የዘመቻ-ሙሽታራክ ድል ደስታ እና የሽብር እልቂቱ ሰቀቀን | ዓለም | DW | 15.03.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የዘመቻ-ሙሽታራክ ድል ደስታ እና የሽብር እልቂቱ ሰቀቀን

የጦር፥ ዲፕሎማሲ ድል፥ የምርኮ ገድል ብሥራት፥የሽብር፥ እልቂት የደም ጎርፍ መዓት-ነዉ የሁለቱ ተጎራባች ሐገራት የቅርብ አመታት ወግ

default

ሔልማድ-ዘመቻዉ

15 03 10

በአፍቃኖቹ ትልቅ ጎሳ ቋንቋ-ፓሽቱንኛ የተሰየመዉ፣ከትልቁ ጎሳ ትላልቅ መኖሪያ ግዛቶች በአንዱ-ሔልማንድ፣ የመሸገዉን ደፈጣ ተዋጊ ቡድን-ታሊባንን ለመደምሰስ ያለመዉ ትልቅ ዘመቻ-ሙሽታራክ (አንድነት ነዉ ፍቺዉ) ወር ደፈነ።ቅዳሜ።የታሊባን የጦር አዛዥ ፓኪስታን ዉስጥ በመያዙ ዜና ብሥራት ታጅቦ የተጀመረዉ ትልቅ ዘመቻ የወር-ድል ገድል በርግጥ ትልቅ ነዉ።ፖኪስታንም፣ አፍቃኒስታንም የትልቁ ምርኮ፣የትልቁን-ድል ገድል አንደኛ ወር በሽብር፣ ግድያ ፅልመት መዘከራቸዉ እንጂ ሰቀቀኑ።የምርኮ፣ ዘመቻዉ ድል ደስታ እና የሽብር እልቂቱ ሰቀቀን ተቃርኖ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁን ቆዩ።

አሜሪካ መራሹ ጦር የታሊባን መንግሥትን ከሥልጣን ካስወገደ ወዲሕ የመጀመሪያዉ ትልቅ ፀረ-ታሊባን ዉጊያ-ዘመቻ ሙሽታራክ በተከፈተ በሳልስቱ የታሉባኑ ምክትል መሪና የጦር አዛዥ ሙላሕ አብዱል ጋኒ ባራዳር ካራቺ-ፓኪስታን ዉስጥ መማረካቸዉ ይፋ ሆነ።የባራዳር የመያዝ-ዜና በዘመቻ ሙሽታራክ ለሚሳተፉት አስራ-አምስት ሺሕ ወታደሮች ታላቅ መንፈሳዊ ብርታት፥ ለታሊባን ደግሞ በአፍቃኒስታን የቀድሞዉ የፓኪስታን አምባሳደር ሩስታም ሸሕ መሐመድ እንዳሉት ቆጥቋጭ በትር ነበር።

«ለታሊባን በጣም አሳማሚ ምት ነዉ።ሁለተኛ ሰዉ ነበር፥ ከፍተኛ ልምድ ያለዉ አዋጊም ነበር።የሰዉዬዉ መያዝ በታሊባን ንቅናቄ ዉስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል።»

በምርኮ-ድል-ብሥራት የታጀመዉ ታላቅ ዘመቻ የወር ዉጤቱም በርግጥ ድል ነበር።ሕብረ-ብሔሩ ጦር ከአንድ መቶ የሚበልጡ የታሊባን ሸማቂዎችን ገድሏል።ከአለም ከፍተኛዉ ኦፒየም የሚመረትባት የሄልማድ ግዛትን ተቆጣጥሯ።ታሊባን ከግዛቲቱ ዋና ከተማ ከማርጃሕ አካባቢ ከሚሰበስበዉ ኦፕየም ብቻ በወር ከሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ ያገኝ ነበር።ከሠረ።

ታላቁ ድል የብሪታንያዉን ጠቅላይ ሚንስትር ጎርደን ብራዉንን ከለንደን ማርጃሕ፥የዩናይትድ ስቴትሱን መከላከያ ሚንስትር ሮበርት ጌትስን ከዋሽንግተን ካቡል አድርሶ መልሷል።ባለፈዉ ሳምንት የዛሬን ̎እለት አፍቃኒስታንን የጎበኙት ጌትስ እንዳሉት የዘመቻ ሙሽታራክ ድል-የሚለከዉ ታሊባን ባጣዉ የሰዉ፥ የገንዘብ፥ እና የግዛት ብዛት ብቻ አይደለም።በሔልማድ ግዛት ልማት እንጂ።

«የሥራ እድል የመፍጠር፥የእርሻ መስኩን የማስፋፋት መርሐ-ግብሮች ተዘርግተዋል።መደብሮችና ትምሕር ቤቶች እየተከፈቱ ነዉ።ከሁሉም በላይ የተፈናቀሉ ቤተሰቦች ወደየቀያቸዉ እየተመለሱ ነዉ።»

ላለፉት ስምንት አመታት የካቡል ከንቲባ በሚል ቅፅል የሚታሙት ሐሚድ ካርዛይም እንደ ሐገር መሪ ያን አካባቢ ለማየት ቻሉ።ሕዝቡንም-ሰማሁ፥ ሰማኝም አሉ ካርዛይ።-እድሜ ለዘመቻ ሙሽታራክ

«ከሕዝቡ ጋር ሐሳብ ተለዋዉጠናል።እነሱን ሰምቻቸዋለሁ።እኔንም ሰምተዉኛል።አንዳድ በጣም ተገቢ የሆነ ቅሬታ አላቸዉ።ተረስተናል የሚል ስሜት አላቸዉ።በብዙ መልኩ ይሕ እዉነት ነዉ።እንዲሕ አይነቱ ሥሜት መወገድ አለበት።ለችግራቸዉ መፍትሔ ልሰጥ ይገባል።እስካሁን መፍትሔ አልሰጠንም።ደሕነ

Selbstmordanschlägen in Kandahar

ካንዳሐር-ሽብሩ

ታቸዉን ማስከበር አለብን።»

የአሜሪካዉ መከላከያ ሚንስትር እንዳሉት ዘመቻ ሙሽታራክ የታሊባን ደፈጣ ተዋጊዎች ለማጥፋት ከሚደረገዉ ዉጊያ አንዱ እና የመጀመሪያዉ እንጂ ሁሉና የመጨረሻዉ አይደለም።አፍቃኒስታን የሰፈረዉ የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ጦር (NATO) አዛዥ አሜሪካዊዉ ጄኔራል ስታንሌይ ማክ ክርይስታል ሁለተኛዉን መጠነ ሰፊ ዘመቻ ለመጀመር እቅዳቸዉን ነድፈዉ ማጠናቀቃቸዉን አልሸሸጉም።የሁለተኛዉ ዘመቻ ኢላማ ካንዳሐር።

ቅዳሜ ግን ካንዳሐር ላይ በርግጥ ታሊባን ቀደመ።በጦር አዛዡ መያዝ፥ በመቶ ተዋጊዎቹ መገደል፥ በሔልማድ ግዛት ሽንት ተፍረክርኳል የተባለዉ ታሊባን ደቡባዊ አፍቃኒስታን ባጠመዳቸዉ ቦምቦች ቅዳሜ ዉሎዉን ስድስት ሰዎች ገደለ።ማምሻዉን ደግሞ ወደ ካንዳሐር ያዘመታቸዉ አጥፍቶ ጠፊዎች ትልቂቱን ከተማ አሸበሩ።ሰላሳ-አምስት ሰዉ ገደሉ።ከሟቾቹ አስራ-ሰወስቱ ፖሊሶች ነበሩ።የተቀረዉ ሰላማዊ ሰዉ።

የአሸባሪ-ገዳዮቹ አላማ ካንዳሐር ወሕኒ የታሰሩ የታሊባን ደፈጣ ተዋጊዎችን ማስፈታት ነበር።ይሕ በርግጥ አልተሳካም።ካርዛይ ደሕነቱን ልንጠብቅለት ይገባል ያሉት ሠላማዊ ሰዉ ግን በርግጥ ከዘመቻ ሙሽታራክ በፊት እንደኖረበት ተገደለ። ቆሰለ።ቀሪዉ ተሸበረ።ዛሬ ደግሞ ታሊባኖች ባጠመዱት ቦምብ አምስት ሰዉ ተገደለ።

ከአፍቃኒስታንዋ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ካንዳሐር፥ ከሰፊዋ ግዛት ሔልማድ በስተደቡብ ለመሸጉት ለፓኪስታን ታሊበኖች አርብ ተረኛዋ የሐገሪቱ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ነበረች-ላሆር።

«አጥፍቶ ጠፊዎቹ ወደ አካባቢዉ የተጓዙት በእግራቸዉ ነበር።ለማኝነት ያሕል የሁለቱን አጥፍቶ ጠፊዎች አስከሬን አግኝተናል።»

Pakistan General Ashfaq Pervaiz mit soldaten im Swat Tal

ስዋት የዘመተዉ የፓኪስታን ጦር

አሉ የላሆሩ ፖሊስ።አሸባሪዎቹ-ሥልሳ ሰዉ፥ አጥፍተዉ፥ ከአንድ መቶ በላይ አቁስለዉ ነዉ-የጠፉት።ቅዳሜ ደግሞ ተረኛዋ የፓኪስታን ጦር በታሊባኖች ላይ መጠነሰፊ ጥቃት-የከፈተ፥ ትልቅ ድልም የተቀዳጀባት የስዋት ሸለቆ ትልቅ ከተማ ነበረች።ሚንጎራ።አንድ አጥፍቶ ጠፊ-አስራ አራት ሰዉ ገድሎ፥ ሞተባት።
--------------------------------------------

ከአፍቃኒስታን ጋር ሰፊ-ድንበር ትጋራለች።እንደ-ልዩ ወሰንተኛ የተመሳሳይ ጎሳ ተወላጅ፣ ቋንቋ ወግ ባሕል፥ ሐይማኖት ተጋሪ ሕዝብ ታኖራለች።ፓኪስታን።የኢስላማባድ መሪዎች ከሁለቱ ሐገራት ቅርበት ተመሳስሎ አንድነቱ ጋር ሐገራቸዉ በጦር፣ በምጣኔ ሐብት፣ በእዉቀት አቅሟ ላቅ በማለቷ ብዙ ጊዜ የካቡልን ፖለቲካ አንድም ለራሳቸዉ አለያም ለምዕራብ ወዳጆቾ በሚመች መንገድ ያልዘወሩበት ዘመን አልነበረም።

የኢስላማባድ መሪዎች በለንደን ዋሽግተኖች ድጋፍና ይሁንታ አንዳዴም ትዕዛዝ ንጉስ መሐመድ ዛሒር በዙፋናቸዉ የቆዩትን ያሕል እንዲቆዩ የደገፏቸዉን ያሕል-አማቻቸዉ መሐመድ ዳዉድ ከሐን ንጉሱን እንዲያስወግዱም ዙሪያ መለስ ድጋፍ ሰጥተዋቸዋል።ካሐንን ካቡል ቤተ መንግ-መንግሥት እንደ ዶሎ ሁሉ፣ ኑር መሐመድ ታሪኪ፣ካሕንን፣መሐመድ ናጂ ቡላሕ ታሪኪን እያጠፉ ሥልጣን ሲይዙ ባንድ ወይም በሌላ መልኩ የኢስላማዶች እጅ ነበረበት።

የናጂቡላሕን ኮሚንስታዊ መንግሥት ለመደገፍ የዘመተዉን የሶቬት ሕብረትን ጦርን ከአፍቃኒስታን ለማስወጣት ዩናይትድ ስቴትስ፣ ሌሎች ምዕራባዉያን ሐገራት እና የአረብ ወዳጆቻቸዉ ሙጃሒዲያንን ከመላዉ ሙስሊም አለም መመልመል ማስታጠቃቸዉ በርግጥ አያጠያይቅም።ሙጃሒዱን ያሰለጠነች ፣ስደተኛዉን ከየመጠለያ ጣቢያዉ፣ ደረሳዉን ከየመድረሳዉ እየለቀመች ታሊባንን ያደራጀች፣ያዘመተች ለድል-ሥልጣንም ያበቃችዉ ግን በርግጥ ፓኪስታን ነች።

አሜሪካ መራሹ ጦር የታሊባን መንግሥትን ለመስወገድ ሲዘምት-የኢስላማድ ፖለቲከኞች የቀድሞ ወዳጆቻዉን ለማስወገድ ሠልፋቸዉን ከሐያላኑ ጎን ማሰመሩ በርግጥ አልገደዳቸዉም።ሕንድ የተማሩ-የኖሩት ኻሚድ ካርዛይ ከኢስላማባድ ይልቅ ደልሒን-ማማተራቸዉ፥በኢስላማድ በኩል ይብስ በቀጥታ ዋሽንግተንን ማዘዉተራቸዉ፥አሜሪካኖች ኢስላማዶችን በጥርጣሬ ማየታቸዉ ፔርቬዝ ሙሸረፍ፣ ነዋዝ ሸሪፍ፣ ቤናዚር ቡቶን ይሁን ናሲፍ አሊ ሳልዳሪን የሚያስቆጣ ደግሞ ካጣብቂኝ የሚከትም ነበር።

የኢስላማድ መሪዎች ባንድ በኩል ካርዛይን ለመበቀል-ወይም የበላይነታቸዉን ለማሳየት፣ በሌላ በኩል ለዋሽግተን-ለንደን ታሞችነታቸዉን ለማረጋገጥ የፓኪስታን ታሊባንን በጦር ሐይል ጡንቻ፥ የአፍቃኒስታን ታሊባንን በሥለላ መረብ ከማበርከክ ሌላ ምርጫ አልነበራቸዉም።አደረጉት።

ስዋት ሸለቆ የመሸገዉን የታሊባን ሐይል መቱ።የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ሰዉ አልባ አዉሮፕላን ግዛታቸዉን ዘልቆ የሸማቂዉን ቡድን መሪዎች እንዲገድል ፈቀዱ።በርካታ የአፍቃኒስታን ታሊባን አባላትን እየለቀሙ አሰሩ።ሙላሕ አብዱል ጋኒ ባራዳር ትልቁ ነበሩ።የስዋት ሸለቆዉ ድል፥ የካራቺ ላሆሩ ምርኮ የፓኪስን ፖለቲከኞች ለሐያል ወዳጆቻቸዉ ታማኝነታቸዉን ለማረጋገጥ ትልቅ ምስክር ነዉ።

የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ሮበርት ጊብስ ያኔ እንዳሉት ደግሞ በዲፕሎማሲዉ ቋንቋ የጋራ ሥራ ታላቅ ድል ነበር።

«ይሕ ሰዉ በመንቀሳቀስ ላይ ያለዉ የአፍቃኒስታን ታሊባን ሁለተኛ ሰዉ ነዉ ብዬ አምናለሁ።እና (መያዙ) በአካባቢዉ ለምናዉ የጋራ ጥረት ታላቅ ድል ነዉ።»

Pakistan Lahore Bombenanschlag

ሽብሩ-ላሆር

የዘመቻ-ሙሽታራክ ድል፥ የካራቺዉ ምርኮ ገድል አንደኛ ወር ቅዳሜ ሊዘከር አንድ ቀን ሲቀረዉ አርብ የአፍቃኒስታኑ ፕሬዝዳት ሐሚድ ካርዛይ ኢስላማድን ጎብኝዋል።ጉብኝቱ ቢያንስ ላሁኑ ካቡሎች ከኢስላማዶች አለማራቃቸዉን አመልካች፥ለፓኪስታን መሪዎች እንደ ሁለተኛ ድል የሚቆጠር ነዉ።የሁለቱን ሐገራት ልምድ ግን አልቀየረዉም።የጦር፥ ዲፕሎማሲ ድል፥ የምርኮ ገድል ብሥራት፥የሽብር፥ እልቂት የደም ጎርፍ መዓት-ነዉ የሁለቱ ተጎራባች ሐገራት የቅርብ አመታት ወግ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

dw,Agenturen

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠAudios and videos on the topic