የ“ዘመን” ፈርጦች | ወጣቶች | DW | 17.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

የ“ዘመን” ፈርጦች

በኢትዮጵያ የጥበብ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች ችሎታ እና አቅማቸውን የሚያሳዩባቸውን መድረኮች ማግኘት ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ዝንባሌ ያላቸዉ ወጣቶች-ሁሉም ማለት ባንችልም- ቦታ ቢያገኙ ብቃታቸውን ሊያሳዩ እንደሚችሉ ለመታዘብ አሁን በዕይታ ላይ ያለውን “ዘመን” ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማን መመልከት በቂ ነው፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:56

የዘመን ድራማ ወጣት ተዋንያን

የአንድ ቤተሰብ ፍንካቾች፣ የ“እናት ሆድ ዥንጉርጉር” ማሳያዎች ፣ የዘመኑ ወጣት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ እርሷ የግል ኮሌጅ ተማሪ፣  ዓላማ አለኝ የምትል፣ አንገት ደፊ፣ አባቷ የሚንሰፈሰፉላት ኮረዳ ነች፡፡ እርሱ ሁለተኛ ደረጃን አጠናቅቆ ያለስራ የተቀመጠ፣ ከትምህርትም ከስራም አለመሆኑን በቀልድ እና ጨዋታ ለማምለጥ የሚሞክር፣ ገንዘብ ለማግኘት አለ የተባለውን አቋራጭ መንገድ ሁሉ የሚያስስ ጎረምሳ ነው፡፡ ኃይለኛውና ቁጡው ጫማ ሰፊ አባታቸው አቶ በልሁ በእርሷ እየኮሩ፣ በእርሱ እያፈሩ፣ ቤተሰባቸው ውስጥ ያለን ውጥንቅጥቅ መፍታት አቅቷቸው የሚውተረተሩ ናቸው፡፡

በቤተሰብ የዕለት ተዕለት ህይወት ላይ ማጠንጠኛው ያደረገው “ዘመን” ድራማ ከስራ አጥነት እስከ ስደት፣ ከተማሪ አስተማሪ ግንኙነት እስከ የትዳር ችግሮች ያሉ ማሕበራዊ  አጀንዳዎችን ያነሳል፡፡ የህይወትን ገጸ-ባህሪ የተላበሰችው የ21 ዓመቷ ጸደይ ፋንታሁን ስትሆን የአቡሽን ደግሞ የ27 ዓመቱ ትንሳኤ ብርሃነ እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ጸደይ እና ትንሳኤ በ“ዘመን” ድራማ ላይ የመሳተፍ ዕድል ያገኙት የድራማው ደራሲዎች እና አዘጋጆች ያወጡትን የተዋኞች  መለኪያን (audtition) አልፈው ነው፡፡ በድራማው ውስጥ ላሉ የተለያዩ ሚናዎች እስከ 600 ተዋኞች መወዳደራቸውን አዘጋጆቹ ይናገራሉ፡፡ ጸደይ ከአንድም ሁለቴ የምልመላ ፈተና መውሰዷን ትገልጻለች፡፡ በመጀመሪያ የተሰጣት ሚና ሳሮን የተሰኘችውን ገጸ-ባህሪ ለመጫወት ሲሆን አሁን የተላበሳችትን ገጸ-ባህሪ ያገኘችው የዕድሜያዋ መቀራረብ ታይቶ እንደሆነ ታስረዳለች፡፡

ውድድር እና ፈተና ለጸደይ አዲስ ነገሮች አይደሉም፡፡ “የማለዳ ኮኮቦች” በተሰኘ የትወና ተሰጥኦ ውድድር የመጀመሪያ ዙር ላይ ተሳትፋ የአሸናፊነቱን አክሊል ደፍታለች፡፡ ውድድሩ ሶስተኛ ዙር ደርሶ “ዘመን” ድራማ እየተላለፈበት በሚገኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ በየሳምንቱ መታየቱን ቀጥሏል፡፡ “ተዋኝ ለመሆን ማሰብ የጀመርኩት ከዘጠኝ ዓመቴ ጀምሮ ነበር” ለምትለው ጸደይ ይህ ውድድር ህልሟን ለማሳካት ላደረገችው ጉዞ መንገዱን ጠርጎላታል፡፡

Äthiopien Addis Abeba - Drama Filmarbeiten

የዘመን ድራማ በቀረጻ ላይ

የድራማው ወንድሟ ትንሳኤ ግን ወደ ትወና እንኳ የገባው በአጋጣሚ ነው፡፡ ሊያውም ካፌ ውስጥ በተዋወቀው ሰው አማካኝነት፡፡ ሰውየው ዲንጎ በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው የሀገር ፍቅር ተዋኝ ዘነበ ተስፋዬ ነበር፡፡ ከትንሳኤ ጋር ሲያወጉ ፊልም መስራት ይፈልግ እንደሁ ይጠይቀዋል፡፡ በእንጦጦ ቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ቤት የአውቶሚካኒክ ተማሪ የነበረው ትንሳኤ ከትምህርቱ ጎን ሊያስኬደው እንደሚችል ያሰላና እሺታውን ይገልጻል፡፡

ይህ ቀላል አጋጣሚ ትንሳኤን ወደ ጥበቡ ዓለም ጎትቶ ማምጣት ብቻ ሳይሆን በሙሉ ጊዜ ትያትር ላይ ለመተወን ዕድሉን ይከፍትለታል፡፡ አንድ ዓመት የፈጀው “ግራና ቀኝ” የተሰኘው ትያትር ልምምድ ለትንሳኤ የትወና ትምህርት ቤቱ ነበር፡፡ ትያትሩ ወደ መድረክ ሲወጣ ዲንጎን ጨምሮ ስም ካላቸው ተዋንያን ጎን መሰለፍ ቻለ፡፡ ነገር ግን ትያትሩ እንደታሰበው ረጅም ጊዜ አልተጓዘም፡፡

በትያትር ዓይኑን የገለጠው ትንሳኤ እንደገና ዕድል በሩን አንኳኩታ እስክትመጣ ከጥበብ መንደር ጠፍቶ ቆይቷል፡፡ ጭራሹኑ የተመረቀበትን የአውቶሜካኒክ ሙያ ትቶ አካውንቲንግ ለማጥናት ቅድስተማርያም ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ተመዘግቦ መማር ይጀምራል፡፡ አሁንም ካፌ ውስጥ ያገኘው ሰው ወደ ትወና ይመልሰዋል፡፡ ሰውየው በሃይሉ ዋሴ የተባለ የፊልም አዘጋጅ ነበር፡፡ “የልደቴ ቀን” የተሰኘ ፊልሙን ለመቅረጽ እየተዘጋጀ ነበርና ትንሳኤን ለተዋኞች በተዘጋጀ የምልመላ ፈተና ላይ እንዲሳተፍ ይጋብዘዋል፡፡ ፈተናውን አልፎም በፊልሙ ላይ ተሳተፈ፡፡

ትንሳኤ ብርሃነ -የዘመን ድራማ ተዋናይ

ትንሳኤ ብርሃነ -የዘመን ድራማ ተዋናይ

በአንድ ትያትርና ፊልም ተሳትፎው ዕውቅና እና ተከታታይ ስራዎች እንደሚመጡለት የተማመነው ትንሳኤ ብዙ ጠበቀ፡፡ ግን ምንም አላገኘም፡፡ ባገኘው የተዋኞች ምልመላ ፈተና ላይ ተሳተፈ፡፡ ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡ አስራ ስምንት ዓመት ሲሞላው ቤተሰቡን ተሰናብቶ ህይወቱን ለብቻው መምራት ጀምሮ ነበርና ራሱን ለማስተዳደር ስራ ማፈላለግ ያዘ፡፡ ሩቅ ሳይሄድ ገንዘብ ሲኖረው ያዘወትረው ከነበረ ምግብ ቤት ስራ ጠየቀ፡፡ በአዲስ አበባ እምብርት ፒያሳ የሚገኘው ይህ ምግብ ቤት ትንሳኤን በአስተናጋጅነት ቀጠረው፡፡ እስካሁንም በዚህ ቤት አለ፡፡

ትንሳኤ በምግብ ቤቱ ከፍ ያለው የስራ ደረጃ ላይ ቢደርስም በአጋጣሚ የተሳበበትን የትወና ህይወት ሙሉ በሙሉ አልተወም፡፡ በተዋናይ ምልመላዎች ላይም መሳተፉን አላቋረጠም፡፡ ቀደም ሲል “ሰው ለሰው” በተሰኘ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ድራማቸው ዝና ያተረፉት አዘጋጆች አዲስ ድራማ ለመስራት ሰው እየመለመሉ መሆኑን ሲሰማ በደስታ ነበር ወደ ቦታው የሄደው፡፡ እንደ ጸደይ ሁሉ በሁለት የተለያዩ ገጸ-ባህርያት ሁለት ፈተና ወስዶ ነው የ“ዘመን” ድራማ የተዋናያንን ቡድን የተቀላቀለው፡፡ 

በኢትዮጵያ መዝናኛ ላይ የሚያተኩሩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቁጥር ከፍ ማለትን ተከትሎ የተከታታይ ድራማዎች ቁጥርም ጨምሯል፡፡ ይህ ደግሞ ፉክክሩን አበርትቶታል፡፡ መስከረም ላይ የተጀመረው “ዘመን” በሳምንት ሁለቴ እየታየ ሃያኛ ክፍሉ ላይ ደርሷል፡፡ በሳተላይት የቴሌቪዥን ስርጭት ከሚታየው በተጨማሪ በዩ-ቲዩብ አማካኝነት እስከ አራት መቶ ሺህዎች ሰዎች ድራማውን እየተከታተሉት ይገኛሉ፡፡

“ዘመን”ን ቀልብ እንዲስብ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ በርከት ያሉ ወጣትና አዳዲስ ተዋናዮችን ማሳተፉ ነው፡፡ ከወጣቶቹ ተዋናያን ውስጥ ደግሞ በተሻለ የትወና ብቃት ስማቸው በተመልካች ተደጋግሞ ሲነሳ የሚደመጠው ጸደይ እና ትንሳኤ ናቸው፡፡ የድራማው ረዳት አዘጋጅ እና ሲኒማቶግራፈር ታሪኩ ደሳለኝም የተመልካቾችን አስተያየት ይጋራል፡፡ ሁለቱ ወጣቶች እያሳዩት ያለው ብቃት “ከሚጠበቀው በላይ” እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ገጸ-ባህሪያቸውን ለመረዳት የሚያደርጉትን ጥረትም ያደንቃል፡፡ 

Television serial drama in Ethiopia

የዘመን ድራማ በቀረፃ ላይ

የ“ማለዳ ኮኮቦች” ጠንሳሽ እና አዘጋጅ ፍጹም አስፋው በታሪኩ ገለጻ ይስማማል፡፡ በውድድር ወቅት የጸደይን ችሎታ በቅርበት የተመለከተው ፍጹም የተሰጣትን ገጸ-ባህሪ ለመረዳት “ሰፊ ጊዜ ወስዳ የምትለማመድ” እና “ከፍተኛ ጥረት” የምትደርግ እንደሆነች ይመሰክርላታል፡፡ ጸደይ ከታዋቂ ተዋናያን ጋር ስትተውን ብቃቷን ማሳየቷ ፍጹምን እንዳስደመመው ሁሉ አብረዋት የሚተውኑት ዝነኞችም በእርሷ አተዋወን ተገርመዋል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሆነ አጋጣሚን ሲኒማቶግራፈሩ ታሪኩ ያስታውሳል፡፡ የጫማ ሰፊውን የአቶ በልሁን ገጸ-ባህሪ የሚጫወተው አበበ ባልቻ እና ልጁ ሆና የምትተውነው ጸደይ በድራማው ውስጥ ያሉ የተለያዩ ክፍሎችን ለየብቻቸው ሲቀረጹ ከርመዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት በድራማው ክፍል አንድ የቀረበን ገቢር ሲጫወቱ ነበር፡፡

ገቢሩ ልጃቸውን እንደዓይናቸው ብሌን የሚሳሱላት ተደርገው የተሳሉት አቶ በልሁ ከልጃቸው በሚቀርብላቸው ፈታኝ ጥያቄ ምክንያት እጃቸውን ሲያነሱባት የሚሳይ ስሜት ቆንጣጭ ትዕይንት ነው፡፡ ቀረጻው እንደተጠናቀቀ በጸደይ የተገረመው አበበ ባልቻ ቆሞ እንዳጨበጨበላት ታሪኩ ይናገራል፡፡ ከአንጋፋዎቹ እና ታዋቂዎቹ ተዋናዮች የሚሰጣቸው እንዲህ አይነት ማበረታቻዎች ባይኖሩ ኖሩ ትወናው ይከብዳቸው እንደነበር ጸደይም ሆነች ትንሳኤ ይናገራሉ፡፡ የረጅም ዓመታት የትወና ልምድ ካላቸው ተዋናዮች ጎን መስራታቸው ብዙ እንዳስተማራቸውም ይገልጻሉ፡፡

ጸደይም ሆነች ትንሳኤ እንዲህ እንዳሁኑ የዝና እርካብን ከመርገጣቸው በፊት በርካታ ተስፋ አስቆራጭ ፈተናዎችን አልፈዋል፡፡ የመተወን ፍላጎታቸው በቤተሰብም በጓደኛም አልተወደደላቸውም፡፡ ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ የሚጎተጉታቸው ብዙ ነበር፡፡ ችሎታቸውን የሚያሳዩበት መድረክ በቀላሉ አለመገኘትም ጉዟቸውን አዳጋች አድርጎባቸዋል፡፡ አሁን ህልማቸውን ለመኖር መንገዱን እንደጀመሩት ይሰማቸዋል፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ

 

 

 

Audios and videos on the topic