1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

የዓድዋ ድል በዓል በአሜሪካ

እሑድ፣ የካቲት 24 2016

"ነጮች በዘራቸው ንጹህ ስለሆኑ፣ ከሰው ሁሉ በላይ ናቸው፣ ማንም ነጭ ያልሆነ ነጭን ሊያሽንፍ አይችልም የሚል እምነት ለ500 ዓመታት፣ አሜሪካ ከተቆረቆረች ጊዜ ጀምሮ ያራምዱ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ነጭን በከፍተኛ ደረጃ ያዋረደ ሰው ቢኖር ሚኒሊክ ነው ብሎ አንድ እንግሊዛዊ ጽፏል። " የታሪክ ሙሁር ፕሮፌሰር ሃይሌ ላሬቦ

https://p.dw.com/p/4d7F7
Äthiopien Siegesdenkmal von Adwa, Addis Abeba
ምስል Seyoum Getu/DW

የዓድዋ ድል በዓል በአሜሪካ

የዓድዋ ድል በዓል መታሰቢያ ፣በአትላንታ የኢትዮጵያውያን ማኀበረሰብ ማኀበር ውስጥ ትናንት ሲከበር፤የየካቲት 12 መታሰቢያ እና የካራማራ ድል በዓሎችንም ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያኑ አያይዘው አክብረዋል።

የዓድዋ ድል አንደምታ በታሪክ ምሁሩ ዕይታ

የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት በጆርጂያው ሞር ሐውስ ኮሌጅ የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ኀይሌ ላሬቦ፣ባደረጉት ንግግር ማኀበረሰቡ ታሪክና ማንነቱን እና ታሪኩን እንዲኖር፣ማኀበሩ የሚያደርገው ጥረት የሚመሰገን እና የሚደነቅ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። የዓድዋ ጦርነት ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያና የጣልያን ተደርጎ ብቻ እንደሚታይ የገለጹት የታሪክ ምሁሩ አያይዘውም፤

" እስከ ዓድዋ ድረስ በዓለም ከፍተኛ ዘመቻ እና ጉዞ ያደረገው መሪ ቢኖር ናፖሊዮን ነው።ናፖሊዮን ወደ ሩሲያ ሲጓዝ 490 ማይልስ ጉዞ አድርጓል፤ያም ሦስት ወር ነው የወሰደው።የዓፄ ምኒልክ ግን አምስት ወር ነው የወሰደው፤ 580 ማይልስ ነው። እንግዲህ በጣም በታሪክ የመጀመሪያው ክብረወሰን የሚሰብር ነው ማለት ነው።" ሲሉ ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር ኀይሌ፣ የዓድዋ ድል በሁለተኛ ደረጃ በታሪክ በከፍተኛ ደረጃ የሚታወቅበትን ምክንያት ሲያስረዱም የሚከተለውን ተናግረዋል።

"ለአምስት መቶ ዓመታት ያህል በዓለም ላይ ሰፍኖ የነበረውን ርዕዮተ ዓለም፣ የሰው አመለካከት ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጥማጡን አጠፋ።ያ እምነት ምንድነው ነጮች በዘራቸው ንጹህ ስለሆኑ፣ ከሰው ሁሉ በላይ ናቸው፣ ማንም ነጭ ያልሆነ ነጭን ሊያሽንፍ አይችልም የሚል እምነት ለ500 ዓመታት፣ አሜሪካ ከተቆረቆረች ጊዜ ጀምሮ ያራምዱ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ነጭን በከፍተኛ ደረጃ ያዋረደ ሰው ቢኖር ሚኒሊክ ነው ብሎ አንድ እንግሊዛዊ ጽፏል። እንግዲህ ይህ ነው የዓድዋ ታላቅነት።"

ሁሉም የሰው ልጅ ዘር አንድ ነው፣ትክክል ነው፣ አንዱ ከፍ ሌላው ዝቅ አይልም የሚለው ትምህርት፣በዓፄ ሚኒልክ የዓድዋ ድል ዘመቻ መጀመሩን እና ለሌሎችም  የነፃነት ጮራ የፈነጠቀ ድል መሆኑንም የታሪክ ምሁሩ  አብራርተዋል።

የታሪክ ሙሁር ፕሮፍሰር ሃይሌ ላሬቦ በመድረኩ ንግግር ሲያደርጉ
የታሪክ ሙሁር ፕሮፍሰር ሃይሌ ላሬቦ በመድረኩ ንግግር ሲያደርጉምስል Tariku Hailu /DW

ድሉ  የኢትዮጵያውያንን ህብረት ያጠናክራል

የአትላንታ ማኀበረሰብ ማኀበር ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ንጉስ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያኑ የድል በዓላቸውን አንድ ላይ ማክበራቸው ህብረታቸውን የሚያጠናክር ተግባር መሆኑን አመልክተዋል።

"ይህ ከሀገራችን ውጭ ያለ፣ ኢትዮጵያን የሚወክል ቦታ ነው።የዓድዋ በዓል በኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማክበር፣ዓድዋን ከየአካባቢው፣ከየጎሣው፣ከኃይማኖቱ ተሰባስበው የጣሊያንን ወረራ እንደተከላከሉ ሁሉ፣ እዚሁ ባለንበት ከተማ ኢትዮጵያውያን ተሰባስበን ታሪካችንን፣ አንድነታችን የተለያየ ባህል ኖሮን ከእኛ የበለጠ እውቀት የነበራቸው አባቶቻችን፣ይህን የመሰለ ትልቅ እሴት ወይም ገድል ለትውልድ አስተላልፈዋል።"

 የማህበሩ ዳይሬክተር አቶ መርዕድ አለማየሁ በፈንታቸው፣ የኢትዮጵያ ቀደምት መሪዎች፣በከፈሉትት መስዋዕትነት፣ አሁን ያለው ትውልድ በነፃነት ቀና ብሎ እንዲራመድ ያስቻሉበትን ሁኔታ እንደሚከተለው ገልጸውታል።

 "ኢትዮጵያ በህሊናችን ዕሳቦት፣ በልባችን ደም ምትና በስጋ አጥንታችን ስሪት ውስጥ የናኘች ኑባሬ ናት ብለው ስለሚያስቡ ነው ለዚህ መስዋእትነት የተዘጋጁት።"
በዚሁ ክብረ በዓል ላይ፣የዓድዋ ድልን የተመለከተ የሥዕል ዓውደ ርዕይ፣ ተውኔት፣ ስነ ግጥሞችና የሙዚቃ ድግስ ቀርቧል።

ከበዓሉ ታዳሚዎች በከፊል
ከበዓሉ ታዳሚዎች በከፊልምስል Tariku Hailu /DW

"የመላው ጥቁር ህዝቦች ኩራት"

በተመሣሣይ ሁኔታ፣128ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል፣ "ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል" ቡድን በሚል ቃል፣ በዩናይትድ ስቴትስ ምዕራባዊ ክፍል በሚኖሩ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አባላት በበይነ መረብ አማካይነት ተከብሯል።  የበዓሉ የክብር እንግዳ፣ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልእክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶክተር ስለሺ በቀለ ለዝግጅቱ ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት፣የዓድዋ ድል በዓል፣ ለኢትዮጵያኖች ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ህዝቦች ኩራት መሆኑን አውስተዋል።
በዚህ የዓድዋ ድል መታሰቢያ  በዓል ላይ የዕምነት አባቶች፣ የኪነጥበብ ሰዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣የኢትዮጵያ ወዳጆች እና ዲያስፖራ አደረጃጀቶች አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን፣ከኤምባሲው ማኀበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ ካገኘነው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
ታሪኩ ሃይሉ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር