የ«ዘመን» እንግልትና፥ ስጋት ያጠላበት ሐይቅ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 14.07.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የ«ዘመን» እንግልትና፥ ስጋት ያጠላበት ሐይቅ

በአማርኛ ቋንቋ የሚተላለፈው «ዘመን» የተሰኘው የቴሌቪዝን ድራማ ተዋንያን እና ባልደረቦች በምሥራቅ ኢትዮጵያ የደረሰባቸው መንገላታት በዛሬው ዝግጅታችን ትኩረት ተሰጥቶታል። «እንቦጭ» የተሰኘው አረም በጣና ሐይቅ ላይ የደቀነው ስጋትም ሌላኛው ርእሳችን ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:57

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ጣናን ምን ነካው? የብዙዎች ጥያቄ ነው። ጣና ሐይቅ «እምቦጭ» በተሰኘ መጤ አረም የመወረሩ ዜና በርካቶችን አሳስቧል። የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ርእስም ኾኗል። ከኢትዮጵያ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች መካከል አንዱ የኾነው «ዘመን» ድራማ ባልደረቦች በምሥራቅ ኢትዮጵያ ሶማሌ ለቀረጻ ወጥተው እንግልት እንደደረሰባቸው በዚሁ መድረክ ገልጸዋል። የድራማው ሠሪዎች የአካባቢው ፖሊስ በስህተት ላደረሰባቸው እንግልት ይቅርታ እንደጠየቃቸው በፌስቡክ ገጻቸዉ ተናግረዋል። የለም ሌላ ተልዕኮ ነበራቸው ሲል በዛው በፌስቡክ ላይ የጻፈም አለ። ጽሑፍን «ተረት ተረት» ሲሉ የተቹም አልጠፉም። 

በሳምንት ሁለት ጊዜ የሚቀርበው «ዘመን» ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ባልደረቦች በምሥራቅ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል  በጸጥታ ኃይላት ደረሰብን ያሉት ውጣ ውረድ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ትኩረት ስቧል። የድራማ ቀረጻው አባላት ስለ ስደተኞች ለመቅረጽ በሄዱበት ሥፍራ አጋጠመን ስላሉት እንግልት ሲገልጹ፥ አባላቱ ለተለየ ተልዕኮ በሥፍራው መከሰታቸውን በመግለጥ የሚከስ ጽሑፍም በዛው በማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተነቧል። 

የ«ዘመን» ድራማ ቀረጻ ወብርሃን መሪ (director of photography) ታሪኩ ደሳለኝ በወቅቱ ስለገጠማቸው በፌስቡክ ገጹ በዝርዝር ጽፏል። በእስር ላይ የሚገኘው፥ የታዋቂው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ታናሽ ወንድም ታሪኩ ደሳለኝ በሥፍራው የሶማሊኛ ቋንቋ ተናጋሪ በሆኑ፤ መሣሪያ በታጠቁ የጸጥታ ኃይላት እየተዋከቡ በመኪና ተጭነው መወሰዳቸውን ተናግሯል።

 

«ከሠላሳ በላይ ባለጠብ-መንጃ ወታደር ከተኮሳተረ ፊት ጋር በምሽት ዙሪያህን በሦስት ፒካፕ የወታደር መኪናና በአንድ ድፌንደር መኪና ተከበህ መሣሪያ እየተቀባበለብህ መሰማት መናገር በማትችልበት ቋንቋ ከዚህም ከዚያ `ጋንተ ዲብ` እጅ ስጥ ስትባል ምን እንደሚሰማህ አስበው?» ሲል በወቅቱ ስለደረሰባቸው በዝርዝር ጽፏል።

የታሪኩ ጽሑፍ ዘለግ ያለ ቢሆንም በአካባቢው ደረሰብን ያሉትን በዝርዝር በዐይነ-ኅሊና የሚያሳይ ነው። ምስል ከሳቹ የታሪኩ ጽሑፍ እንዲህ ይቀጥላል፦ «ግራ በመጋባትና ከአሁን አሁን ምን ሊፈጠር ነው ብለን እየጠበቅን ከወታደሮቹ ጋር ስንተያይ ድንገት ከመሀላቸው አንዱ በግማሽ አማርኛ በንዴት አፍጥጦ እያየን ‘እዚህ ምን ልትሠሩ መጣችሁ? እዚህ ምንድነው የምትሠሩት’ አለን ‘በመጀመሪያ እዚህ የመጣነው ሀገራችን ስለሆነ ነው...’ ከማለቴ በወታደር ጫማ ከጉልበቴ ስር ተመታሁ ሌሎችም ወታደሮቹ በያዙት ዱላ ባገኙት ነገር ወንድ ሴት ሳይሉ እየተማቱ በከፍተኛ እንግልት ፒካፕ መኪናቸው ላይ ወረወሩን...» ያለው ታሪኩ ወታደሮቹ በተሽከርካሪያቸው ከጫኗቸው በኋላ በኮሮኮንች መንገድ ላይ በ160 የመኪና ፍጥነት 12 ኪ.ሜ እየከነፉ በማሽከርከር እንደወሰዷቸው ገልጧል። 

ከዚያም አንድ ግቢ ውስጥ አስገቡን ያለው ታሪኩ ኹኔታውን ያብራራል። «ግቢ ውስጥ እንደገባን ከመኪናው ላይ እየጉተቱ ካወረዱን በኋላ የያዝነውን ዕቃ ፊት ለፊት እንድናስቀምጥ ካደረጉን በኋላ በየተራ እያስቆሙ፣ እያመናጨቁ ፈተሹን። ወንዶችን ለብቻ ሴቶችንም ለብቻ ካደረጉን በኋላ የመጡት ወታደሮች ሁሉ ከ10 ጊዜ በላይ ቆጠሩን። ይሄ ሁሉ ሲሆን እንድናወራ አልፈቀዱልንም እራሳቸው ይጠይቃሉ፥ እራሳቸው ይመልሳሉ ደግሞም ይጮሀሉ። ከቆጠራና ከፍተሻ በኋላ ወንዶችን በሦስት መስመር እንድንቀመጥ አደረጉን። ወደ ፊታችን ሁለት ሰዎች መተው ቆሙ፤ አንደኛው የእጅ ሽጉጥ የያዘ ሲሆን ሁለተኛው ሽመል ይዟል። እነዚህ ሰዎች ከመጀመሪያው ጀምሮ በነሱ ትእዛዝ የያዝነው ንብረቶች እየተወረ[ወሩ] መኪና ውስጥ እንዲገባ እና እኛም ተጭነን እንድንመጣ ትእዛዝ ሲሰጡ የነበሩት ግለሰቦች ናቸው። ባለመሣሪያው የአካባቢው የፀጥታ ክፍል ኃላፊ ሲሆን፤ ባለሽመሉ የፖሊስ ኮሚሽን ነው። ሁለቱ ሰዎች ወደኛ እንደቀረቡ ወታደሮቹም ዙሪያችንን ከበው እጃቸውን የመሣሪያቸው መላጭ ላይ አደረጉ ... » በማለት ይቀጥላል የታሪኩ ጽሑፍ። 

Television serial drama in Ethiopia

ዘመን የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማ፥ ታሪኩ ደሳለኝ በቀረጻ ወቅት

ታሪኩ ተፈጸመብን ያለው ድርጊት የተከሰተው፦ «ዓርብ ሰኔ 30 ቀን 2009ዓ.ም ከአዲስ አበባ 592 ኬሎ ሜትር እርቀት ላይ በምትገኘው የሱማሌ ክልል በሆነችው ሽንሌ ወረዳ (ድሬደዋ ኬላ) ከምሽቱ 1:20 ላይ» እንደሆነም ገልጧል። የፀጥታ ኃላፊው ስልክ ደውሎ ንግግሩን ከጨረሰ በኋላ ነገሩ መርገቡን የገለጠው ታሪኩ ኃላፊው «አንድ ቃል ተናገረ፤ ተተረጉመልን ‘አሁን አውቀናል ሄዱ’ ተባልን እንግዲህ ምን እናድርግ ሄደን» ብሏል። ወደ አካባቢው «ዘመን ድራማን ለመሥራት» ሲሄዱም ለ3ኛ ጊዜያቸው እንደነበር ጽፏል። 

የ«ዘመን» ድራማ ባልደረቦች ለቀረጻ ወደ ሥፍራው በሄዱበት ወቅት «ድሬደዋ ከተማ በከፍተኛ ውጥረት በተለያየ ቦታ መንገድ ተዘግቶ በወታደሮች እየተጠበቀች» እንደነበር ታሪኩ ገልጧል። «ምክንያቱም» ይላል ታሪኩ «ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ስለነበሩ ነው። እኛም ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ ካሉበት 16 ኬ.ሜ እርቀት ላይ ነበርን። ዳሩ መንግሥት የመንግስት ብቻ እንደሆነ ህዝብም ህዝብ እንደሆነ በአንድ ሀገር ሳንተያይ መኖር ከጀምርን 26 አመት አልፎናል» ሲልም ጽሑፉን አጠቃሏል። 

ሲፒጄ በተባለው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ተቋም በአንድ ወቅት የዓለም የፕረስ ነፃነት ተሸላሚ የነበረውና አውራምባ ታይምስ የተሰኘዉ የአማርኛ ጋዜጣ አዘጋጅ ዳዊት ከበደ በበኩሉ ከታሪኩ ደሳለኝ ጽሑፍ ፈጽሞ ተቃራኒ የሆነ ሌላ ጽሑፍ በፌስቡክ ገጹ ላይ አስነብቧል። የዳዊት ጽሑፍ፦«የዘመን ድራማ ፕሮዲውሰሮች በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ለምን ችግር ገጠማቸው?» በሚል ርእስ ነው የሚንደረደረው።

Television serial drama in Ethiopia

የዘመን ድራማ ቀረጻ

«ፕሮዲውሰሮቹ ‘በድራማ ቀረጻ’ ሰበብ በድብቅ የቀረጹትን footage [የቪዲዮ ምስል ለማለት ነው]  አውሮጳ ለሚገኝ አንድ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም እንዲያቀብሉ ተልእኮ ተሰጥቷቸው ነበር።  የቡድኑ አባላት ወደ ክልሉ ለቀረጻ የገቡት ከክልሉ መንግሥት እውቅና ውጪ በድብቅ ነው» ብሏል ዳዊት። 

«ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ማምሻው ላይ ያገኘሁትን መረጃ ይዤ ቀርቤያለሁ» ያለው ዳዊት የ«ዘመን» ድራማ አባላት «በድብቅ ቀረጹት» ስላለው የቪዲዮ ምስል ማረጋገጫ  በጽሑፉ ላይ አላቀረበም። ይልቁንስ ዳዊት አካባቢው ቀድሞ የነበረውን እና አሁን የሚገኝበትን የጸጥታ ኹኔታ በስፋት በመተንተን ከዚህ ቀደም በአካባቢው በጸጥታ ኃይላት ታስረው ስለነበሩ የውጭ ጋዜጠኞች በሰፊው አትቷል።

ዳዊት ከአካባቢው የጸጥታ ኃላፊ አገኘሁት ባለው መረጃ የ«ዘመን» ድራማ ፕሮዲውሰሮች ውጭ ከሚገኝ ድርጅት ጋር ግንኙነት አድርገዋል ይላል። ለዚህም ቢሆን መረጃውን ይፋ አላደረገም። ዳዊት ይቀጥላል፦ «በተደረገው የኤሌክትሮኒክ መረጃ ልውውጥ ድራማው ስለስደት የሚያሳይ [ትእይንት] ስላለው ይህንን ወርቃማ አጋጣሚ በ ‘ድራማ ቀረጻ‘  ሰበብ በድብቅ ወደ ክልሉ ገብተው ለሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ስሞታ የሚመች የቪዲዮ (footage) ቀርጸው እንዲያቀብሏቸው ያለመ» መሆኑን ኃላፊው ነገሩኝ ይላል።

ዳዊት በጽሑፉ ማጠቃለያ ላይ ባሰፈረው ዐረፍተ-ነገር ግን ከላይ የገለጠውን የራሱን ክስ የሚቃረን ጽሑፍ ጽፏል። «ሳያስፈቅዱ ለቀረጻ መግባታቸው ብቻውን ከጥርጣሬ በዘለለ የውጭ ኃይል ተባባሪ ናቸው ብሎ ለመደምደም አያበቃም» በሚል። ይኽንንም የጸጥታው ኃላፊ እንደነገሩት ገልጧል። 

የድራማው ባልደረቦችም ያለፈቃድ ወደ ሥፍራው መንቀሳቀሳቸውን ጽፏል። የዳዊት ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦«ሆኖም የድራማው ቡድን አባላት ወደ ክልሉ የገቡት በድብቅ በመሆኑ የክልሉ የጸጥታ አካላት ቀረጻውን እንዲያካሂዱ አልፈቀዱላቸውም ብቻ ሳይሆን የተፈጸመው ድርጊት ሕገወጥ ስለሆነ በልጆቹ ላይ ምርመራ ለማካሄድ ተገደዋል ብለውናል።» 

Somali Äthiopien Shinile-Zone Dürre erschwert Lebensbedingungen

ድርቅ የሚያጠቃው የሽንሌ ዞን ከፊል ገጽታ

የ«ዘመን» ድራማ ደራሲ መስፍን ጌታቸው ለዳዊት አጭር መልእክት በፌስቡክ አስፍሯል። «ወንድሜ ዳዊት ሆይ እውነቱን በጣም ስተኸዋል። ወይም ሆን ብለህ አጣመኸዋል። እኛ ክልሉን ከሚመራው ፓርቲ የድሬዳዋ ጽ/ቤት በአግባቡ ፍቃድ ጠይቀን፣ ለሽንሌ ዞን አስተዳዳሪዎች አሳውቀን ከድሬዳዋ ፖሊስ ፈቃድ ጠይቀን ብቻ ሳይሆን ለቀረፃ የሚያስፈልግ መሣሪያ ተሰጥቶንና አጃቢ ፖሊስ ተመድቦልን ነው ሥራችንን በመሥራት ላይ የነበርነው።» ያለው መስፍን «ምንም ዓይነት ምርመራ» እንዳልተደረገባቸው ጽፏል። «ስህተት በመሠራቱም በአግባቡ ይቅርታ ተጠይቀን ነው የተለቀቅነው» ይላል መስፍን አክሎም «ከዛ በኋላም እስካሁን ድረስ ሥራችንን በስፍራው እየሠራን እንገኛለን» ብሏል። መስፍን በፌስቡክ ገጹ ለዳዊት መልስ የሰጠበት ጽሑፉን ፦ «አንድ እውነት ልንገርህ መቼም ቢሆን አገራችንን አደጋ ላይ የሚጥል አንዳችም ተግባር ላይ እንድንሳተፍ የሚያበረታታ ልብ የለንም። ከማንም የውጭ ድርጅት ጋርም ተባብረን አገራችን ላይ አንዶልትም። ኦጋዴን አካባቢም ዝር ብለን አናውቅም። ሽንሌ ከድሬዳዋ በ12 ኪ.ሜ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ነች። በስፍራው ቀረፃ ስናከናውን ደግሞ ይህ የመጀመሪያችን አይደለም። ስለሚዛናዊ ጋዜጠኝነት ደግሞ እኔ ላንተ ልነግርህ አልችልም። ሁሌም ቢሆን ለእውነት ዋጋ መስጠት ትልቅነት ነው» ሲል አጠቃሏል።

ይኽ በ«ዘመን» ድራማ ሠራተኞች ላይ ደረሰ የተባለውን እንግልት የሚገልጸዉን መረጃ በርካቶች በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ተቀባብለውታል።    

ጣና ሐይቅ ካለፉት አራት እና አምስት ዓመታት አንስቶ በመጤ አረም የመወረሩ ዜና በርካቶችን አስደንግጧል። አረሙ በአፋጣኝ ካልተወገደ በዓባይ ምንጭነቱ የሚታወቀው የጣና ሐይቅን ሊያደርቀው ይችላል ተብሏል። ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ዶይቸ ቬለ ከዘገበበት በኋላ የበለጠ ትኩረት ሊያገኝ እንደቻለ አንዳንድ አድማጮቻችን ገልጠውልናል። 

በዶይቸ ቬለ የፌስቡክ ገጽ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ደምስ አየለው የተባለ የገጻችን ተከታታይ፦ «በዓለም በዮኒስኮ በቅርስነት የተመዘገበው ጣና ሐይቅ እንቦጭ የተባለው አረም ወሮት አደጋ ላይ መሆኑን እያየን ነው። የሀገራችን ህዝብ ተቆርቋሪነቱን በተለያየ ማኅበራዊ ድረ ገፅ እየገለፀ ይገኛል» በማለት ይጀምርና መፍትኄ የሚለውንም ሐሳብ አስፍሯል። 

Wasserhyazinthen Lake Tana Äthiopien

ጣናን የወረረው «እምቦጭ» የተሰኘው መጤ አረም

«በኔ አስተሳሰብ ይህን አረም ለማጥፋት የክልሉ መንግሥት ከአቅሙ በላይ የሚሆን አይመስለኝም። የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ቢሮስ ዝምታን ለምን መረጠ? ዩኒስኮ ምን አለ? የሚመለከተው ሁሉ ይህን የንቃት ጥሪ ደወል ሊያሰማ ይገባል። ጩኸቱ ሰሚ እሰከሚያገኝ ይቀጥል» ሲል ሐሳቡን ቋጭቷል።

አረሙን ለማጥፋት ይረዳል በሚል የመፍትኄ ሐሳብ የሰጠን ሌላው የፌስቡክ ተከታታያችን የዑራኤል ልጅ ነኝ የሚል የፌስቡክ መጠሪያ አለው። እንዲህ ይላል፦ «ይህን አረም ለማጥፋት እንደ ሌሎች አገራዊ ጉዳዮች በቴሌ በኩል ገንዘብ የሚሠበሠብበት መንገድ ቢመቻች መልካም ነዉ። የሁሉም ኢትዮጵያውያን ችግር ነዉና።» 

ይሄነው ላቀው በበኩሉ፦ «ጣናን ሐይቅ ፌደራሉ መንግሥት አይመለከተውም እንዴ? ሕዳሴ ግድብ መለመኛ ሆኗል በጣናም ይለመና» ሲል ጣና ሐይቅ እንደ ሕዳሴው ግድብ በመንግሥት በኩል ትኩረት አልተሰጠዉም የሚል አስተያየቱን ሰጥቷል። አምባዬ ወልደ-ማሪያምም አረሙ ያሳሰበው ይመስላል። «ኧረ ያገሬ ሕዝብ እንነሳ እንነጋገርበት፤ ሌላ ሀገር አለን ወይ? ጣና ከሌለ ባሕር ዳር እሚባል ነገር ተረት ይሆናል» ብሏል። ታደሰ ወልደአብ በአጭር አረፍተ-ነገር ያሰፈረው መልእክቱ፦ «ይህን ያኽል ጊዜ ለምን ዝም ተባለ!!» ሲል ይነበባል። የአባ ሉማ አጭር መልእክትም «እንኳን ጣና አገሪቱም ተወራለች!!!» ይላል።

ገበሬዎች በሐይቁ ዙሪያ «እምቦጭ» የተባለውን አረም ሲነቅሉ የሚያሳዩ ፎቶዎችም በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ይገኛሉ። ከፎቶዉ ጋር አረሙን ለማጥፋት አስቸኳይ መፍትኄ እንደሚያሻው የሚጠቁሙ መልእክቶችም ይነበባሉ። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ
 

Audios and videos on the topic