1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሀን መድረክ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 11 2016

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አና ሌና ቤርቦክ ባሰሙት ንግግር አንዳንድ መንግሥታት ጋዜጠኞችን ሊጠብቋቸው ሲገባ ለአደጋ እያጋለጧቸው ነው ሲሉ ከሰዋል። በመላው ዓለም የሚገኙ ጋዜጠኞች በሞያቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቤርቦክ ለማንም የማይወግን ጋዜጠኝነት በመላው ዓለም ጫና ውስጥ ወድቋልም ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4hCtx
GMF 2024 | How can we (re)establish trust in journalism?
ምስል Philipp Böll/DW

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሀን መድረክ


የዶቼቬለ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መድረክ ትናንት ሰኔ 10 እና ዛሬ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓም ጣቢያው በሚገኝበት በቦን ከተማ «መፍትኄዎችን መጋራት» በሚል መሪ ቃል ተካሂዶ ተጠናቋል። ።የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አና ሌና ቤርቦክ በእንግድነት በተገኙበት በዚህ መድረክ ከ100 በላይ ሀገራት የተወከሉ ወደ 1500 የሚጠጉ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።መድረኩ  በተለይ  ፤በዓለም ዙሪያ  በጋዜጠኝነት እና በመገናኛ ብዙኃን  አንገብጋቢ ጥያቄዎች እና መፍትሄዎች ላይ አትኩሮ ተነጋግሯል። የDW  የዝግጅቱ ዋና ተጠሪ ቤንጃሚን ፓርጋን እንደተናገሩት፣ መድረኩ ካነሳቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የአካል፣ የስነ-ልቦና፣ ሕጋዊና ኤኮኖሚያዊ ደህንነት  ይገኝበታል። መድረኩ በጎርጎሮሳዊው 2024 ዓ:ም. ልዩ ትኩረት ስለተሰጣቸው የህንድና የአውሮጳ ኅብረት ምርጫዎች አዘጋገብ እንዲሁም በዚሁ ዓመት በህዳር ወር በሚካሄደው የአሜሪካን ምርጫ ዘገባ ላይም ተነጋግሯል። ለ17 ተኛ ጊዜ የተካሄደው ይኽው መድረክ የሀሰት መረጃ ዘመቻዎችን፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት  ፈጣን እድገት እና በጋዜጠኞች የእለት ተእለት ስራ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖምላይ  ተወያይቷል።ቤንጃሚን ፓርጋን ስለ ስለመድረኩ እንደተናገሩት በመገናኛ ብዙሀን መስክ የተደረሰበት እድገት ወደ ኋላ የሚመለስ አይደለም። የመገናኛ ብዙሀን ድርጅቶች ሚና አሁንም ቀላል የሚባል አይደለም።ስለዚህ መገናኛ ብዙሀን ዓላማቸውን ለማሳካት አሰራሮቻቸውን ማስተካከል ይኖርባቸዋል።8ኛው የዶይቸ ቬለ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መድረክ


«የመገናኛ ብዙሀን ድርጅቶች ነገሮችን ከመቃወም ይልቅ እንዲስተካከሉ መርዳት አለባቸው። በተመሳሳይ ጊዜም ያሉትን እድሎችና አደጋዎችም በትክክል መገምገም አለባቸው። እድሎችንና   አደጋዎችን ከመላው ዓለም ከመጡ የሙያ ባልደረቦቻችን ጋር በሚካሄዱ ውይይቶች በማሳየት በግልጽ ማካፈል እንፈልጋለን።»ቦን ከተማ የምትገኝበት የኖርድ ራይን ቬስትፋለን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንድሪክ ቩስት በቪድዮ ባስተላለፉት መልዕክት ስለተች ዘገባዎች አስፈላጊነት የጀርመንን ልምድ አካፍለዋል።አክራሪ ኃይሎች በፕሬስ ነጻነት ላይ የሚያካሂዱትን ዘመቻ ለመቋቋም በድፍረት መታገል እንደሚገባም አሳስበዋል። «በጀርመንም ነገሮችን በጥልቀት የሚያዩ ተች ዘገባዎች እና ለአንድ ወገን የማያዳላ መረጃ የሚደገፉና ግዴታም ናቸው።እዚህም ቢሆን ታዲያ አክራሪ ኃይሎች የፕሬስና የመገናኛ ብዙሀን ነጻነትን እየተዋጉ ነው። የዴሞክራሲያችን ተቃዋሚዎች እውነታውን አይቀበሉም። በስሜታዊ እና ጥላቻን በሚቀሰቅሱ የሀሰት ዜናዎችና ውሸቶች ላይ ነው የሚተማመኑት። ይህንንም በክርክር ኃይል ለነጻነትና ዴሞክራሲ ባለን ፍቅር በድፍረት በመታገል መቃወም አለብን።»

የዶቼቬለ ዋና ሃላፊ ፔትር ሊምቡርግ በመገናና ብዙሀን መድረክ ላይ የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ
የዶቼቬለ ዋና ሃላፊ ፔትር ሊምቡርግ በመገናና ብዙሀን መድረክ ላይ የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ ምስል Philipp Böll/DW


ጋዜጠኝነት ታላቅ ሞያ ነው። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ ጋዜጠኞች በርካታ ተግዳሮቶች ይገጥሟቸዋል። ከመካከላቸው የተሳሳተ መረጃ እና አርቲፊሻል አስተውሎት ይገኙበታል። ዛቻዎች ጥቃት አንዳንዴም ጦርነት የጋዜጠኞች ፈተናዎች ናቸው። የዘንድሮው የዶቼቬለ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መድረክ አዘጋጆች ለነዚህ ችግሮች መፍትኄ የመፈለግ ተስፋ ሰንቀው ነው መድረኩን ያካሄዱት። በመድረኩ ላይ የተገኙት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አና ሌና ቤርቦክ ባሰሙት ንግግር አንዳንድ መንግሥታት ጋዜጠኞችን ሊጠብቋቸው ሲገባ ለአደጋ እያጋለጧቸው ነው ሲሉ ጠቁመዋል። በመላው ዓለም የሚገኙ ጋዜጠኞች በሞያቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቤርቦክ ለማንም የማይወግን ጋዜጠኝነት በመላው ዓለም ጫና ውስጥ ወድቋልም ብለዋል። የዚህ አንዱ ምክንያትም ጋዜጠኞች የጦርነትና ግጭቶች ሰለባዎች መሆናቸው መሆኑንንም ጠቁመዋል። «በጎርጎሮሳዊው 2023 ፣ 120 ጋዜጠኞች በስራ ገበታቸው ላይ እያሉ ተገድለዋል።  ከመካከላቸው ሁለት ሦስተኛው ብቻ በጋዛው ጦርነት  ነው የተገደሉት። ይህ ደግሞ ተቀባይነት የለውም።በዓለም ዙሪያ ነጻ መገናኛ ብዙኃንን የሚጫኑ አምባገነን መንግሥታት ቁጥር እየጨመረ ነው።» ዓለም አቀፉ የብዙሃን መገናኛ መድረክ

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አና ሌና ቤርቦክ በቦኑ የመገናኛ ብዙሀን መድረክ ላይ ንግግር ሲያደርጉ
የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አና ሌና ቤርቦክ በቦኑ የመገናኛ ብዙሀን መድረክ ላይ ንግግር ሲያደርጉ ምስል Ayse Tasci/DW


በጋዜጠኞችና በሙያው ላይ የሚደርሰውን የጥቃት ደረጃን በማስረጃ የጠቆሙት ቤርቦክ ሰው ሰራሽ አስተውሎትም መከፋፈልን የመዝራት እንዲሁም እኩልነትን የሚጻረሩ ድርጊቶች እንዲጨምሩ የሚያደርግ ሊሆን አንደሚችልም አስጠንቅቀዋል። ቤርቦክ እንዳሉት ጀርመን ይህን አደገኛ አዝማሚያ ለመቋቋም ዓለም አቀፍ ሕጎች እንዲወጡ ግፊት እያደረገች ነው። እነዚህን ስጋቶች ቤርቦክ በተገኙበት የፓናል ውይይት ላይ የተሳተፉት  ፊሊፒናዊ- አሜሪካዊቷ የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ማርያ ሬሳም ተጋርተዋል። «ጋዜጠኝነት ለአምባገነንነት መድኃኒት ነው። ጋዜጠኞች ብቻ ናቸው አንድ አምባገነንን በመጋፈጥ ከባድ ጥያቄዎችን በተለሳለሰ መንገድ የሚያነሱት ።ትክክል ነው ሆኖም የዲጂታል ዜና ገጽ ከሆናችሁ በትላልቅ ቴክኖሎጂዎች እርምጃ ልትሞቱ ትችላላችሁ ። ድረ ገጻችን በአንድ ዓመት ውስጥ ሊሞት ይችላል።» ቤርቦክ ከዚህ ሌላ «ዴሞክራሲ ከሰማይ የወረደ እንዳይደለ» አስገንዝበው «ልንጠብቀው ይገባልም »ሲሉ አሳስበዋል። ዴሞክራሲ የማይነካ ዘላለማዊ ለሚመስላቸው በተወሰኑ የፖለቲካ ተዋናዮች እየተረበሸ መሆኑንም አስጠንቅቀዋል።  ቤርቦክ፣ ፊሊፒናዊ አሜሪካዊቷ  ጋዜጠኛ ማርያ ሬሳ እንዲሁም ኡጋንዳዊቷ ጋዜጠኛና የመገናኛ ብዙሀን ባለቤት ስኮቪያ ኩልቶን ናካሚ በመድረኩ በዴሞክራሲ ጉልበት ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት አካሂደዋል። ሦስቱ የውይይቱ ተካፋዮች ኅብረተሰቡና ዴሞክራሲ ይበልጥ እንዲጠናከሩ አስፈላጊ ባሏቸው ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሂደቶች ላይ ሃሳባቸውን አካፍለዋል። ከዚህ ሌላ በመገናኛ ብዙሀን የተለያዩ ድምጾች ይበልጥ ትኩረት እንደሚያገኙም አስገንዝበዋል። 

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አና ሌና ቤርቦክ እና  ጋዜጠኛ ማርያ ሬሳ ስለዴሞክራሲ ጉልበት በተካሄደ የፓናል ውይይት ላይ ሃሳባቸውን ሲያካፍሉ
የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አና ሌና ቤርቦክ እና ጋዜጠኛ ማርያ ሬሳ ስለዴሞክራሲ ጉልበት በተካሄደ የፓናል ውይይት ላይ ሃሳባቸውን ሲያካፍሉምስል Philipp Böll/DW


10 ኛው የዓለም የመገናኛ ብዙኃን መድረክበቦኑ ዓመታዊው የመገናኛ ብዙኃን መድረክ ላይ የተካፈሉ አብዛኛዎቹ የመገናኛ ብዙሀን ባለሞያዎች እንደሰጡት አስተያየት ከሆነ መድረኩ ትልቁን ጉዳይ ለማየት ጠቃሚ እድል ያገኙበት ነበር። የውይይቱ ተሳታፊዎች ለዶቼቬለ በሰጡት አስተያየት ከውይይቶቹ ያገኑትን ልምድ አካፍለዋል። «ቴክኖሎጂን በሕግን ማረቅን እንዲሁም በጋዜጠኝነት ሞያ ውስጥ ሴቶች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶችን  የተመለከቱትን ውይይቶች ተደስቼባቸዋለሁ።» «ከተለያዩ ከእስያ ከላቲን አሜሪካ ከሜክሲኮ ከሞሮኮ እና ከሌሎች አገራት ከመጡ ሰዎች ጋር ለመገናኘት ችለናል። አብዛኛዎቹ ጉዳዮቻችን መመሳሰላቸው ያስደንቃል። » ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በተመለከተ የዶቼቬለ ዋና ሃላፊ ፔተር ሊምቡርግ  ባስተላለፉት መልዕክት ሰው ሰራሽ አስተውሎት ሊያግዝ እንደሚችል ሆኖም በጋዜጠኝነት ወሳኝ ጉዳዮች ግን በሰው ልጅ መወሰን እንደሚገባቸው ተናግረዋል። ሊምቡርግ መድረኩ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መነጋገር መቻሉን አድንንቀዋል። 
«ሰው ሰራሽ አስተውሎትም ይሁን የዩክሬን ጦርነት ወይም የመድረኮች ሃላፊነት እንዲሁም መካከለኛው ምሥራቅ በርካታ ጽንፎች አሉ። ሆኖም እዚህ ቦን በዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሀን መድረክ ቢያንስ እንነጋገርባቸዋለን።» ንግግሩ ሲቀጥል ዴሞክራሲ ይኖራል። ይህ እዚህ ሁሉም የተጋሩት ይመስላል። 

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ