1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ በ2015 ከዕቃዎች የወጪ ንግድ ያገኘችው የውጭ ምንዛሪ ነዳጅ ከገዛችበት ያነሰ ነው

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ኅዳር 26 2016

የዋጋ ንረት እና የውጭ ምንዛሪ እጥረት የበረታባት ኢትዮጵያ ከአበዳሪዎቿ የሁለት ዓመት የዕዳ ክፍያ እፎይታ አግኝታለች። ሥምምነቱ ለኢትዮጵያ 1.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያድን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ ተናግረዋል። ሀገሪቱ ባለፈው ዓመት ለነዳጅ መግዣ ብቻ ያወጣችው 4 .1 ቢሊዮን ዶላር ከዕቃዎች የወጪ ንግድ ካገኘችው የበለጠ ነው

https://p.dw.com/p/4Zq0M
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ
ኢትዮጵያ ከአበዳሪዎቿ ያገኘችው የዕዳ ክፍያ እፎይታ መንግሥትን ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያድን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ ተናግረዋል። ምስል CC BY 2.0/U.S. Institute of Peace

የኢትዮጵያ የዕዳ ክፍያ እፎይታ ከIMF ጋር በሚኖራት ሥምምነት እጣ ፈንታ ላይ የተንጠለጠለ ነው

ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የአገልግሎት ንግድን ሳይጨምር ለዓለም ገበያ ካቀረበቻቸው ሸቀጦች ያገኘችው የውጭ ምንዛሪ ነዳጅ ከሸመተችበት ያነሰ ሆኗል። የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምኅረቱ ሪፖርት እንደሚያሳየው በዓመቱ 4.1 ቢሊዮን ዶላር ነዳጅ ለመግዛት ያወጣችው ኢትዮጵያ ከዕቃዎች የወጪ ንግድ ያገኘችው ገቢ ግን 3.6 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነበር።

አቶ ማሞ “4.1 ቢሊዮን ዶላር ለነዳጅ መክፈል ማለት አጠቃላይ የኢትዮጵያ ኤክስፖርት፤ በተለይ የዕቃዎች ኤክስፖርት በአመዛኙ ነዳጅ ለመግዛት እንደሚውል ማየት ይቻላል” ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ማሞ ባለፈው ሣምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡት ሪፖርት እንደጠቀሱት መንግሥታቸው በ2015 ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያገኘው ከአገልግሎት ንግድ ዘርፍ ነው። አቶ ማሞ ከአገልግሎት ንግድ ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ 7.1 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን ተናግረዋል።

ከግለሰቦች የሚላክ ሐዋላ ለኢትዮጵያ ጠቀም ያለ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ ከግለሰቦች ሐዋላ 4.6 ቢሊዮን ዶላር፣ ከዕቃዎች የወጪ ንግድ 3.6 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች። 

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ከውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ-ንዋይ 3.4 ቢሊዮን ዶላር፣ ከግል ድርጅቶች ሐዋላ 2.2 ቢሊዮን ዶላር፣ ከውጭ ዕርዳታ 1.1 ቢሊዮን ዶላር፣ ከመንግሥት ብድር 900 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተናግረዋል። 

የብሔራዊ ባንክ ገዥ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ዓመት 17.1 ቢሊዮን ዶላር ለገቢ ንግድ፤ 2 ቢሊዮን ዶላር ለአፈር ማዳበሪያ መግዣ ወጪ ማድረጉን ተናግረዋል። አቶ ማሞ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት በሰጡት ማብራሪያ ከ2015 መደበኛ እና ካፒታል በጀት ከፍተኛውን ድርሻ ለወሰደው የዕዳ ክፍያ መንግሥታቸው ምን ያክል የውጭ ምንዛሪ እንዳወጣ ያሉት ነገር የለም።

በ2014 በጀት ዓመት ብቻ 1.7 ቢሊዮን ዶላር ብድር የከፈለው የኢትዮጵያ መንግሥት የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ በፍጥነት ይጠናቀቃል የሚል ተስፋ ነበረው። የውጭ ምንዛሪ እጥረት ክፉኛ የሚፈትነው መንግሥት ከአበዳሪ ሀገሮች የዕዳ ክፍያ እፎይታ ማግኘቱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ለቋሚ ኮሚቴው ያበሰሩት አዎንታዊ ዜና ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት ሦስት ወራት ከአበዳሪዎች ጋር ባደረገው ውይይት “ጊዜያዊ የዕዳ ክፍያ እፎይታ ሥምምነት” ላይ መድረሱን የገለጹት አቶ ማሞ “ይኸም በመሆኑ በየዓመቱ ለዕዳ ልንከፍል የሚገባውን ወደ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ለመቀነስ አስችሎናል” ብለዋል።

ለኢትዮጵያ የዕዳ ክፍያ እፎይታ የሚሰጠው ሥምምነት በፈረንሳይ እና ቻይና ተባባሪ ሊቀ-መንበርነት በሚመራው የአበዳሪዎች ኮሚቴ አቀናጅነት የተደረሰ እንደሆነ 22 አበዳሪ አባል ሀገራት ያሉት ፓሪስ ክለብ ባለፈው ዓርብ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በመግለጫው መሠረት የኦፊሴያል አበዳሪዎች ኮሚቴ እና የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ከሥምምነት የደረሱት ሕዳር 13 ቀን 2016 ነው።

የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ 28 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ እንዳለባት የገንዘብ ሚኒስቴር ሰነድ ያሳያልምስል Eshete Bekele/DW

ውሳኔው በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ከተደረሰው ተመሣሣይ ሥምምነት ጋር የሚጣጣም እንደሆነ ፓሪስ ክለብ በመግለጫው ጠቁሟል። ኢትዮጵያ ካለባት 28 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ 14 ቢሊዮን በማበደር ቀዳሚ የሆነችው ቻይና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የዕዳ ክፍያ እፎይታ ሰጥታለች። ባለፈው ሣምንት ይፋ የሆነው የዕዳ ክፍያ እፎይታ ቻይናን እንደማይጨምር ፓሪስ ክለብ አስታውቋል።

ይኸ ሥምምነት ከታኅሳስ 2015 እስከ ታኅሳስ 22 ቀን 2017 ባሉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ መክፈል የሚጠበቅባትን ዕዳ እና ወለድ የተመለከተ ነው። በፓሪስ ክለብ መግለጫ መሠረት በሥምምነቱ የታገደውን ዕዳ የእፎይታ ጊዜው ካበቃ በኋላ ኢትዮጵያ ከጎርጎሮሳዊው 2027 እስከ 2029 ባሉት ዓመታት እንድትከፍል ይጠበቃል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምኅረቱ ይኸ የዕዳ ክፍያ እፎይታ “የውጭ ምንዛሪ አስተዳደራችንን የበለጠ እንደሚያሻሽለው ይጠበቃል” ሲሉ ተናግረዋል። በጉዳዩ ላይ የተደረገ ውይይት ከኢትዮጵያ የዕዳ እና የወለድ ክፍያ የሚጠብቁ ሀገራት የተሳተፉበት ነው።

ከፓሪስ ክለብ አባል ሀገራት መካከል የኦስትሪያ፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ እስራኤል፣ ጣልያን፣ ኮሪያ፣ ስዊድን፣ ደቡብ አፍሪካ እና ስዊትዘርላንድ ተወካዮች ተሳትፈዋል። ከዚህ በተጨማሪ የፓሪስ ክለብ አባል ያልሆኑት ቻይና፣ ሕንድ፣ ኩዌት፣ ፖላንድ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ቱርክ ተሳትፈውበታል።

የአውሮፓ ኅብረት የዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ዩታ ኡርፒላይነን እና የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በአዲስ አበባ
ባለፈው ጥቅምት ወር የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ሀገሪቱ “ያለባትን የዕዳ ጫና ለመቀነስ” ከቻይና የፋይናንስ ተቋማት እንዲደራደር መወሰኑን አቶ አሕመድ ሽዴ ተናግረዋል።ምስል European Union | CC BY 4.0

የኢትዮጵያ መንግሥት በመጪው ሣምንት ለዩሮ ቦንድ ባለቤቶች 33 ሚሊዮን ዶላር መክፈል ይጠበቅበታል። ይኸ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣን ላይ ሳሉ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ የሸጠችውን የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ለገዙ የግል አበዳሪዎች የሚከፈል ነው። ኢትዮጵያ በሕዳር 2007 በዓለም ገበያ የሸጠችው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ በሚቀጥለው ዓመት ታኅሳስ ወር ይጎመራል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ግን ከግል አበዳሪዎችም የዕዳ ክፍያ ማሻሻያ ይፈልጋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ቦንዱን ከገዙ የግል አበዳሪዎች ጋር በአከፋፈል ላይ ያተኮረ ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ “ከዩሮ ቦንድ አበዳሪዎቻችን ጋርም ውይይት ጀምረናል። ገና አልጨረስንም። የእነሱም እንደሌላው የዕዳ አይነት መፍትሔ ይኖረዋል ማለት ነው” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከአበዳሪዎቿ ጋር የደረሰችበት የክፍያ እፎይታ የሚሰጥ ሥምምነት በቡድን 20 ማዕቀፍ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ እስኪሰራ ድረስ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለሚፈትነው ኤኮኖሚ “በጊዜ የተገደበ እፎይታ” የሚሰጥ ነው። ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ ሁለተኛ ምዕራፍ በጠየቀችው የድጋፍ መርሐ-ግብር ላይ ከሥምምነት ሲደረስ በቡድን 20 ማዕቀፍ የተጀመረው የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ውይይት እንደሚፋጠን የፓሪስ ክለብ ገልጿል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ከአራት ወራት በኋላ ማለትም በመጋቢት መገባደጃ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ጋር በጉዳዩ ላይ ከሥምምነት ካልደረሰ ግን የዕዳ ክፍያ እፎይታው “ዋጋ ቢስ” እንደሚሆን ፓሪስ ክለብ አስታውቋል።

በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር በሎስ አንጀለስ ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ተወካዮች ጋር
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር “ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር ያለን ግንኙነት በዋናነት የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ አለመውደቁን ለማረጋገጥ የሚደረግ ጥረት ላይ ያተኮረ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ምስል Maebel Gebremedhin

በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከፍ ያለ ድምጽ ያላት አሜሪካ በፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነት አተገባበር ረገድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ላይ ማሳደር ለምትሻው ጫና በኢትዮጵያ እና በተቋሙ መካከል የሚደረገውን ውይይት መጠቀሚያ የማድረግ ፍላጎት እንደሌላት አምባሳደር ማይክ ሐመር ባለፈው ሣምንት ፍንጭ ሰጥተዋል።

በአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ፊት ቀርበው ማብራሪያ የሰጡት በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር ዋናው ትኩረት የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ ከውድቀት ለማዳን የሚደረገው ጥረት እንደሆነ አስረድተዋል።

“ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር ያለን ግንኙነት በዋናነት የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ አለመውደቁን ለማረጋገጥ የሚደረግ ጥረት ላይ ያተኮረ ነው” ያሉት አምባሳደር ማይክ ሐመር የኤኮኖሚ ውድቀት “የአሜሪካም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት አይደለም” ሲሉ ተደምጠዋል።

ልዩ ልዑኩ “ሁሉንም ኢትዮጵያውያን የሚጠቅሙ የኤኮኖሚ ማሻሻያዎች ለማምጣት እና ተቋማትን ወደ ግል ለማዛወር በሚደረገው ጥረት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር ያለን ግንኙነት ጠቃሚ ነው” ሲሉ በአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ እና ማብራሪያቸውን ለታደሙ የመንግሥታቸውን አቋም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ በበርሊን የኢትዮጵያ ጀርመን የንግድ እና የመዋዕለ ንዋይ ፎረም
በቡድን 20 ማዕቀፍ በኩል ኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ለማድረግ የጀመረችው ሒደት በጎርጎሮሳዊው 2024 የመጀመሪያ መንፈቅ ይጠናቀቃል የሚል ተስፋ እንዳላቸው የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል Eshete Bekele/DW

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ለምጣኔ ሐብታዊ ማሻሻያ በጠየቀው ብድር ላይ በተደጋጋሚ ውይይቶች ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የምትሻው አዲስ መርሐ ግብር “የልማት አጋሮች ግልጽ ቁርጠኝነት እና የአበዳሪዎችን የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ” እንደሚፈልግ መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው ተቋም አስታውቋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከአበዳሪዎች ካገኘው የዕዳ እፎይታ በኋላ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ቃል አቀባይ በመጪው ጥር ወር አካባቢ የተቋማቸው ባለሙያዎች ለተጨማሪ ውይይት ወደ አዲስ አበባ ሊያቀኑ እንደሚችሉ ለሬውተርስ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ለማድረግ ጥያቄ ያቀረበው በሐምሌ 2013 ነው። የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ ይኸ ሒደት በጎርጎሮሳዊው 2024 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ይጠናቀል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ