የዘመነ-ቃዳፊ የመጨረሻ መጀመሪያ | ዓለም | DW | 28.02.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የዘመነ-ቃዳፊ የመጨረሻ መጀመሪያ

የሊቢያ ሶሻሊስት ጀምሕሪያ የመስከረም አንዱ ታላቅ አብዮት መሪ-የከንግዲሕ እርምጃቸዉ 6.5 ሚሊዮን ሕዝባቸዉን ማወክ፥ ተቃዋሚያቸዉን መግደል፥ ከአፍሪቃ አረተኛዋን ሰፊ፥ ሐብታም ሐገር ሊቢያን በጎሳ ጠርዝ የሚከፋፍል እንዳይሆን በርግጥ ያሰጋል።

default

ተቃዋሚዎች-ኔዘርላንድስ

 የሊቢያ ሕዝብ አመፅ ኮሎኔል ሙአመር ቃዛፊን አሽቀንጥሮ እንደ ጎረቤቶቹ በድል ማሳረጉ በርግጥ አላጠራጠረም።የሊቢያ ሕዝብ ከቱኒዚያና ከግብፅ ጎረቤቶቹ ዘር፥ባሕል እምነት ድንበር መጨቆን-በጨቋኞች ላይ ማመፅን የመጋራቱን ያክል በጎሰኝነት ስሜቱ፣በአሰፋፈር ታሪኩ ይለያል።ቃዛፊም ከቤን ዓሊ፣ ከሙባረክ ጋር የመመሳሰላቸዉን ያክል የሕዝባቸዉን ስሜት-ታሪክን፥ ሐብቱን ለመመዝበሪያ፣ ለመግደያነት በማዋል ይለያሉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን እንዳሉት ሊቢያ ላይ ጊዜ በጠፋ ቁጥር ብዙ ሕይወት ይጠፋል።ይሕ ነዉ፣የማያጠራጥረዉ ሕዝባዊ ድል በቃዛፊ ዉድቀት እስኪረጋገጥ የሚያስጨንቀዉ።የቃዛፊን ፖለቲካዊ ዳራ፣ የጭካኔቸዉን ልክ፣ ከሊቢያ ሁኔታ ጋር አጣቅሰን፣ የጭንቀቱን ሰበብ-ምክንያት ላፍታ እንቃኛለን አብራችሁኝ ቆዩ።
                

እንደ ጦር መኮንን የዉጊያ ስልት ማርቀቅ ማዉጣቱ ሆኖላቸዉ አያዉቅም።እንደ ተራ ወታደር ግን ደፋር ናቸዉ።እንደ ሐገር መሪ በመርሕ-ጥናት ላይ የተመሠረተ የአመራር ዘዴ፣ ራዕይ ብልሐትን-አያዉቁትም።አያዉቃቸዉምም።የሚሉ የሚያደርጉት በሌሎች ዘንድ ለሚሰጠዉ ፍቺ፣ በሐገር ሕዝባቸዉ፣ በራሳቸዉም ላይ የሚስከትለዉን ጥቅም-ጉዳትን የማሰብ፣ ማስተንተን-መጠንቀቅ  አያዉቁም።

እንደ ኮሚኒስት ካድሬዎች የሚጠሉትን እያወገዙ፣ የሚወዱትን እያወደሱ፣ ጣታቸን እየወዘወዙ፣ ክርናቸዉን-ቁልቁል እደፈቁ፣ ወይም ጭብጣቸዉን ሽቅብ እያጓኑ መፈከር፣ለረጅም ጊዜ መደስኮርን ግን በርጥ ተክነዉበታል።አርባ ሁለት ዘመን እንደኖሩበት ባለፈዉ ሰኞም-እንደ ጦር መኮንን ባልነደፉት ስልት እንደ ወታደር ሊዋጉ፣ እንደ መሪ ሳይጠነቀቁ፣ እንደ ተራ ካድሬ  
በሕዝባቸዉ ላይ ፈከሩ።
                  

በዛሬዉ መካከለኛዉ ምሥራቅ ባቢሎኖች ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኙትን ጭቃ ብጤ ነገር ቻይኖች ዉሐን እትንነዉ ጨዉ ለማምረቻነት፣ ጃፖኖች ለማቀጣጠያ፣ ፋርሶች ለመብራት ሲጠቀሙበት ዘመነ-ዘመናት አስቆጥራል።የጥንቱ ሰዉ ከጨዉ፣ ከሸክላ፣ እኩል እንኳን ያልቆጠረዉ ያ-ማዕድን ባቢሎኖች ባወቁት በአራት ሺኛዉ ዓመት ሥልጣኔ ለወለደዉ የሰዉ ልጅ ፍላጎት ወሳኝነቱ ሲረጋገጥ-የመጀመሪያ መገኛዉ መዛቂያዉም ሆነ።መካከለኛዉ ምሥራቅ።ነዳጅ ዘይት።

ከ1905 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጀምሮ በተደረገዉ ጥናትና ቁፋሮ ከሚወጣዉ ነዳጅ ዘይት የሚዛቀዉ ዶላር የዚያን በረሐማ ምድር ሕዝብን ጥንታዊ ሥልጣኔ እዉቀቱን፤ ለማዳበር፣ኑሮዉን ለማሻሻል፣ ከእልምና መስፋፋት ጀምሮ ባካባቢዉ የፀናዉን ፖለቲካዊ ሥርዓት ለመቀየር ከበቂ በላይ በሆነ ነበር።

ሐብቱን የሚቆጣጠሩት ገዢዎች ድንቁርና፣ ስግግብነት፣ የቅኝ ገዢዎች ሻጥር፣ ከወግ አጥባቂዉ የአረብ ነባር ባሕልና ሐይማኖት ጋር ተዳምሮ ጥቂት የደሳ፣ ድንኳን መንደሮችን ወደ ሕንፃ ከተማነት፣ ጥቂት ግመል ጎታቾችን ወደ ነጋዴነት ከመቀየር ባለፍ የአዲሱ ዘመን ትልቅ ሐብት የሕዝቡን አስተሳሰብ፣ ኑሮ፣ ፖለቲካዊ ሥርዓትን ብዙም ሳይለዉጥዉ ዓለም በሁለት ጦርነቶች ደቅቃ ሁለቴ ተለወጠች።

NO FLASH Libyen Tripolis Gaddafi Aufstand

«አጥር»

ከሁለተኛዉ የአለም ጦርነት ፍፃሜ እንዳዲስ የተለወጠዉ አለም አዲስ ከመሠረታት እስራኤል ጋር አረቦች የገጠሙት ጦርነት፣ የቅኝ አገዛዝ ፍፃሜ፣ የኮሚንስቶች መጠናከር በአረቦች ዘንድ ያሰረፀዉ አዲስ አስተሳሰብ ግን ለአብዛኞቹ የዚያ ምድር የእስከዚያ ዘመን ገዢዎች የፍፃሜቸዉ መጀመሪያ ነበር።አዲሱ አስተሳሰብ የሱዳን፤ የቱኒዚያ፣ የአልጄሪያ፣ የሞሮኮ፥ የየመን ሕዝብን የፀረ- ቅኝ አገዛዝ ትግልን ሲያጠናክር ኮሎኔል ገማል አብድናስር የመሯቸዉ የግብፅ መኮንኖች የንጉስ ፋሩቅን ዘዉዳዊ አገዛዝ አስወግደዉ ለስልጣን አበቃ።1952።

ናስር ካይሮ ላይ የለኮሱት የለዉጥ ማዕበል የኢራቅ፥ የሶሪያ እና የሊባኖስ ገዢዎችን ጠራርጎ የናስርን ፍልስፍና የሚያቀነቅኑ ጦር መኮንኖችን ከየአብያተ-መንግሥቱ ሲዶል፣ሱዳንን፣ ቱኒዚያን፣ አልጄሪያን፣ ሞሮኮንና ብጤዎቻቸዉን ነፃ አዉጥቶ የናስር መርሕ አድናቂዎች የየሐገራቸዉን ሥልጣን የሚቆጣጠሩበትን ሥልት እንዲያዉጠነጥኑ በር ከፈተ።

ናስር በ1967ቱ የአረብ እስራኤሎች ጦርነት በደረሰባቸዉ ሽንፈት የተደናገጡትን የአረብ መሪዎችን ለማበረታት በዉጤቱም የአረብ አንድነት ለማጠናከር ለሁለት አመት ያሕል ያደረጉት ጥረት መስመር እየያዘላቸዉ ነዉ።መስከረም አንድ-1969 ።የዚያን ቀን ካይሮ ላይ በጠሩት የግንባር መስመር ሐገራት ጉባኤ ላይም የዮርዳኖስ፣ የሶሪያ፣ የኢራቅ፣የሱዳንና የአልጄሪያና የሞሮኮ መሪዎች ተገኝተዋል።ናስር ተደስተዋል።

ናስር የሚሉትን ብለዉ፣ ዮርዳኖሱ ንጉስ ሁሴንን ማብራሪያ በጥሞና ሲያዳምጡ ረዳቸዉ አናጠባቸዉ ።ብጫቂ ወረቀት አቀበላቸዉ።«የንጉስ ኢድሪስ መንግሥት ተገለበጠ» ትለለች ወረቀቷ።«ገልባጮቹ ማናቸዉ?» ጠየቁ ናስር።«ብዙም አይታወቁም ጌታዬ።» አንሾካሾከ ረዳታቸዉ።« ከመግለጫቸዉ እንደተረዳነዉ ግን መርሐቸዉ ነፃነት፣ሶሻሊዝም እና አንድነት የሚል ነዉ።»

የሊቢያ መፈንቅለ-መንግሥት መሪዎች መርሕ-የሳቸዉ መርሕ ነዉ።ተደሰቱ ወይም የተደሰቱ መሰሉ።የሃያ-ሰባት አመቱን ሻምበል ግን ካይሮ ቀርቶ ቤንጋዚም ዉስጥ የሚያዉቅ አልነበረም።ንጉስ አስወግደዉ ስልጣን በያዙ በአርባኛ አመታቸዉ የአፍሪቃ ንጉሰ-ነገስትነኝ አሉ።«ነፃነት» ብለዉ ሥልጣን ይዘዉ የሕዝባቸዉ ነፃነት እንዳፈኑት።ዘንድሮ በአርባ ሁለተኛ አመቱ ነፃነት የጠየቀዉን ሕዝብ ጥይት ያዘንቡበት ያዙ።

ከቃዳፊ ቅጥረኞች ጥይት ያመለጠዉ፥ ከጋዳፊ አገዛዝ የተላቀቀዉ የሰሜን-ምሥራቃዊ ሊቢያ ሕዝብ በርግጥ ነፃ ወጣሁ እያለ ነዉ።«ሁሉንም ተቆጣጥረናል።ፖሊስ ጣቢያዉን፥ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን፥ መንገዶችን ሁሉንም እየተቆጣጠርን ነዉ።---ነፃነት፥ በስተመጨረሻዉ ነፃወጣን»

ሌላ ሥፍራ ግን በአስር ቀናት እድሜ በትንሽ ግምት ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዉ በቃዛፊ ደጋፊ-ታጣቂ፥ ቅጥረኞች ተገድሏል።ማስገደል-ማሸበር ለቃዛፊ እንግዳ አይደለም።የኖሩበት ነዉ።

ለቃዛፊ አመራር አገዛዛቸዉን የተቃወመ የትም ቢሆን መጥፋት አለበት።አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል በ1987 እንዳስታወቀዉ ከ1980 እስከ 1987 በነበረዉ ሰባት አመት ብቻ ቃዛፊ ዉጪ የተሰደዱ ሃያ-አምስት እዉቅ ተቃዋሚዎቻቸዉን እያሳደኑ አስገድለዋል።

ከዚያ በሕዋላ የተገደለዉን በትክክል የሚያዉቀዉ የለም።ቃዛፊ ዛሬም ያስገድላሉ።የናስርን መርሕ አንግበዉ እንደናስር ደም-ባልፈሰሰበት መፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን በያዙ ማግሥት ሊቢያ ከግብፅ ጋር መዋኸድ አለበት ብለዉ ግብፅ ከሚገኝ አንድ መስጊድ ዉስጥ እስከ መመሸግ ደርሰዉ ነበር።ከናስር ምክትል እና ከኋላ አልጋ ወራሻቸዉ ከአንዋር አሳዳት የበለጠ ናስርን የሚወድ ለመርሐቸዉ የሚገዛ ነበር ማለት በርግጥ ያሳስታል።

ሳዳት በ1981 በሰዉ እጅ መገደላቸዉን እንደሰሙ «ለፈፀሙት በደል» አሉ ቃዛፊ «ተገቢ ቅጣት» ነዉ።«በደል» ያሉት ሳዳት የአረብን ሕዝብ ፍላጎት ጥሰዋል ነዉ።ዛሬ አርባ ሁለት አመት የጨቆኑት ሕዝባቸዉ ነፃነቱን ሲጠይቃቸዉ ግን አሸባሪ አሉት።የሕዝቡን ጥያቄ ከዉጪ ሐይላት ወረራ እኩል ቆጥረዉት ለሊቢያ ነፃነት ከኢጣሊያ ቅኝ ገዢዎች ጋር የተፋለሙትን የነፃነት አርበኛ ዑመር ሙክታርን እያወደሱ ደጋፊያቸዉ በሰላማዊ ሰልፈኛዉ ላይ እንዲነሳ አዘዙ።
«ሊቢያን ለመታደግ፥ነዳጅ ዘይቷን ከዘረፋ፥ ማንነታችንን ከጥፋት፥ ነፃነትና፥ክብራችንን ለማዳን ተዋጉ።»

ጮኸት ፉከራቸዉ በርግጥ የጣር ነዉ።ያገዛዝ ሕልቅታቸዉ እስኪጠፋ ብዙ ሕይወት-አካል ለማጥፋት መዛታቸዉ ነዉ አሳሳቢዉ።ከአርብነት ይልቅ የበርበር ነገድነቱ ከሚጫጫነዉ ከአናሳዉ የቃዳፋ ጎሳ የሚወለዱት ቃዛፊ-ከፖሊቲካ እዉቀታቸዉ ማነስ በተጨማሪ የጎሳ የበታችነት ስሜትም እንደተጠናወታቸዉ ነዉ። ሥልጣን እንደያዙ የሐገሪቱን ርዕሠ-ከተማ አብዛሐዉ የቀድሞዉ ንጉስ ኢድሪስ ጎሳ ከሚኖርባት ከቤንጋዚ ወደ ትሪፖሊ ያዙሩት ከትላልቆቹ ጎሳዎች ሕዝብ የሚነሳባቸዉን ተቃዉሞ ሽሽት ነበር።

NO FLASH Libyen Tripolis Pro Gaddafi Anhänger

የትሪፖሊ «ደጋፊዎች»

ሕዝባዊ አመፅ በተነሳ በሰወስተኛዉ ቀን የቤንጋዚ ሕዝብ ከተማይቱን ከቃዛፊ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ ግን በቀላሉ ማላቀቅ በሕዝቡ ቋንቋ ነፃ ማዉጣት የቻለዉም የሰዉዬዉ የአገዛዝ ተፅኖ እዚያ አካባቢ ልል በመሆኑ ነዉ።ሕዝባዊ አመፅ ተቀጣጥሎ የጋዛፊ አገዛዝ በብዙዎቹ የሰሜን ምሥራቅ ሊቢያ ከተሞች ተወግዷል።በርካታ የሊቢያ ጦር አባላት፥ ባለሥልጣናትና ዲፕሎማቶች የቃዛፊን አገዛዝ እየከዱ የተቃዋሚዉን ጎራ እየተቀየጡ ነዉ።

ቃዳፊ የሚወለዱበት የአል-ቃዳፍ ጎሳ አባላት ግን አሁንም ለታላቁ አብዮት መሪ ታላቅ ድጋፋቸዉን እየሰጡ ነዉ።ኮሎኔሉ በተደጋጋሚ እንዳሉት ላአልጋ ወራሽነት ያጯቸዉ ልጃቸዉ ሰይፍ አል-ኢስልም ደግሞ በቀደም እንዛቱት ያለ ብዙ ደም መፋሰስ እንደ ቤን ዓሊ መሰደድ፥ ወይም እንደ ሙባረክ ሙባረክ ሥልጣን መልቀቅ የለም።
                   

«እቅድ ሀ፥ እቅድ ለ እና መ-አለን።እቅድ ሀ-ሊቢያ መኖርና መሞት ነዉ።እቅድ ለ-ሊቢያ መኖርና መሞት ነዉ።እቅድ መ-ሊቢያ መኖር እና መሞት ነዉ።»

መርሐቸዉ አንድነት ነፃነትና ሶሻሊዝም ነበር።ግን ቻድን ወርረዋል።ለዉደት የለመኗትን ግብፅን ለመዉጋት በ1977  ጦር አዝምተዉ ተሸንፈዋል።የዩጋንዳዉን አምባገነን መሪ ኢዲ አሚንን ደግፎ ታንዛኒያን እንዲወጋ ያዘመቱት ጦር ስድስት መቶ ወታደሮቹን እዚያዉ ቀብሯል።ከኢትዮጵያ-እስከ ሶማሊያ፥ከሱዳን እስከ ኮንጎ፥ ከኒካራጓ-እስከ ፊሊፒንስ የሚገኙ ሐገራትን ባደቀቀዉ የመገጠል ወይም የርስ በርስ ጦርነት እጃቸዉን ዶለዋል።ከፍልስጤም ነፃ አዉጪዎች እኩል፥ የሰሜን አየርላንድ፥ የባስክ፥ የሎችንም ተገንጣይ ሐይላት አስታጥቀዋል።
               
ከ1980 አጋማሽ ጀምሮ በርሊን ዳንስ ቤት፥ ሎከርቢና ኒጀርን ሰማይ ላይ ብዙ ሕይወት ባጠፋዉ የሽብር ጥቃት ሰበብ ዩናይትድ ስቴትስ የፈፀመችባቸዉ ድብደባ፥ የግድያ ሙከራ ተረስቶ፥ 3.66 ቢሊዮን ዶላር ከፍለዉ፥ የኑክሌር መርሐ-ግብራቸዉን መነቃቅረዉ በአሸባሪነት መወንጀል፥መቀጣቱ ተፍቆላቸዉ የምዕራቦችን ልብ እንዳገኙ ብራስልስ መጥተዉ ነበር።

ለአዉሮጳ መሪዎች ባደረጉት ንግግር በርካታ ሐገራት ባወደመና በከፋፈለዉ ዉጊያ እጃቸዉን ያስገቡበትን ምክንያት «ታሪካዊ ሐላፊነት» አሉት።«ሐላፊነታችንን ተወጥተናል።የነፃነት ተዋጊዎች ነፃነታቸዉን ያገኙ ዘንድ አሰልጥነናል።ይሕ ታሪካዊ ሐላፊነታችን ነዉ ብለን እናምናለን።»

Libyen / Gaddafi / Kairo

ተቃዋሚዎች-ካይሮ

የሊቢያ ሶሻሊስት ጀምሕሪያ የመስከረም አንዱ ታላቅ አብዮት መሪ-የከንግዲሕ እርምጃቸዉ 6.5 ሚሊዮን ሕዝባቸዉን ማወክ፥ ተቃዋሚያቸዉን መግደል፥ ከአፍሪቃ አረተኛዋን ሰፊ፥ ሐብታም ሐገር ሊቢያን በጎሳ ጠርዝ የሚከፋፍል እንዳይሆን በርግጥ ያሰጋል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዉግዘት፥ ቅጣትን የሚሰሙበት፥ የሕዝባቸዉን አመፅ የሚያስተናግዱበት ብልጠት፥ እዉቀት፥ ስብዕናዉም ያላቸዉ አይምስልም።ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን። 

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ