የዚምባቡዌ ምርጫ ዝግጅት | አፍሪቃ | DW | 04.06.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የዚምባቡዌ ምርጫ ዝግጅት

ዚምባቡዌ ለምርጫ እየተዘጋጀች ነዉ። የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞርጋን ቻንጊራይ አስቀድሞ አንዳንድ ማሻሻያዎች መደረግ እንደሚኖርባቸዉ እያሳሰቡ ነዉ። ፕሬዝደንት ሮበር ሙጋቤ በበኩላቸዉ ህገመንግስታዊዉ ፍርድ ቤት በወሰነዉ መሠረት ምርጫዉ በሐምሌ ወር ማለቂያ እንደሚካሄድ ይፋ አድርገዋል።

ከምርጫዉ በኋላ ሁለቱ የሚመሩት የጥምር መንግስት እንደሚያከትም ሲጠበቅ ሙጋቤ እና ቻንግራይ ለፕሬዝደንትነት ይፎካከራሉ። በሃራሬ ጎዳናዎች የሚዘዋወሩ የዚምባቡዌ ዜጎች ስለምርጫዉ አስተያየት ከመስጠት መቆጠባቸዉ እጅግም አይገርምም። ምርጫ ዚምባቤዉ ዉስጥ በአብዛኛዉ ከአመፅ ጋ የተዛመደ ነዉና። ባለፈዉ ሳምንት ዓርብ የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምርጫዉ ሐምሌ 24 ቀን 2005ዓ,ም እንዲያካሄድ ወስኗል። ሩጋሬ ጉምቦ የፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤ ፓርቲ ዛኑ PF ቃል አቀባይ ቢቻል ምርጫዉ ከዚህም ቀድሞ እንዲካሄድ ነዉ የሚሹት። ፓርቲያቸዉ ማሸነፉንም አይጠራጠሩም። አራት ዓመታትን ያስቆጠረዉ የጥምር ፓርቲ ከሚፈለገዉ በላይ ረዥም ጊዜ ቆይቷል ባይናቸዉ።

Simbabwe Robert Mugabe neue Verfassung 22.05.2013

ፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤ

«በእኛ እይታ ሁሉን ያካተተው መንግስት በጣም ገዳቢ ነዉ። ብዙ ክርክርና ዉዝግብ አለ፤ በለዴሞክራሲ ለዉጥ ንቅናቄዉ በኩል ሲታይ ምንም ተጨባጭ መርሃግብር እንደሌለዉ ተጋልጧል። ለሕዝቡ የሚያቀርቡት ምንድነዉ? መልካም አስተዳደር? ዴሞክራሲ? የሰብዓዊ መብቶች? ነገር ግን የዚምባቤዌ ሕዝብ የሰብዓዊ መብቶችን አይበላም? መልካም አስተዳደርንም አይበላም። የሚፈልጉት ገበታቸዉ ላይ የሚያቀርቡት ነገር ነዉ፤ የዳቦና ማባያ ጉዳይ ነዉ።»

በእሳቸዉ እምነትም በዚህ ምክንያት የጠቅላይ ሚኒስትር ሞርጋን ቻንጊራይ MDC ፓርቲ በቀጣዬ የዚምባቡዌ ምርጫ አይሳካለትም። ጠ/ሚ ቻንጊራይ ምርጫዉ ከመካሄዱ አስቀድሞ መሻሻል የሚገባቸዉ ነገሮች እንዳሉ እያሳሰቡ ነዉ። ያ ካልሆነ ከወራት በፊት የጸደቀዉ ሕገመንግስት ያካተታቸዉ የማሻሻያ ሃሳቦች ተግባራዊ የመሆናቸዉ ነገር አጠያያቂ ይሆናል። ቃል አቀባያቸዉ በጉዳዩ ላይ ባወጡት መግለጫ የምርጫዉን ቀን የመወሰን ስልጣን የፍርድ ቤት እንዳልሆነ ነዉ ያመለከቱት። ዳግላስ ሙዎንዞራ የMDC ፓርቲ ቃል አቀባይ አነጋጋሪዉ ጉዳይ የቀኑ ሳይሆን ከምርጫዉ በፊት ሊደረጉ የሚገባቸዉ ነገሮች አለመከናወናቸዉ መሆኑን ያሳስባሉ፤

«MDC ያነሳዉ ጉዳይ ምርጫዉ ሐምሌ 22 ወይም 23 ይካሄድ የሚል አይደለም። ዋናዉ ነጥብ፤ ምርጫዉ መካሄድ የሚኖርበት አስፈላጊዉ ማሻሻያ ከተከናወነ በኋላ ነዉ የሚል ነዉ። እነዚህ ማሻሻያዎች ደግሞ ዘመናት የሚወስዱ አይደሉም፤ የምንላቸዉ ማሻሻያዎች ከወር በላይ ወይም ከዚያ ያነሰ ጊዜ ነዉ የሚፈልጉት። እነዚህ ማሻሻያዎች ሊደረጉ ይችላሉ።»

MDC የጠየቀዉ ማሻሻያ ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ የመንግስት መገናኛ ብዙሃንን ለብቻ መቆጣጠሩን ያቁም፤ የመራጮች ምዝገባ ይጠናቀቅ የሚሉትን ያካትታል። ከዚህም ሌላ በስልጣን ላይ የሚገኙ የጦር ኃይሉ መኮንኖች ለፕሬዝደንት ሙጋቤ ያላቸዉን ድጋፍ በይፋ መግለጻቸዉም MDCን አላስደሰተም። ርምጃቸዉ የሀገሪቱን ሕገመንግስት እንደሚፃረርም አመልክቷል። በሌላ በኩል ምርጫዉ መቃረቡ እየተነገረ ባለበት ሁኔታ ለዚሁ የሚዉል የገንዘብ እጥረት መኖሩ እየተሰማ ነዉ።

Morgan Tsvangirai Simbabwe

ጠ/ሚኒስትር ሞርጋን ቻንጊራይ

ባለፈዉ ሳምንት የዚምባቡዌ የገንዘብ ሚኒስትር ለምርጫዉ ከ130 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግና ያንንም ለማሰባሰብ እየታገሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ከበርሊን ዌስትሚኒስተር ዩኒቨርሲቲ የመገናኛ ብዙሃንና ዴሞክራሲ ዘርፍ የዶክተሬት ተመራማሪ ፔድዚሳ ሩሃንያ እንዲህ ባለዉ ሁኔታ ምርጫዉ በተባለዉ ቀን ስለመካሄዱ ጥርጥር አላቸዉ፤

«ፍርድ ቤቱ አዲሱ ሕገመንግስት የሚላቸዉን ከግምት ያስገባ አይመስለኝም። ዉሳኔዉን ተግባራዊ ማድረግ ያስቸግራል። አገሪቱ ለሠላሳ ቀናት የመራጮች ምዝገባ ማካሄድ ይኖርባታል። ያ ገና አልተጀመረም። ታዳያ እንዴት ሆኖ ነዉ በሐምሌ ወር ምርጫ ሊኖር የሚችለዉ? የምርጫ ሕጉም መሻሻል ይኖርበታል፤ ያም አልደረገም። ስለዚህ የቀኑ ጉዳይ ሳይሆን ሂደቱ ነዉ ቀኑን ለመወሰን የሚያስችለዉ።»

ባለፈዉ መጋቢት ወር ዚምባቡዌ ለአዲሱ ሕገመንግስት ዉሳኔ ሕዝብ አካሂዳለች። ይህም የዚምባቡዌ ጥምር መንግስት ከአራት ዓመታት በኋላ ምርጫ ለማካሄድ እንዲችል የአፍሪቃ መሪዎች ካስቀመጡለት ቅድመ ሁኔታ አንዱ ነዉ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2008ዓ,ም ምርጫ በኋላ የሙጋቤን ድል እንደማይቀበሉ የገለፁት የአፍሪቃ መሪዎች ናቸዉ ዛኑ PF እና MDC ስልጣን እንዲጋሩ ያስማሙት። አሁን ዚምባቡዌ ለምርጫ ዝግጅት ጀምራለች ተጣማሪዎቹ ፓርቲዎችን የሚያወዛግቧቸዉ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነዉ ገንዘብ ከተገኘ ደቡብ አፍሪቃዊቱ አገር ሐምሌ መገባደጃ ምርጫዋን ልታካሂድ ትችላለች።

አይዛክ ሙጋቤ/ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic