የዘር ፍጅት ያሰጋት ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ | አፍሪቃ | DW | 26.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የዘር ፍጅት ያሰጋት ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ

ግጭት እና ሁከት አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለባት ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የሰብዓዊ መብት ይዞታ እጅግ ተበላሽቷል። በሰበቡም የሲብሉ ሕዝብ ስቃይና መከራ በዝቷል። ሀገሪቱም ወደከፋ ደረጃ እንዳትሸጋገር አስግቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:53
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:53 ደቂቃ

«ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ለሌላው የዓለም ከፊል ስልታዊ ስጋት የደቀነች ሀገር ሆና አለመታየቷ ችግር ደቅኗል።»

ከጎርጎሪዮሳዊው መጋቢት 2013 ዓም ወዲህ ውዝግብ ባላቋረጠባት ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ውስጥ በወቅቱ የመጀመሪያዎቹ የዘር ማጥፋት ርምጃ ምልክቶች እየታዩ ነው ሲል የተመድ አስጠነቀቀ።   ከጥቂት ጊዜ ወዲህ ተጠናክሮ እየተካሄደ ያለው ግጭት እየከፋ ሊሄድ  እና ሀገሪቱን ወደዘር ፍጅት ሊያመራ እንደሚችል የተመድ አስቸኳይ ርዳታ አስተባባሪ ስቴፈን ኦብሪየን  ጠቁመው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ባፋጣኝ ርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል። የዓለሙ መንግሥታት ድርጅት ሲቭሉን ህዝብ ለመከላከል እና በፕሬዚደንት ፎስተ አርሾንዥ ቱዋዴራ የሚመራውን መንግሥት ለመደገፍ በዚችው ሀገር ያሰማራውን 12,500 ሰላም አስከባሪ ቁጥርም እንዲያሳድግ  ስቴፈን ኦብሪየን በተጨማሪ ጠይቀዋል። በውጊያው የተመድ ወታደሮችች እና ሲቭሎችም ሰለባ ሆነዋል።  በዚህ በተያዘው ጎርጎሪዮሳዊው 2017 ዓመት ብቻ እንኳን  800 ሲቭሎች ተገድለዋል። ከአንድ ሚልዮን የሚበልጥ ሰው ደግሞ ተሰዷል።  ሀገሪቱን ከጥቂት ጊዜ በፊት የጎበኙት ኦብሪያን እንዳስታወቁት፣ ከ4,5 ሚልዮኑ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ህዝብ መካከል በቀጠለው የኃይል ርምጃ ሰበብ የተፈናቀለው ሰው ቁጥር አምና በዚሁ ጊዜ ከተመዘገበው በ40% ከፍ ብሏል። ታዛቢዎች እንዳመለከቱትም፣ በሙስሊም የሴሌካ እና የክርስትያኖቹ ፀረ ባላካ ዓማፅያን ቡድኖች መካከል በዚህ ሳምንት ውጊያው እንደአዲስ ያገረሸው ውጊያ በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች  የኃይሉ ተግባርን አባብሶ ለብዙዎች መፈናቀልም ምክንያት ሆኗል። የሀገሪቱ የሰብዓዊ መብት ይዞታ እጅግ አስከፊ ሆኗል። 
በውጊያው ወቅት የተፈጸመው ዘግናኝ ጥቃት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶችም አስታውቀዋል። «በኃይሉ ተግባር ሰበብ ምንም ስራ መስራት አልቻልንም፣ ሁሌ የጥቃት ዒላማ በሆንበት እና ሰራተኞቻችንም በሚጠቁባት ሀገር ውስጥ ለመስራት አልቻልንም፣»  ሲሉ አምስት ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች ለተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶንዮ ጉተረሽ በጋራ በላኩት ግልጽ ደብዳቤ አመልክተዋል።  የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም የሁኔታውን አሳሳቢነት አጉልተዋል፣ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፣ ሂውመን ራይትስ ዎች ባልደረባ ልዊስ ማጅ በዚችው አፍሪቃዊት ሀገር የሰላም ማስከበር ተግባር በማከናወን ላይ የሚገኘው የተመድ ተጨማሪ ርምጃ እንዲወስድ  ጠይቀዋል።


«እነዚህ ዓማፅያን መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት እንኳን የማያከብሩ ናቸው። የጦር ወንጀል ይፈጽማሉ። ይህም ነው ሁኔታውን አሳሳቢ ያደረገው። እና በነዚህ ተቀናቃኝ ቡድኖች መካከል ሰላማዊ ውይይት ማካሄድ፣ ወንጀል የፈጸሙትን በኃላፊነት መጠየቅ እና በተወሰነ ደረጃም የጦር መሳሪያ ትጥቅ ማስፈታትቱ የሚቻልበትን ቅድመ ሁኔታ ማመቻቸት እንግዲህ በሀገሪቱ እዚህም እዚያ የተሰማራው የተመድ ተግባር መሆን ይኖርበታል። »
ልዊስ ማጅ ያቀረቡት ሀሳብ የሚደገፍ ነው። ይሁንና፣ ሀሳቡን በተግባር መተርጎሙ ከአቅም በላይ እንደሆነ ነው የሚነገረው። የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ባወጧቸው ዘገቦች መሰረት፣ ምንም እንኳን 12,500 የተመድ ሰላም አስከባሪዎች በሀገሪቱ ቢሰማሩም ፣ ዓማፅያኑ ቡድኖች በወቅቱ ከ70% በላይ የሚሆነውን አካባቢ ተቆጣጥረዋል። የሴሌካ ዓማፅያን በጎርጎሪዮሳዊው መጋቢት፣ 2013 ዓም የቀድሞ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ  ፕሬዚደንት ፍሯንስዋ ቦዚዜን ከስልጣን ካስወግዱ በኋላ በሀገሪቱ ያስፋፉትን የኃይል ተግባር ለማስቆም በ2014 ዓም የቀድሞዋ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ እና የአፍሪቃ ህብረት ወታደሮች፣ ወደኋላም ላይ የተመድ ሰላም አስከባሪ፣ የሚኑስካ ወታደሮች በሀገሪቱ ቢሰማሩም ፣ ተግባራቸው ከመዲናይቱ ባንጊ አካባቢ አለማለፉ ችግሩን እንዳላስወገደ ቻተም ሀውስ የተባለው የብሪታንያውያኑ ፖለቲካ ተቋም ተንታኝ ፖል ሜሊ ከዶይቸ ቬለ ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል።
« ሀገሪቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ካየነው በባሰ ሁኔታ ወደከፋው የኃይል ተግባር ልትመለስ የምትችልበት ትልቅ ስጋት አለ። ይህም ሊሆን የቻለው የተመድ እና ፈረንሳይ በጎርጎሪዮሳዊው 2013 ዓም ባደረጉት ጣልቃ ገብነት መዲናዋን ባንጊ ብቻ አረጋግተው፣  ሰሜኑን እና ምሥራቃዊውን የሀገሪቱን ከፊል ለጦር ባላባቶች የተዉበት ድርጊት አሁን የሚታየውን ሁኔታ ፈጥሯል። ከዚሁ አካባቢ መካከልም አንዳንዱ ግዙፍ የማዕድን ይዘት አለው፣ ለምሳሌ ብሪያ በአልማዝ ማዕድን ይዘቱ ይታወቃል። እና እነዚህ የጦር ባላባቶች የራሳቸውን ኤኮኖሚያዊ ጥቅም ለማረጋገጥ ይችሉ ዘንድ በማዕድን ከታደለው አካባቢ ብዙውን ለመቆጣጠር ውጊያ ያካሂዳሉ።»

Demokratische Republik Kongo Mine Diamanten Diamantenmine (AP)

የጦር ክንፍ አዛዥ ኑረዲን አዳም በሚመሩት የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ዳግም ውልደት የህዝብ ግንባር፣ በምህፃሩ በኤፍፒአርሲ ውስጥ ልዩነቱ  እየገዘፈ መሄዱ ቡድኑ እንዳይከፋፈል እና የሀገሪቱን ችግርም  ይበልጡን እንዳያወሳስበው ስጋት መኖሩን  ተንታኙ ገልጸዋል።   
ከመጋቢት 2016 ዓም ወዲህ በስልጣን ላይ የሚገኘው የፕሬዚደንት ፎስተ አርሾንዥ ቱዋዴራ የሚመሩት የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ መንግሥትም  የኃይሉን ተግባር ማስቆም አልሆነለትም።  እንደ ፖለቲካ ተንታኙ ፖል ሜሊ አስተያየት፣ ደካማ የሚሉት የሀገሪቱ መንግሥት የዓማፅያን ቡድን መሪዎችን በድርድር በፖለቲካ ስልጣን መዋቅር ውስጥ ማዋኃድ አልቻለም፣ የጦር ወንጀል ፈጸሙ የሚባሉትን ዓማፅያንን በኃላፊነት የሚጠይቅ ልዩ ፍርድ ቤት ቢቋቋምም ስራውን አልጀመረም። እና ዓማፅያኔ በኃላፊነት እስካልተጠየቁ ድረስ ውጊያውን እንደማያቆሙ ፖል ሜሊ ግምታቸውን ሰጥተዋል። እርግጥ፣ በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ መንግሥት እና በዓማፅያን ቡድኖች መካከል ባለፈው ሰኔ ወር አንድ የሰላም ውል ተፈርሞ እንደነበር ሊ,ሂውመን ራይትስ ዎች ባልደረባ ልዊስ ማጅ አስታውሰዋል፣ ግን፣ ብዙም ሳይቆይ  የማዕድኑ አልማዝ ማዕከል በምትባለው በብሪያ አካባቢ በተቀናቃኝ ዓማፅያን ቡድኖች መካከል  በፈነዳው ውጊያ ሰበብ ወዲያው መፍረሱን እና በውጊያ ከሁለቱም ወገኖች ከ100 የሚበልጥ ሰው መገደሉን ማጅ ገልጸዋል። የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክን ለማረጋጋት  ብቸኛው መንገድ ሚኑስካን ማጠናከር መሆኑን የቻተም ሀውስ ተንታኝ ፖል ሜሊ አስረድተዋል።


« የተመድ ጓድ ተልዕኮ ባፋጣኝ ሊጠናከር ይገባል በሚለው ጉዳይ ላይ ስምምነት ያለ ይመስላል። ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክን በመሰለች ትልቅ ሀገር ውስጥ የመጓጓዣው ግንኙነት ቀላል ስላልሆነ ጓዱ ተጨማሪ ሄሊኮፕተሮች፣ አይሮፕላኖች እና ተጨማሪ ወታደሮች እንዲቀርቡለት ጠይቋል። በቅርቡም በሚገባ የሰለጠነ ፈጣን አጥቂ ጦር ከዛምቢያ ይላካል ተብሎ ይጠበቃል። እርግጥ ፈረንሳውያኑ ወታደሮች ከማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ለቀው ወጥተዋል፣ ግን በጎረቤት ቻድ የጦር ሰፈር ስላቸው የተጨማሪ ሄሊኮፕተሮች አቅርቦትን በተመለከተ ሊረዱ ይችሉ ይሆናል። »
ይሁንና፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማዕከላይ አፍሪቃ ውዝግብ ለተሰማራው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ፣ ሚኑስካ  ጦር መዋጮ ላይ ለመሳተፍ እንደማይፈልጉ ፖል ሜሊ አስታውቀዋል።
« ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ፣ በማሊ አንጻር፣  ለሌላው የዓለም ከፊል ስልታዊ ስጋት የደቀነች ሀገር ሆና አለመታየቷ ችግር ሊሆን ይችላል።  »  
ከግጭት እና ሁከት ከቀጠለባት ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ዜጋ  መካከል ከየሁለቱ  አንዱ በርዳታ ላይ ጥገኛ ነው። በተመድ የልማት መመዘኛ መዘርዝር ውስጥ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ እጅግ ድሆች ከሚባሉት ሀገራት መካከል የመጨረሻው ደረጃ ላይ ትገኛለች። የፖለቲካ ተንታኙ ፖል ሜሊ እንደሚሉት፣ ሀገሪቱ እስካልተረጋጋችም ድረስ ይህ ሁኔታ መለወጡ አዳጋች ይሆናል። 

አርያም ተክሌ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች