የዓድዋ ጉዞ 5 ገጠመኞች   | ባህል | DW | 08.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የዓድዋ ጉዞ 5 ገጠመኞች  

የዓድዋ ጉዞ 5 ገጠመኞች  

የዘንድሮ ጉዞ የተጀመረዉ ጥር 8 ቀን ነዉ። የ 46 ቀናት ጉዞአችን በርካታ መንደሮችን የገጠር ቦታዎችን እያቆራረጥን ነዉ ያለፍነዉ። ከአዲስ አበባ ከወጣን በኋላ በአራተኛዉ ቀን ማለትም ደብረ ብርኃን ስንደርስ ዋናዉን መስመር ትተን ወደ ግራ አንጎለላ የሚባል ቦታ ገብተን አድረን ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:02

«አጼ ምንሊክን በዜማ አወድሰናል»

ክቡራን የጉዞ ዓድዋ ቤተሰቦች ለሳምንታት ከፌስቡክ መንደራችን ጠፍተን ከርመን እነሆ ዛሬ የግንኙነት ብርሃን አላማጣ ከተማ ስንደርስ አግኝተናል። መረጃችን በመጥፋቱ ምክንያት በርካታ ወገኖቻችን ስጋት አድሮባቸው እንደነበር ሰምተናል። እኛ ግን በደጉ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍቅር እና የላቀ መስተንግዶ ከአዲስ አበባ በተነሳን በ24ኛ ቀናችን በደብረ ብርሃን፤ በኮምቦልቻ፤ በደሴ፤ በሐይቅ፤ በውጫሌ፤ በመርሳ፤ በወልዲያና በቆቦ አልፈን ዛሬ ምሽቱን አላማጣ ከተማ ገብተናል። ከአንጎለላ በገዛ ፍቃዷ የተቀላቀለችን ተአምረኛዋ ውሻም ጉዞውን እንደቀጠለች ነው።

ከፊሉ መንገዱ በስጋትና በውጥረት የተሞላ ቢሆንም የህዝብ ፍቅር ተላብሰን የዓድዋን ድል እየዘከርን ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና ሰራዊታቸው የስራውን ታላቅ ታሪክ እየመሰከርን ያለምንም ችግር ጉዟችንን ቀጥለናል፤  ይላል፤ የዘንድሮዉ የጉዞ ዓድዋ አምስት ተጓዦች ማስታወሻ። ጥር ስምንት ቀን ከአዲስ አበባ የተነሱት 25 ቱ የዘንድሮ የጎዞ ዓድዋ ተጓዦች በኢንተርኔት መስመር መቆራረጥና ብሎም አልፎ አልፎ ጭርሶ መጥፋት ምክንያት እንደ አሁን ቀደሙ ማስታወሻቸዉን በየጊዜዉ ለማኅበራዊ መገናኛ ተከታታዮች በየጊዜዉ ማካፈል ባይችሉም አንድ ሁለት ሦስት ጊዜ በአገኙት አጋጣሚ ደህንነታቸዉን የሚገልፅ ፎቶዎችና አጫጭር ማስታዎሻዎችንና ሲያካፍሉ ቆይተዋል። 

የጉዞ ዓድዋ 5 ተሳታፊዎች ዓድዋ ላይ በተዘጋጀዉ ሥነ-ስርዓት ላይ ያዜሙትን በዝግጅቱ ላይ ማድመጥ ይቻላል። 25 ወጣት ተሳታፊዎች የነበሩቡት የጉዞ ዓድዋ አምስት ዝግጅት አራት ሴቶችን ያካተተ ነበር። ሙዚቀኛ ቴዲ አፍሮ አዲስ አበባ መዉጫ ድረስ መቶ እኛ የጎዞ ዓድዋ አምስትን ተጓዦች  "የኢትዮጵያ አምላክ ይከተላችሁ"  ሲል ሽኝት አደረገልል ሲሉ ተጓዦዙ ከፎቶግራፍ ጋር በዚሁ የማኅበራዊ መገናኛ ማስታወሻ ማስቀመጫ ሳጥናቸዉ ዉስጥ ለተከታታዮቻቸዉ አጋርተዉም ነበር። የጉዞዉ ዋና አስተባባሪና የፊልም ሥራ ባለሞያዉ ወጣት ያሬድ ሹመቴ ከጉዞ በኋላ አዲስ አበባ አቀባበል ሥነስርዓት ላይ በስልክ አግኝተነዉ ስለጉዞዉ እንዲህ ተርኮልናል። 

 

«የዘንድሮ ጉዞ የተጀመረዉ ጥር 8 ቀን ነዉ። የ 46 ቀናት ጉዞአችን በርካታ መንደሮችን የገጠር ቦታዎችን እያቆራረጥን ነዉ ያለፍነዉ። ከአዲስ አበባ ከወጣን በኋላ በአራተኛዉ ቀን ማለትም ደብረ ብርኃን ስንደርስ ዋናዉን መስመር ትተን ወደ ግራ አንጎለላ የሚባል ቦታ ገብተን አድረን ነበር። ይህ ቦታ የዳግማዊ አፄ ምኒሊክ የትዉልድ መንደር ነዉ። በተጨማሪም ደግሞ በጣም በዓድዋ ስማቸዉ የገነነዉ፤ የፊታዉራሪ ገበየሁ የትዉልድ ቦታ ብቻ ሳይሆን አጽማቸዉም የሚገኝበት ቦታ ነዉ። አፅማቸዉ የሚገኝ ስንል መቃብር ሳይሆን በመስታወት ማቆያ ዉስጥ ቤተ-ክርስትያን ዉስጥ ሕዝብ ሊያየዉ በሚችለዉ ቦታ የሚታዩ ጀግና ናቸዉ። ዓድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰዉ፤ ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰዉ። ተብሎ የተዜመላቸዉ ስማቸዉ የናኘ ትልቅ ጀግና ናቸዉ።  እኚህ ጀግና የሚገኙበት ነዉ ደብረ ብርኃን አቅራብያ የሚገኘዉ አንጎለላ ትልቅ ታሪካዊ ቦታ። እዚህ ከደረስን በኋላ በሚገርም ሁኔታ ያልጠበቅነዉ ነገር ተከሰተ አንዲት ዉሻ ከዛ ተነስታ ተቀላቅላ ወደ ኋላ እንድትመለስ ብዙ ግፊት ቢደረግባትም ፤ እየዞረች እየመጣች ፤ ማለትም እስከ ዓድዋ ተራሮች ፤ ሶሎዳ ተራራ ጫፍ ማማ ላይ ድረስ ሰንደቅ እስኪሰቀል ድረስ ሳትለይ በእግር ጉዞ የጨረሰች ዉሻ ናት። የክብር ስም ሰጥተናታል። ባሻ ቡቺ ትባባለች። »

በርግጥ ባሻ ቡቺን ወደ አዲስ አበባ ለማምጣት ችግር እደነበረ አቶ ያሬድ በቃለ ምልልሱ ወቅት ቢነግረንም ከቀናትበኋላ ቡቺ አዲስ አበባ መግባትዋን ሰምተናል።  

«ለኛ ይህ የሚያሳየን የዓድዋ ድል በዓል እንስሳ ሁሉ የተሳተፉበት በቅሎ አህያ ግመልና ፈረስ፤ ትልቅ ቦታ ነበራቸዉ። በጠባቂነት ሚና ብቻ ሳይሆን በሸክምም በተለያዩ ግልጋሎቶች ላይ ተሳትፈዋል። በተለይ ከመሃል አገር ከወረይሉ ተነስተዉ አጠቃላይ የኢትዮጵያን የስንቅ ማቀበል ስራ ይሰሩ የነበሩ ቢትወደድ አጥናፍ ወልደዮኃንስ የሚባሉ ሰዉ ነበሩ። ቢትወደድ ስድስት ሺህ ግመል አሰማርተዉ ጦርነቱ በተካሄደባቸዉ ወረይሉ አምባላጌን መቀሌን ጨምሮ ብዜ ተሳትፎን አድርገዋል።»   

የጉዞ ዓድዋ 5 ዘማቾች በጉዞ ላይ ሳሉ በሃገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች የሚከሰቱትን ግጭቶች በተመለከተ ማስታወሻቸዉ ላይ ይፅፉ ነበር ፤  ለሚመለከተዉ አካል ይፍዊ ጥያቄንም ያስተላልፉ ነበር። በወልዲያ ወገኖቻችን ላይ በረሰው ሞት እና የአካል ጉዳት የተሰማንን ልባዊ ሀዘን ለመግለጽ እንወዳለን። ሀገራችን እና ህዝቧ ሰላም እንዲሆኑ ሀላፊነት ሊወስድ የሚገባው የመንግስት አካል ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ በቀደሙ ለሀገር ነጻነት በተሰዉ የዓድዋ ጀግኖች ስም እንማፀናለን ይላል።

«በየቦታዉ ስንደርስ ከፍተና አቀባበል ተደርጎናል እንደ አምናዉ ወይም እስከዛሬዉ ሁሉ። ያለፍንባቸዉ አብዛኞቹ ቦታዎች፤ በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት ሰላም ያልነበረባቸዉ ቦታዎች ነበሩ። እዚህ ቦታዎች ላይ የነበሩ አቀባበሎች ደብዘዝ ያሉ ቢሆንም አብዛኞቹ ቦታዎች ላይ ግን በጣm ደስ የሚል አቀባበል ነዉ የተደረገዉ።  መቀሌ ዩንቨርስቲ በየዓመቱ እኛን በክብር ይቀበላል። በተለይም የእንዳ እየሱስ ምሽግ መልሶ ከተገነባ እና በሙዚየምነት አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በኋላ ከዩንቨርስቲዉ ጋር በጣም የጠነከረ ግንኙነት አለን። እዛ ተገንተን ዉስጥ እግርራችን ተማሪዎች አጥበዋል በጣም ዉስጥን የሚያቃጥል የኢትዮጵያዊነት ባህሪ አጉልቶ የሚያወጣ ነበር። በጣም ደስ ይላል። እናም በዝማሪ ምስጋናችንን አቅርበን በዓድዋ ጀግኖቹን እያነሳን እያወደስን መሪዉ ዋናዉ አስተባባሪዉ ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ናቸዉና እሳቸዉን በክብር የሚነሳ ዜማን መቀሌ ላይ አሰምተናል።»  

ዓድዋ  መዲና ተራሮችዋ ታሪክን ይናገራሉ፡፡ 122ኛዉ የአፍሪቃ የጉዞ ዓድዋ 5 ተጓዦች ዓድዋ ሲደርሱ የዓድዋ ክብረ በዓል ላይ የክብር እንግዶቾ የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ፤የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም እና የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊው አቶ ዳዊት ኃይሉ በክብር እንግድነት ቦታቸዉን ይዘዉ ነበር። የብሔራዊ ቲያትር አርቲስቶችም ታሪክን የሚዘክር አጫጭር ተዉኔት በበዓሉ ላይ አቅርበዋል። ከበዓሉን ለማክበር ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጣዉ ታዳሚ የሶሎዳን ተራራ ከቦ ቆሞአልል። ከኢትዮጵያ አልፎ የጥቁር ሕዝቦች ግንባር ቀደም ተምሳሌት የሆነዉ የዓድዋ ድል የካቲት 23 ቀን በሃገሪቱ ሲከበር በዓለም ሕዝቦች ዘንድ በታሪክ ማኅደር ሲወሳ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከአዲስ አበባ ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በዚሁ እለት ማፅደቁ በርግጥ ሁኔታዉን አወዛጋቢ አርጎት ዉሎአል።

ምንም እንኳ ከአዲስ አበባ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ይለጠፍ የነበረዉ ፎቶግራፎች ታሪካዊ በዓሉን በድምቀት እየተከበረ መሆኑን ገላጭ ቢሆኑም፤ በሌሎች አካባቢዎች ተቃዉሞዎች መቀጠላቸዉን የሚያሳዩ ዘገባዎችና ፎቶግራፎች በዚሁ እለት ይፋ ሆነዋል።  ዘንድሮ ከአዲስ አበባ ተጉዘዉ ሶሎዳ ተራራ የደረሱት ተጓዦችም በዝግጅቱ ላይ መድረክ እንዳልተሰጣቸዉ በኃዘኔታ ተናግረዋል።

የዳግማዊ አፄ ምኒልክን ስም በጉልህ ለማወደስ ያደረግነው ጥረት ተሳክቶልን በድል እርምጃችንን ጨርሰን አዲስ አበባ ተመልሰናል፤ ደስ ብሎናል ያሉት የጉዞ ዓድዋ 5 ተካፋዮች፤ የዛሬ ሳምንት ሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2010 ዓ.ም የዘንድሮውን የዓድዋ ድል ክብረ በዓል የመዝጊያ ዝግጅት እናደርጋለን ሲሉ ይፋ አድርገዋል። 25ቱም ተጓዦች የዓድዋ ድል ጀግኖቻቸውን ያስተዋውቃሉ፤ ባሻ ቡቺም ትገኛለች ብለዋል። ዝግጁ ናችሁ ሲሉ ጥያቄያቸዉን አቅርበዋል። ለቃለ ምልልሱ የጉዞ ዓድዋ አምስት ተጓዦችን እያመሰገንንን ሙሉ ቅንብሩን የድምጽ ማድመቻ ማዕቀፉን በመቻን ሙሉ መሰናዶዉን እንድያደምጡ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ  

ሸዋዬ ለገሠ  

 

 

 

Audios and videos on the topic