት አብላጫ ድምፅ የዙማን የፕሬዚዳንትነት ስልጣን ተቆናጠጡ። የወቅቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፖዛ በቀድሞዉ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚዳንት ዙማ የሙስና ቅሌት ላይ ምስክር የሚሰጡ ግለሰብ መሆናቸዉ ተመልክቶአል። ራማፖዛ እንደተናገሩት ለምስክርነት ስፈለግ ሁሉም ዝግጁ ነኝ ብለዋል።   

በሚቀጥለዉ የጎርጎረሳዉያን 2020 የዙማን የሙስና ቅሌት መረጃን የሰበሰበዉ የመጨረሻ ክፍል መረጃ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። የፖለቲካ ጉዳይ ምሑሩ ራልፍ ማቴካ እንደሚሉት በጃኮብ ዙማም ሆነ በተባባሪዎቻቸዉ ላይ በአፋጣኝ የሕግ ርምጃ እንዲወሰድ ይመክራሉ። ምክንያቱ ደግሞ ክሱ ተመስርቶ ምርመራዉ እስኪካሄድ እና እስኪጣራ ዉሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ሌላ ዓመትን ይፈጃል ባይ ናቸዉ።  ቱጃሮቹ የ«ጉብታ» ኩባንያ የቤተሰብ አባላት፤ አዲስ የምጣኔ ኃብት ምንጭን ለመገንባት ደቡብ አፍሪቃን ጥለዉ ወደ ዱባይ ማቅናታቸዉ ተሰምቶአል።  በደቡብ አፍሪቃ   «የሙስና ቁጥጥር» በተሰኘ ድርጅት ዉስጥ የሚያገለግሉ ዴቪድ ሉዊስ እንደሚሉት የዙማ የሙስና ቅሌት ይፋ በሆነበት እለት የገዥዉ ፓርቲ አባላት ለመከታተል ቦታዉ ላይ ከተገኙ የሚናደደዉና እና የሚበሳጨዉ አባል ቁጥር መጨመሩ አይቀሬ ነዉ።

« ሁኔታዉ ያሳዝናል። ኮሚሽኑ የሰበሰበዉን መረጃ ይፋ ባደረገ ቁጥር፤ ወንጀሉን የፈፀሙት ሰዎች ማንነት ግልፅ ሲወጣ ፤ ወንጀለኞቹ አሁንም በነፃ ይንቀሳቀሳሉ፤ ብሎ የሚበሳጨዉ ዜጋ ቁጥር ይጨምራል። ሃገሪቱ በጣም ተከፋፍላለች።» አብዛኛዉ ደቡብ አፍሪቃዊ በሃገሪቱ ስለተፈፀመዉ የሙስና ቅሌት ጥንቅቆ እንደሚያዉቅ ያቃል ሲሊም ዴቪድ ሉዎስ አክለዋል። የሙስና አጣሪ ኮሚሽኑም እጅግ ስኬታማ ስራን ስርቶአል ብለዋል። ግን ይላሉ ዴቪድ ሉዊስ አጣሪ ኮሚሽኑ የሰበሰበዉን መረጃ ይፋ እስኪያደርግ መጠበቅ የለበትም፤ ወንጀለኞቹ በቁጥጥር ስር መዋል አለባቸዉ።

« የባለስልጣን መሥርያ ቤቱ የዙማ አጣሪ ኮሚሽን የሙስና እና የስልጣን መባለግ ወንጀል የፈፀሙት ድርጅቶች እና ዜጎች መረጃ በዝርዝር አቅርቦ እስኪጨርስ ድረስ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር ካለማድረግ መቆጠብ የለበትም» ግን እነዚህ እነዚህ ድርጅቶች ማለትም ጉፕታ እና ዙማ ምንም አይነት ምርመራ እዳይደረግባቸዉ ዘግተዉ የተቀመጡ የተቆላለፉ መሆናቸዉ ነዉ የተመለከተዉ።

አዜብ ታደሰ / ማራቲና ሽቪኮቭስኪ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic